1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግብ ወሳኙ የሥነ ቴክኒክ ዳኛ፣

ረቡዕ፣ ሰኔ 12 2005

በዓለማችን ከ 87 ዓመታት በኋላ፣ በሥነ ቴክኒክ የተራቀቀው ዓለም፤ በተለይ፣ በኮምፒዩተሩ ዓለም፤ በመገናኛዎች ፤ በኢንዱስትሪዎችና በተለያዩ መ/ቤቶች፤ ተግባራትን አቅደው የሚያከናውኑ፤ ውሳኔ የሚሰጡ«ሮቦቶች» እንጂ ሰዎች ላይሆኑ እንደሚችሉ ሲነገር እንሰማለን።

https://p.dw.com/p/18t9k

እየተጻፈም እናነብባለን። ቀላል የሚመስለው ሆኖም ፤ በዓለም ዙሪያ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረውን እግር ኳስ አፍቃሪ ህዝብ የሚያነጋግረው አንዱ ጉዳይ፤ ካለፈው ሳምንት ማለቂያ አንስቶ ብራዚል ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው የኮንፌደሬሽን ዋንጫ ውድድር ፤ በተለይ ለመሃል ዳኛና ለመሥመር ዳኞች፣ አጠራጣሪ የሚመስልን ግብ ፣ ማረጋገጥ የሚችለው ፤ «ጎል ኮንትሮል» የተሰኘው አንድ የጀርመን ኩባንያ ሠርቶ ያቀረበው ከካሜራ ለዳኞች በግማሽ ሴኮንድ ፣ መልእክቱን (ውሳኔውን ) የሚያሳውቀው ፣ በ 14 ወይም 16 ካሜራዎች እርዳታ በ3 ማዕዝናት የሚያነሣውን የኳስ መድረሻ ውጤት እንቅሥቃሴ ውጤት ፣ ኳስ ፣ የግቡን መሥመር ከአየርም ሆነ ከየብስ ማለፍ አለማለፏን ፣ ግብ መሆን አለመሆኗን የሚያመላክተው ሥነ ቴክኒክ ነው።

Computeranimation Torlinientechnik GoalControl
ምስል picture-alliance/dpa

ይህ ሥነ- ቴክኒክ ሥራ ላይ እንዲውል ያስገደደበት ምክንያት ምን ይሆን?የመጀመሪያው ታሪካዊ መንስዔ ፤ ከ 47 ዓመት ገደማ በፊት፤ በሐምሌ ወር 1958 ዓ ም፤ (እ ጎ አ ሐምሌ 30,1966 ) ኢንግላንድ በዓለም የእግር ኳስ ፍጻሜ ግጥሚያ፤ ምዕራብ ጀርመንን በሰዓት ጭማሪ 4-2 አሸንፋ የዋንጫው ባለቤት ለመሆን የበቃችበት ውጤት በተለይ የኢንግላንድ 3ኛ ጎል አከራካሪነት ነው። የፊት አጥቂ ጀፍ ኸርስት፣ ጊዜ ከተጨመረ በኋላ፣ በ 11ኛው ደቂቃ የመታት ኳስ የግቡን አግዳሚ እንጨት ውስጠኛውን ክፍል ከመታች በኋላ በኖራ ከተሠመረበት መስመር ላይ ነጥራ ብትመለስም፤

የመስመር ዳኛው ግብ መሆን አለመሆኗን ለጠየቋቸው አጫዋች ዳኛ ምልክት በመስጠታቸው ግቡ ጸደቀ። ያኔ ጨዋታውን በቴሌቭዥን የተከታተሉ 400 ሚሊዮን ያህል ተመልካቾችና በእስታዲዮም የነበረውም ተመላካች ግን ክርክር ውስጥ መግባቱ አልቀረም። «የዳኛ ውሳኔ አይሻርም» በሚለው የፊፋ ደንብ መሠረት ውጤቱ እንዲጸና ተደረገ። ከዚያም በኋላ 4ኛው ግብ ተከተለ። ጀርመናውያን እስካዛሬ ድረስ ለኢንግላንድ በተሰጠችው፣ ግብ መሥመር ላይ የነጠረችውን ኳስ «የዌምብሊ ግብ»( Wembley Tor)የሚል ስያሜ በመስጠት በቁጭት ከማስታወስ ችላ ያሉበት ጊዜ የለም።

Dirk Broichhausen GoalControl mit Torkamera
ምስል picture-alliance/dpa

ከዚያ ወዲህ ፤ በየሃገራቱ በተለያዩ ጊዜያት የእግር ኳስ ክለቦች ግጥሚያ ፤ የሻምፒዮና ውድድር ጭምር የዌምብሊ ዓይነት ግብ አላጋጠመም ባይባልም ፣ ይበልጥ የሚታወሱት፤ እ ጎ አ ከ 1966 ቱ የዓለም ዋንጫ ወዲህ ማለት ነው፤ በ 2010 ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ፤ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ውድድር፣ ጀርመን ከምድብ ተጋጣሚዋ ኢንግላንድ ጋር ፣በ2ኛ ዙር ግጥሚያ ፣ ጀርመን፣ ከዕረፍት በፊት 2-1 በመምራት ላይ ሳለች፤ የኢንግላንድ ብሔራዊ ቡድን የመሃል ሜዳ ተጫዋች ፍራንክ ላምፓርድ ከሩቅ የመታት ኳስ የግቡን መሥመር አልፋ በመንጠሯ ግብ እንደነበረች ቢታወቅም፤ ዳኛው ጨዋታው እንዲቀጥል በመወሰናቸው፤ የተናደዱት የኢንግላንድ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በአጠቃላይ 4-1 ተሸንፈው ነበረ የወጡት።

ይህ ብቻ አልነበረም ፤ እ ጎ አ በ 2012ም ተሠለሰ ። በአውሮፓ አገሮች የሻምፒዮና ውድድር፤ ከፖላንድ ጋር በተዳባይነት ያስተናገደችው ሀገር ዩክሬይን፤ ከኢንግላንድ ጋር ባደረገችው ግጥሚያ መሥመር አልፋ አየር ላይ ግብ ልትቆጠር የሚገባትን ኳስ፣ የኢንግላንድ ተከላካይ ጆን ቴሪ በእግሩ መትቶ ያስወጣበት ሁኔታ ዩክሬይንን እንደጎዳት ለተመልካች ግልጽ ነበር። ዳኛ ግን ዩክሬይንን ግብ ነፍገው ጨዋታው እንዲቀጥል ነበረ ያደረጉት።

እነዚህና የመሳሰሉት ክሥተቶች ናቸው እንግዲህ ፣ የዓለም የእግር ኳስ ፌደሬሽን (FIFA)በረዳቱ ሥነ ቴክኒክ ላይ እንዲመካ የገፋፋው። ታዲያ በዚህ ረገድ ከብዙዎቹ የዚህ ሥነ ቴክኒክ ባለቤቶች ከሆኑ ኩባንያዎች መካከል በምዕራብ ጀርመን ፤ አኸን ከተማ አቅራቢያ ፤ Würselen በተባለች ንዑስ ከተማ የሚገኘው ለራሱ የንግሊዝኛ ሥም በመስጠት «ጎል ኮንትሮል » የተሰኘው ኩባንያ ሆኗል በፊፋ የተመረጠውና መሣሪያውን ሰሞኑን በብራዚል በመካሄድ ላይ ላለው የኮንፈደሬሽን ዋንጫ ውድድር በየእስታትዲየሙ ካሜራዎቹ እንዲተከሉ ያደረገው ። በእያንዳንዱ የመወዳደሪያ የእግር ኳስ ሜዳ ፣ እስታዲዮም ጣሪያ ላይ፣ በየግቡ አናት ላይ ፣ ሰባት ፤ ሰባት ፤ ባጠቃላይ 14 ካሜራዎች ናቸው የሚተከሉት። ካሜራዎቹ ከልዩ «ሶፍትዌር» ጋር ግንኙነት አላቸው። እናም መሣሪያው፣ ግብ አካባቢ ኳሷ የምትገኝበትን ቦታ፤ በ3 ማዕዘን ተንቀሳቃሽ ምስል በማቅረብ መረጃ ይሰጣል። ለእያንዳንዱ እስታዲየም በዚህ መሣሪያ ለመገልገል የ 240,000 ዩውሮ ወጪ ያስፈልጋል።

Fußball Test Kameraüberwachung der Torlinie
ምስል picture-alliance/dpa

የጎል ኮንትሮል ኩባንያ የሥራ አመራር ኀላፊ Dirk Broichhausen ስለመሣሪያው ጠቀሜታ እንዲህ ነበረ በኩራት መንፈስ የተናገሩት።

«መሣሪያው ፤ኳሷ የግቡን መሥመር ስታቋርጥ ፣ ለአጫዋቹ ዳኛ ፤ ወደ ልዩው የእጅ ሰዓት፣ በሴኮንድ ምልክት ይተላለፍለታል። እናም ዳኛው ግብ ናት አይደለችም ለመወሰን መረጃው ያግዘዋል፣»

የጀርመን የ« ፍርውን ሆፈር » የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ምርምር ተቋም፣ ባልደረባ ረኔ ዱዑንክለር ስለ ተጠቀሰው ሥነ ቴክኒክ ጠቀሜታ በበኩላቸው እንዲህ ነበረ ያሉት።

«በውስጡ ፣ የመዳብ ሽቦ የተገጠመላት ኳስ አለችን፣ እናም ይህች ኳስ፣ የግቡን መሥመር ስታልፍ የሚቆጣጠራት መሳሪያ ፣ ያለ ሽቦ መስመር ፤ እንዲሁ በአየር አጫዋቹ ዳኛ በእጁ ላይ ወደሚያሥረው ሰዓት ተላልፎ መረጃውን ያሳያል።»

አሁን እንዳዳመጣችሁት የሥነ- ቴክኒኩ ባለሙያዎች ስለመሳሪያው ጠቃሚነት ነግረውናል። ግን ይህ በተለያዩ ምክንያቶች አንድ ወጥ በሆነ መልኩ ተቀባይነት ያላገኘው --ኳስ ግብ መሆን-አለመሆኗን የሚወስነው መሣሪያ ሥራ ላይ መዋሉ፣ በዓለም ዙሪያ በእግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ ምን ዓይነት ስሜት ይፈጥር ይሆን?! ባልደረባችን የእስፖርት ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ --መሥፍን መኮንን--

መሥፍን መኮንን ፣ የወደፊቱ የአግር ኳስ ጨዋታ ዳኝነት አከራካሪ ሆኖ መቀጠሉ እንደማይቀር እንደጠቀሰው ሁሉ፣ ቀድሞ የጀርመን የአንደኛ ምድብ የእግር ኳስ ክለቦች(«ቡንደስሊጋ») ተጫዋች የነበረው ቶርበን ሆፍማንም፣ እንደ ብዙዎቹ ኳስ አፍቃሪዎች ሁሉ ፣የእግር ኳስ ጨዋታ፣ በሰው እንጂ ፣ በ«ሮቦት» መሳሪያ ሊመራ እንዳማይገባው ያምናል።

«አንድ ቦታ ላይ ገደብ ሊደረግ ይገባል። ማየት የምሻው ፣የግብ መሥመር ሥነ-ቴክኒክ ረዳት ብቻ ሆኖ እንዲያገልግል ነው።»

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ