1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግዙፉ የኬንያ የአበባ ምርት ኢንዱስትሪ እና ተግዳሮቶቹ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 7 2011

ኬንያ ከአለም አራት ትላልቅ የአበባ አምራቾች ሀገር አንዷ ናት። የምሥራቅ አፍሪቃዊቷ አገር ኬንያ በተለይም እንደ ጎርጎራውያን አቆጣጠር ከ 1980ዎቹ ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ የግብርና እና ልማት ክፍለ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ትኩረት ከሰጠቻቸው ዓበይት ዘርፎች አንዱ የአገሪቱን የአበባ ምርት ኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ማሳደግ በዋናነት ተጠቃሽ ነው::

https://p.dw.com/p/3FBVc
Rosenzucht in Kenia
ምስል DW/Philipp Sandner

ትኩረት በአፍሪቃ : የኬንያ የአበባ ምርት

ዛሬ ኬንያ ከኔዘርላንድስ ኮሎምቢያ እና ኢኳዶር ቀጥሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ 4ተኛዋ ለዓለም ገበያ የአበባ ምርቶችን የምታቀርብ አገር ሆናለች:: እነዚሁ ልዩ ልዩ የአበባ ምርቶቿ ደግሞ በተለይም በብሪታንያ በጀርመን በኖርዌይ በአውስትራሊያ በአሜሪካ በሩሲያ በቻይና እና በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ተፈላጊነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መቷል:: መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአሁኑ ወቅት በአበባ አቅርቦት ብቻ ከ 38 በመቶ በላይ የአውሮፓን ገበያ የተቆጣጠረችው ኬንያ ከ 60 በላይ አገራት በዓለም ዙሪያ የአበባ ምርቶቿ ተጠቃሚ ሆነዋል:: ባለፈው ዓመት የመጀመሪያዎቹ 4 ወራት ብቻ ወደ ውጭ ከላከቻቸው የአበባ ምርቶች ከ 423 ሚልዮን ዶላር በላይ ማግኘቷም ታውቋል:: ይህ ግዙፍ የቢልዮን ዶላሮች የውጭ ገበያ ኢንዱስትሪ በኬንያ ከግማሽ ሚልዮን ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድልን የፈጠረ እንዲሁም የአገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ ያሳደገ ይሁን እንጂ ለምርት ግብአቱ የሚያገለግሉት የኬሚካል ማዳበሪያዎች እና ጸረ ተባይ መድሃኒቶች yeተፈጥሮ ባክቴሪያዎች እና ፈንገሶች እንዲሁም ወደ ወንዞች እና ሃይቆች የሚለቀቁ የቆሻሻ ፍሳሾች በኬንያ የውሃ ሃብት በአሳ ማስገር ምርቱ-ዘርፍ በሰውና በእንሣት ሕይወት እንዲሁም በአገሪቱ ሥነ ምህዳር ላይ ከፍተኛ ጉዳት የአካባቢ ብክለት እና የአየር ጸባይ ለውጥን ጭምር ማስከተላቸው ነው የሚነገረው :: የአበባ እርሻ ከፍተኛ የመስኖ ውሃ የሚያስፈልገው በመሆኑም ከ 127 የሚልቁ በመላው አገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ አበባ አምራች ድርጅቶች በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦቱም ላይ ይሄ ነው የማይባል ተጽዕኖ እና እጥረት ማሳደራቸው እየተነገረ ነው::

Schnittblumen aus Kenia - zu Hungerlöhnen geerntet
ምስል dpa

DW በአንድ ዘገባው እንዳመለከተው በተለይም በተለምዶ " የአፍሪቃ የአበባ መደብ " እየተባለ የሚወደሰውና ከግማሽ በላይ የሚልቁ የኬንያ አበባ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማዕከል በሆነው የናይይቫሻ ሃይቅ አውራጃ የአበባ ምርት እርሻ መስፋፋቱን ተከትሎ በውሃው የተፈጥሮ ምህዳር እና በአሳ ሃብት ኢንዱስትሪው ላይ የተከሰተውን አሳሳቢ ብክለት ለመቀነስ ብሎም የአበባ ምርት ኢንዱስትሪ ንግድ ዘርፉን ብቁ እና አስተማማኝ ለማድረግ የጀርመኑ ዓለማቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅት እና ዓለማቀፉ የአየር ንብረት ጥበቃ ቡድን በጋራ በተመረጡ ሁለት ከተሞች በሞምባሳ እና ናኩሩ የሙከራ ፕሮጀክቶችን ጀምረዋል::ከዋና መዲና ናይሮቢ ሰሜናዊ ምዕራብ አቅጣጫ 90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የአገሪቱ ትልቁ ሃይቅ የናይይቫሻ አውራጃ ከውሃ ሃብቷ ባሻገር ለአበባ ኢንዱስትሪ ክፍለ ኢኮኖሚ ተስማሚ አየር ስላላት እና ወደ ውጭ ለሽያጭ የሚላኩ ልዩ ልዩ ምርቶችንም በፍጥነት ለሟጓጓዝ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ዘርፍ ቅርብ በመሆኑ በአካባቢው በርካታ የአገር ውስጥ እና የውጭ አበባ ላኪ ድርጅቶች የከተሙባት ማዕከል ሆናለች:: በኬንያ የአበባ ምርት ኢንዱስትሪ እና ተግዳሮቶቹ ዙሪያ ያሉትን ሁነቶች በተጨባጭ ለመቃኘት DW በስፍራው በመገኘት የጉዳዩን ባለቤቶች በቀጥታ አነጋግሯል::

የአበባ ምርቶች ለውጭ ገበያ የሚዘጋጁበት ሰፊ አዳራሽ ጥዑም መአዛ ከሩቅ መንፈስን ያውዳል:: በዚህ ክፍል በመቶዎች የሚቆጠሩ ልዩ ልዩ የሚያምሩ የጽጌረዳ አበባዎች በጠረጴዛው ላይ በዓይነት በዓይነቱ ተሰድረው ይታያሉ::ከፈዛዛ ቢጫ እስከ ደማቅ ብርቱካናማ ከጥቁር እስከ ቀይ የጽጌረዳ አበባ ድረስ በጥንቃቄ ጥራታቸውን እንደጠበቁ ተለይተው ተዘጋጅተዋል:: የአበባ ምርት ሰራተኞቹ በአዳራሹ ውስጥ ለገበያ የተዘጋጀውን እያንዳንዱን አበባ ከሚዋጋ እሾህ እና ልዩ ልዩ ተባይ ነጻ መሆኑን ይቆጣጠራሉ:: ከዚህ ሌላ አትክልትን ከሚያጠቃ ፈንገስ እና ባክቴርያ ጽዱነቱን በሚገባ አረጋግጠው በሚፈለገው መጠን ቁመታቸውን አሳጥሮ ማዘጋጀት በመጨረሻም አበባዎቹ ሳይጠወልጉ እንዲቆዩ የሚረዳና ባክቴሪያን የሚከላከል ንጠረ ውሁድ በተቀላቀለበት ውሃ የሞላ ባልዲ ውስጥ መክተት ቀዳሚው ስራቸው ነው:: ይህ ሁሉ ተግባር ባለሙያዎቹ በጥንቃቄ እና በቅልጥፍና ያከናውናሉ::

Kenia Blumen werden verpackt
ምስል AP

" ይህ አጠቃላይ የአበባ ምርቶችን ለገበያ የማዘጋጀት ሂደት ቢበዛ 45 ደቂቃ ያህል ጊዜ ነው የሚወስደው:: የምርት ጥራቱን ከምንቆጣጠርባቸው ቀዝቃዛ ክፍሎች እስከ አበባዎቹ ተጠቅልለው እስከሚታሸጉበት ሂደት ድረስ ማለት ነው:: "  የአበባ ምርቶቹ በማቀዝቀዣ ክፍል ውስጥ ጉዳት ሳይደርስባቸው ለረጅም ጊዜ መቆየት እንደሚችሉ የምርት ተቆጣጣሪ ባለሙያው ጆሴፍ ካራንጃ ይናገራል:: ይህ ደግሞ ምርቶቹ ከሚሰበሰቡባቸው የአበባ እርሻዎች ጀምሮ በዓለም ዙሪያ በትራንስፖርት አጉዋጉዘን ለምናቀርባቸው ገበያዎች ሳይጠወልጉና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲደርስ ለማድረግ ይረዳል:: "ምርቶቹን የማዘጋጀቱ ሂደት ከ 18 እስከ 20 ዲግሪ የሙቀት መጠን ባለው ክፍል ውስጥ ነው የሚከናወነው:: ቀጣዩ ተግባር አበባዎቹ እንዳይበጣጠሱ እና ጥራታቸውም እንዳይቀንስ ከጉዞ በፊት እስከ ሁለት ዲግሪ ቅዝቃዜ ባላቸው ክፍሎች ምሽቱን እንዲቆዩ ማድረግ ነው:: "

Rosenzucht in Kenia
ምስል DW/Philipp Sandner

የአበባ ምርቶቹ ልዩ ማቀዝቀዣ ባላቸው ትላልቅ ተሽከርካሪዎች አማካኝነት ወደ አውሮጳና የተለያዩ አገራት በሚጓዙ አውሮፕላኖች እስኪጫኑ በማቀዝቀዣ ክፍሎች ውስጥ ማቆየት ግድ ነው :: ይህ ደግሞ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታን ለመጠቀም ከማስገደዱም ሌላ በኬንያ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ክፍያ ውድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በኢንዱስትሪው ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ ማስከተሉ ነው የሚጠቀሰው :: በተለይም ምርቶችን ወደ ውጭ የመላኩ ሂደቱ ዕለት በዕለት ሳያቋርጥ የሚከናውን ሲሆን ወጭውም የዛኑ ያህል ይንራል ነው የሚሉት የዘርፉ ባለሙያዎች ::ስለዚህም ሌላ መላ መዘየድ ግድ ሆኗል::ሳቢነ ኮንቶስ እዛው ኬንያ የሚገኘው የፔንታል አበባዎች አምራች ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት የስራ አመራር ሃላፊ ናቸው::እንደ ጎርጎራውያ በ 2001 ዓ.ም በኬንያ የአበባው ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዓለማቀፍ ዕውቅና ባገኘበት ዘመን ህጋዊ የወጭ ንግድ ፈቃድ አውጥተው እንቅስቃሴ ከጀመሩ ድርጅቶች ግንባር ቀደሙ ነው::

" አሁን ላይ አማራጭ የጸሃይ ኃይል ሶላር ኢነርጂን መጠቀም ጀምረናል :: አካባቢያችን በሞቃታማ አካባቢ መገኘቱም አማራጭ ቴክኖሎጂውን እንድንጠቀም ረድቶናል ::ከወንዞች ከምንጠቀው የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ የቤት ጣሪያዎች ላይ የጸሃይ ሃይል መሰብሰቢያ ዝርግ ሳህኖችን በመግጠም ለአበባ ምርቶቹ ጥራት የምንፈልገውን ሙቀት እና ቅዝቃዜ ወጭን በሚቆጥብ መንገድ ማግኘት ችለናል:: "

ሳቢነ ኮንቶስ ቀደም ባሉት ዓመታት የአበባ ምርት ኢንዱስትሪው እንደ አየር ውሃ አፈር እና ሌሎችም የተፈጥሮ ሃብቶች ላይ ያስከትል የነበረው ጉዳት እና የአካባቢ መራቆት ችግር አሁን ላይ መሻሻል እያሳየ መሄዱን ነው የሚናገሩት::

Kenia Rosen Fair Trade Rosen Blumenfarm Arbeiter
ምስል DW

" ኢንዱስትሪው አሁን የደረሰበትን አጠቃላይ ለውጥ እና የእድገት ደረጃ ከ 20 ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር ማነጻጸር አይቻልም::የዚህም አንዱ ዓብይ ምክንያቱ በተለይም በአውሮጳ ያሉ ዋና ደንበኞቻችን የአበባ ምርቶቻችንን በምን ዓይነት ሁኔታ እንደምናመርት የማወቅ ፍላጎታቸው እየጨመረ መምጣቱ ነው:: ይህም በተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም እና እንክብካቤ ላይ ደረጃቸውን የጠበቁና የተሻሻሉ አሰራሮችን እንድንከተል እንዲሁም የኬሚካል የውሃ እና የኢነርጂ አጠቃቀማችንን እንድናሻሽል ትልቅ አቅም እና ጉልበት ፈጥሮልናል:: "

የኬንያ የአበባ አምራቾች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ምክርቤት ሃላፊ ክሌመንት ቱልዚ 80 በመቶ የሚሆነውን የኬንያን የእርሻ መሬት የሚያለሙ ከ 120 የሚልቁ የአገሪቱ አበባ አምራች ድርጅቶች የመሰረቱት ማህበር መሪ ናቸው:: በምክርቤቱ ዋና ተቆጣጣሪ ኦዲተር በርናርድ ንያምቤጋ የሚመራው ቡድን በበኩሉ የተፈጥሮ እና አካባቢ ጥበቃን ለማጠናከር የማህበሩ አባላት የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋግድ ደንቦችን ማክበራቸውን እና ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶች ለገበያ ማቅረባቸውን በየጊዜው ምርመራ እና ክትትል ያካሂዳል:: በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪው ምክንያት ብክለት ከደረሰባቸው የወንዝ ውሃዎች ከ 60 በመቶ በላይ የሚሆነውን በማከም እና መልሶ ሪሳይክል በማድረግ ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉም ተነግሯል::

" ከፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ጋር በተያያዘ ከአሁን ቀደም አያሌ ስሞታዎች ይቀርቡ ነበር::አሁን ግን ሁኔታዎች ተቀይረዋል::ምናልባት በአመት ውስጥ አንድ ወይም ሁለት የአበባ እርሻ ድርጅት ባለንብረቶች የህግ ጥሰት ፈጽመው ቢገኙ ነው:: የውሃዎችን የጥራት ደረጃ ለመጠበቅም እንዲረዳ አዳዲስ የማጣሪያ መሳሪያዎችን መግጠም ይኖርባቸዋል " ብለዋል ንያምቤጋ::

በኬንያ የቢልዮኖች ዶላር ኢንዱስትሪ የሆነው ግዙፉ የአበባ ምርት ልማት ለገበያ ከመቅረቡ አስቀድሞ አያሌ ፈታኝ ችግሮች እንደሚገጥሙትም ነው የማህበሩ አባላት የሚገልጹት ::ሳቢነ ኮንቶስ የፔንታል አበባዎች አምራች ድርጅት ሃላፊ የፈንገስ በሽታዎች ልክ ጸረ ሰብል ተባዮች እንደሚያደርሱት ጥፋት ሁሉ ለአበባ ምርቶችም እጅግ አደገኛ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ:: እናም ያለ ጸረ ተባይ መድሃኒቶች አበባዎች ህልውና አይኖራቸውም ነው የሚሉት::የምርት ክፍል ሃላፊው ፒተር ኦቴኖ ግን ከዚህ በተቃራኒው የኬሚካል መድሃኒቶች ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ስለሚያመዝን አማራጭ ዘዴዎችን እንጠቀማለን ብለዋል::

Schnittblumen aus Kenia zu Hungerlöhnen geerntet
ምስል picture-alliance/dpa/DB U. Koltermann

"እያንዳንዱ የሚረጭ ኬሚካል በአበቦች ላይም ይሁን በአካባቢ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጉዳት ያስከትላል:: በመሆኑም በተቻለ መጠን በተወሰነ መጠን ነው ለመጠቀም የምንሞክረው::ከዚህ ውጭ ጠቃሚ ነፍሳትን እንዲሁም ሌሎች ተባዮችን እና ተሃዋስያንን በሽታዎችን ለመከላከል እና በአበባው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ነፍሳትን ለመዋጋት እንጠቀማለን ::"

በአሁኑ ወቅት የውሃ ሃብት ብክነትን ለመቀነስ በወንዞች እና ሃይቆች ተፋሰስ ዙሪያ የመስኖ ልማት ዘዴዎችን በማጠናከር ቀድሞ ከነበረው የውሃ አጠቃቀም በግማሽ በመቀነስ ውጤታማ ተግባር መከናወኑን ክሌመንት ቱሌይዝ ያስረዳሉ:: ከዚህ ውጭ የዝናብ ውሃን በማቆር በአማራጭነት ጥቅም ላይ የማዋል ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው በፊት ከወንዝ በሞተር እየተሳበለ እርሻው ይውል የነበረውን የውሃ መጠን እንዲቀንስ ረድቷል ሲሉም ቱሌይዝ ያስረዳሉ::

ከናይሮቢ በቅርብ ርቀት የሚገኘው የናይቫሻ ሃይቅ የትራንስፖርት ወጪን መቀነሱ ምርትን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለገበያ ለማድረስ ምቹ መሆኑ ለአበባ እርሻ ተስማሚ የአየር ጸባይ መታደሉና ከፍተኛ የውሃ ሃብት ክምችቱ የአልሚዎችን ትኩረት በእጅጉ ስቧል:: ይሁን እንጂ ለእርሻዎቹ ጥቅም ላይ የሚውሉት የኬሚካል ማዳበሪያዎች እና መርዛማ ኬሚካሎች በአሳዎች ውሃውን በሚጠቀሙ በሺዎች የሚቆጠሩ ጉማሬዎች እና ሌሎችም እንሣቶች ላይ እንዲሁም በማህበረሰቡ ጤናና በተፈጥሮ ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት እየጨመረ መምጣቱን በመግለጽ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች በተደጋጋሚ ከመውቀስ አልተቆጠቡም :: የኬንያ የአካባቢ እና ተፈጥሮ ጥበቃ ድርጅት ተጠሪ ሊዲያ ቢሪ ግን መደበኛ አምራች ተቋማት በተፈጥሮ ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት መቀነሱን ነው የሚናገሩት::

" አብዛኛዎቹ የአበባ አምራች ድርጅቶች በናይቫሻ ሃይቅ ዙሪያ ነው የልማት ተግባር የሚያከናውኑት:: ይህም በመሆኑ በርካታ የተፈጥሮ ጥበቃ ባለሙያዎች በሥነምህዳሩ ላይ የሚደርሰውን አስከፊ ጉዳት ለመቀነስ ጥረት እንዲደረግ ከፍተኛ ግፊት ያደርጋሉ:: በኛ በኩል የውሃ አካላት በኬሚካሎች እንዳይበከሉ ጠንካራ ክትትል እያደረግን ነው:: ይልቁንም ማህበረሰቡ የሚከተለው የተፈጥሯዊ ቆሻሻዎች አወጋገድ ሥር ዓቱ በተፈጥሮ እና አካባቢ ብክለት ላይ የጎላ ሚና እንዳለው ነው መገንዘብ የቻልነው:: "ኬንያ በአበባው ምርት ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ ገቢና ጥቅም የምታገኝ አገር ትሁን እንጂ በተፈጥሮ ሃብት እና በአካባቢ ምህዳሩ ላይ እያስከተለ ያለው ችግርም እንዲሁ ዛሬ ላይ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱ ነው የሚነገረው:: በዛው በኬንያ የሚገኙ አነስተኛ አምራች ገበሬዎች እና የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያው ጃኮብ ክሬሚን አሁንም የአበባ ምርት ልማት ኢንዱስትሪ ማህበሩም ይሁን ህግ አስከባሪው ዘርፍ በማህበረሰቡ ጤና እና በእንሣት የመኖር ዋስትና ላይ አደጋ የጋረጠውን ችግር ከመቅረፍ ባሻገር በተፈጥሮ ምህዳሩም ላይ ተጨማሪ ጉዳት ሳይደርስ የልማት እንቅስቃሴው ሥርዓት ባለው መልኩ እንዲከናወን ነው የሚጠይቁት:: በአበባ እርሻ ልማት ውስጥ ተቀጥረው አገልግሎት ለሚሰጡ ሰራተኞች ደህንነትና ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ ለመጣው የተፈጥሮ እና አካባቢ ጥበቃ ጉዳይም ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ማሳሰባቸው አልቀረም::

 

እንዳልካቸው ፈቃደ

ልደት አበበ