1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግብፅ ከሙባረክ በኋላ እና ወጣቱ

ዓርብ፣ የካቲት 4 2008

የግብጹ የቀድሞ መሪ ሆስኒ ሙባረክ ከስልጣን ከተወገዱ ትናንት ( ሀሙስ) አምስት ዓመት ሞላቸው። በወቅቱ ታህሪር አደባባይ የተሰበሰበው ግብጻዊ በደስታ ፈንጥዟል። ዛሬ ከአብዮቱ አምስት ዓመት በኋላስ? የሀገሬዉ ወጣት በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

https://p.dw.com/p/1Hu1h
Ägypten Tahrir-Platz am 5. Jahrestag der Revolution
ምስል Reuters/M. Abd El Ghany

ግብፅ ከሙባረክ በኋላ እና ወጣቱ

የቀድሞ የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ከስልጣን ከተወገዱ እነሆ አምስት ዓመታት ተቆጠሩ። በወቅቱ ሙባረክን ለማስወገድ ታህሪር አደባባይ ለተሰበሰበው ግብጻዊ ሶስት ሳምንት እንኳን አልፈጀበትም ነበር። ለመሆኑ ያኔ ሙባረክን ተቃውመው አደባባይ የወጡት ግብፃዊያን እነማን ነበሩ? « ጥር እና የካቲት 2011 ዓም ታህሪር አደባባይ የተሰበሰቡት በርካታ እና የተለያዩ ሰዎች ነበሩ። አብዮቱ በወጣቶች ነበር የተቀሰቀሰው። ነገር ግን የሠራተኞች ማኅበር፣ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ኋላም የሙስሊም ወንድማማቾች እና የህዝቡን ተመሳሳይ ጭንቀት የሚጋራው፤ ለነፃነት እና ለእኩልነት የቆመ ተራው ህዝብም ነበር።»
ይላሉ፤ በበርሊን ዩንቨርስቲ የፖለቲካ ፕሮፌሰር የሆኑት ሲሊያ ሀርደርስ። ሚዳን አት ታህሪር « የነፃነት አደባባይ» የሚል ትርጓሜ ያለው ሜዳ በአስር ሺ በሚቆጠሩ ተቃውሞ ሰልፈኞች ሲከበብ በወቅቱ የ 19 ዓመት ወጣት የነበረው ካሪም ፋሪድ ከሰልፈኞቹ አንዱ ነበር።« ከመጀመሪያው ቀን ረፋዱ ላይ አንስቼ እዛ ነበርኩ። በፍጥነት የወሰንኩት ውሳኔ ነበር። በሀገሪቱ የሚሆነውን በሁለቱም ዓይኔ እመለከት ነበርና እንደ አንድ ወጣት በወቅቱ የተመኘሁት ተስፋ ነበር።»የአብዮቱ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሌሊት የጸጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጢስ እና የፖሊስ ቆመጥ ተጠቅመው አደባባዩን ነጻ አድርገዋል። ያኔም በርካታ ሰልፈኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ። ከሶስት ቀናት በኋላም የተቃዉሞ ሰልፈኞቹ ስፍራውን መልሰው አጥለቀለቁት፤ ቦታውንም የምንለቀው ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ስልጣን ከለቀቁ ብቻ ነው አሉ።«ታህሪር አደባባይ የተሰማኝ ስሜት ለመግለፅ የሚከብድና ህይወቴን ሙሉ በሙሉ የቀየረ ነው። የተለያዩ ሰዎች ነበር ያገኘሁት፤ ለዘብተኛውን፣ ግራውን፣ አክራሪ ሙስሊሙን። ሁሉም እዛ ሆነው ለነፃነት እና ለእኩልነት ነበር የሚታገሉት። ወዲያዉም ተስፋ ይታይ ጀመር።»
« መንግሥት ስልጣን እንዲለቅ ህዝቡ ይፈልጋል» የሚለው መፈክር ተደጋግሞ ይሰማ የነበረ መፈክር ነበር። አብዮቱ በተጀመረ ሳምንትም የመንግሥት ኃይላት ግመል፤ ፈረስ እና ጦሩን ተጠቅመው ለመጨረሻ ጊዜ አደባባዩን ለመቆጣጠር ሞከሩ። ይሁንና ተቃውሞ ሰልፈኞቹ እጅ ሳይሰጡ ስፍራውን እንደያዙ ቀሩ። ዛሬ ይህ ስፍራ የግብፅ ነፃነት መታሠቢያ ቦታ ነው።
የአደባባይ ሙዚቀኞች አላፊ አግዳሚውን በሙዚቃ ያዝናናሉ። ነገር ግን የቀድሞ የግብጹ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ከስልጣን ከተወገዱ አምስት ዓመት በኋላ በሺ የሚቆጠሩ የመንግሥት ተቺዎች እና ተቃዋሚዎች በግብፅ ወህኒ ቤት ይገኛሉ። በርካታ የመብት ተሟጋቾች ተገድለዋል። ከአምስት አመት በፊት አብዮቱ ሲጠነሰስ የነበሩ ለግብፅ ነፃነት የታገሉ የሲቪክ ማህበረሰብ አሁንም አሉ ይሆን? አዎ! ይላሉ የፖለቲካ ምሁር ሲሊያ ሀርደርስ። « ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረው አብዮት ተሞክሮ የተለወጡ እና ማህበረሰቡን የሚያበረታቱ በርካታ ወጣት እና ጎልማሶች አሉ። በርግጥ ለማንሳት የማይደፈሩ የፖለቲካ ጉዳዮች አሉ። ይሁንና ለዚህ ነፃነት የታገሉት በተለይ ወጣቶች ዝም ብለው እጅ አይሰጡም። »
ይሁንና በሀገሪቱ አሁን ድረስ ያለው የኃይል ርምጃ በርካቶችን ዝም እንዳስባለ ሀርደርስ ይናገራሉ። ከአምስት ዓመታት በፊት ለአብዮቱ ትልቅ ሚና የተጫወቱ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም ቢሆኑ ሀሳብን በነፃ ለመግለፅ አሁን አማራጭ አይደሉም። ሀርደርስ እንደሚሉት ሰዎች ኢንተርኔት ላይ ይፋ በሚያደርጉት ሃሳብ የተነሳ ለእስር እና ለክስ ተዳርገዋል። ታድያ በርካቶች አደባባይ ከወጡበት አብዮት እና የነፃነት ትግል አሁን ህዝቡ የተረፈው ምንድነ ነው? ሀርደርስ ያብራራሉ « በአረብ ሃገራት የተደረጉት አመፆች የማህበረሰቡን የፖለቲካ አመለካከት እጅጉን የለወጡ ይመስለኛል። ይሁንና የነፃነት መብትን ማስከበር፣ የተለያዩ የማህበረሰቡ አካልን ያሳተፈ አስተዳደር መመስረትን በተመለከተ ግብፅ ላይ በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታ የተቃራኒው ነው። ለምሳሌ የመንግሥት ስልጣኑን የያዘው ጠንካራ ወታደራዊ የጦር መሪ የነበረ ሰዉ ነው። ትርምስ ከታየበት ዓመታት በኋላ ጠንካራው መንግሥት ችግሩን እንዲፈታ ምኞት ነበር። አሁን ጠንካራ መንግሥት አለ። መንግሥት እየሠራ ያለው ግን ጭቆናውን ማጠናከር ነው። ይህ ደግሞ ጥርጣሬ እና ፍርሀት ፈጥሯል። ግብፅ ውስጥ ለፖለቲካ ተሳትፎ የሚከፈለው ዋጋ ከፍ ያለ ሆኗል።»
በዚህ ካሪም ፋሪድ ይስማማል። ጋዜጠኛ መሆን የሁልጊዜ ምኞቱ የነበረው ካሪም ከግብጹ አብዮት በኋላ በሀገሪቱ ታዋቂ ለሆነው « አክሂር ካላም» የቴሌቪዥን ጣቢያ ይሠራል። የታገለለት ነፃነት ግን ዛሬም አልተከበረለትም።« መንግሥት ሀሳብን በነፃ የመግለጽ መብትን እየታገለ፣ ፍርሃትን ያንሰራፋል። ከነፃነት እና ዲሞክራሲ እንድንርቅ ተደርገናል። ፖሊስ ከለላ ስለሚያደርግልን ውደሱት እንባላለን። መንግሥት በዚህ አመለካከቱ የግል ህይወታችን፣ መብት እና ነፃነታችንን እየተጋፋ ነው ያለው።»
ካሪም የሚሰራበት የቴሌቪዥን ጣቢያ ተዘግቷል። ወጣቱም በሀገሪቱ ተስፋ ስለማይታየው ዱባይ ውስጥ ስራ የሚያገኝበትን መንገድ እያፈላለገ ይገኛል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በርካቶች ላይ ከተበየነው የሞት ፍርድ በተጨማሪ በሀገሪቱ በ10 ሺ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች እንዳሉ ይናገራሉ። አሁን ሀገሪቷን የሚያስተዳድረው የፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ መንግሥት ከሙባረክ ብሶ ይሆን?« ይህ ተቃዋሚዎቹ ከመጀመሪያው አንስቶ ሲሉ የነበረው ነው። አል ሲሲ ስልጣን ስይዙም በተደጋጋሚ የተሰማ አረፍተ ነገር ነው። « ከሙባረክ የባሰ ጊዜ ነው» የሚል። በሙባረክ ስርዓት ስር የተፃፉትም ሆኑ ያልተፃፉት ህጎች የታወቁ ነበሩ። ህዝቡም ይሁን የፖለቲከኛ ተሟጋቾች ገደባቸውን ያውቁ ነበር። ለፖለቲካ አመፅ የሚከፍሉትን ዋጋ ማገናዘብ ይችሉ ነበር። መንግሥት ተሟጋቾችን አሁን እንደሚታየው በተጋነነ ሁኔታ አይጨቁንም ነበር። በአሁኑ ሰዓት በሰፊው እና በጅምላ ነው የሚፈፀመው የጭቆናውን መጠን መገመት ያዳግታል። ይህ ደግሞ የማንም አምባገነን መንግሥት መሰረት ነው። ፍርሃት መፍጠር፤ ፍርሃት ደግሞ ሰዎች ለሚወስዱት ርምጃ የሚጠብቃቸውን ሳያውቁ ሲቀሩ ይፈጠራል።»
ግብፅ አሁንም የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የምትገኝ ሀገር ናት። ሙስና ለዚህ ዋና ሚና ይጫወታል። የወጣት ስራ አጡ ቁጥር 40 በመቶ ይገመታል። የወጣት ግብፅያኑ ተስፋ ዛሬ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?« ይህ ችግር በ2013 የህዝብ ንቅናቄ ፕሬዚዳንት ሙርሲን ከስልጣን ካስወገደ አንስቶ ያለ ነው። ከዛ በኋላ የተከተለው በኋይል የታገዘ ጭቆና ወጣቱን ፤ጎልማሶቹንም ጨምሮ በቂ እየታገላችሁ አይደለም። ወደ ሊቢያ ሄደን አል ቃይዳን ወይም እስላማዊውን መንግሥት እንቀላቀል የሚል ስጋት ይፈጥራል። በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣን ላይ አንድ ጠንካራ የጦር ሰራዊት አባል ተቀምጦ ምንም ነገር አይንቀሳቀስም የሚል ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ይፈጥራል። የስደት ፍላጎቱንም ከፍ ያደርገዋል።»
ልደት አበበ
ሸዋዬ ለገሰ

Symbolbild Arbeitslosigkeit in Ägypten
የግብፅ ስራ አጥምስል Getty Images/J. Mitchell
Symbolbild - Ägypten Rotes Meer
የግብፅ የቱሪስት መስብምስል picture-alliance/dpa
Ägypten Menschen feiern den 5. Jahrestag der Revolution am Tahrir-Platz
የአብዮቱን 5ኛ ዓመት የሚያከብሩምስል Reuters/M. Abd El Ghany