1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግዙፍ የባቡር ሃዲድ ፕሮዤ በአፍሪቃ

ረቡዕ፣ መስከረም 26 2003

በዓለምአቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነው የጀርመን የብረታ-ብረት ኩባንያ ቱሰን-ክሩፕ ደቡብ ሱዳንን ከኡጋንዳና ከዚያም ከኬንያ የሚያገናኝ ከሰባት መቶ ኪሎሜትር በላይ ርዝመት ያለው የባቡር ሃዲድ ለመዘርጋት በማቀድና ለተግባር በመዘጋጀት ላይ ነው።

https://p.dw.com/p/PXEV
ምስል DW / Pirolic

ኩባንያው በደቡብ ሱዳን አስተዳደር ትዕዛዝ ይህን አስፈላጊ የማመለለሻ መስመር ገሃድ ለማድረግ አጥብቆ የሚጥረውን “ኒው ሱዳን ፋውንዴሺን” የተሰኘ አካል ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ሲያማክርና ሲደግፍ ቆይቷል። በፕሮዤው የአሜሪካው የቴክሣስ ኩባንያ አይር-ሎጂስቲክስ-ሊሚትድና የሩሢያው ኩባንያ ኦስ-ሜትሮስትሮይም ይሳተፋሉ። ይህ ታላቅ ፕሮዤ እንዴት ዕውን ሊሆን በቃ? እንደታሰበው ከግቡ ከደረሰስ ለአካባቢው የኤኮኖሚ ዕድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ ምን ያህል ነው?

በምዕራባዊው ጀርመን በኤሰን ተቀማጭ የሆነው የብረታ-ብረት ኩባንያ ቱሰን-ክሩፕ በዘመናዊ ቴክኒክ ሃዲድ በመዘርጋትም ጭምር ሰፊ ዕውቀት፣ ልምድና ጥራት ያለው በዓለምአቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነ ኩባንያ ነው። ኩባንያው ባለፉት ዓመታት የውጭ ንግዱን ይበልጥ እያሰፋ ሲመጣ አሁን ደግሞ በአፍሪቃ ውስጥ ቢቀር በወቅቱ ታላቁ የሆነውን የባቡር መስመር ዝርጊያ ፕሮዤ ዕውን ለማድረግ እየሰራ ነው። የባቡሩ መሥመር በከፊል ራስ ገዝ የሆነችውን የደቡብ ሱዳንን ዋና ከተማ ጁባን ከሰሜን ኡጋንዳ የሚያገናኝ ሲሆን በዚሁ በመጀመሪያው የግንቢያ ደረጃ ወደ ደቡብ ኡጋንዳም ሊስፋፋ የታሰበ ነው። በጥቅሉ 725 ኪሎሜትር ርዝመት የሚኖረው የሃዲድ መስመር ለአካባቢው ገበዮች ጥሩ ሁኔታን የሚያመቻች፤ የምርት ማስገባትንና ወደ ውጭ የመላክን ዕድልም የሚከፍት እንደሚሆን ይጠበቃል።

አፍሪቃ ውስጥ ባለፉት ዓመታት ተለቅ ያሉ መዋቅራዊ ግንባታዎች በተለይ በቻይና ሲካሄዱ ነው የቆዩት። ለነገሩ በልማት ዕርዳታ ተቀባይነት እንጂ በመዋዕለ-ነዋይ ባለቤትነት በማትታወቀው በአፍሪቃ ይህን መሰሉን ተግባር ለማከናወን የደፈረ ወይም የሚደፍር የምዕራቡን ዓለም ኩባንያ ፈልጎ ማግኘቱ ብዙ የሚያዳግት ነው። ከዚህ አንጻር የጀርመኑ ታዋቂ ኩባንያ ቱሰን-ክሩፕ በሃዲዱ ግንቢያ ለመሳተፍ መነሣቱ በብቃቱና በጥራቱ የማስደሰቱን ያህል ጥቂት ማስደነቁም አይቀርም። የሆነው ሆኖ የኩባንያው የሃዲድ ቴክኒክ ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ ሃራልድ ቦገዳይንስ ተግባሩን የሚመለከቱት ቱሰን-ክሩፕ በዓለምአቀፍ ደረጃ የያዘው መስፋፋት አንድ አካል እንደሆነ አድርገው ነው።

“ኩባንያችን ሃዲድ መሥሪያ ነገሮችን በማምረት የታወቀ ነው። ስለዚህም ማንኛውንም መዋቅራዊ ፕሮዤ ከዝግጅትና ከዕቅድ አወጣጡ አንስቶ ዕቃዎችን እስከማቅረቡና ግንቢያውን እስከመቆጣጠሩ ድረስ እናጅባለን። እና ይህም ከደቡብ ሱዳን እስከ ኡጋንዳ የታቀደው መዋቅራዊ ፕሮዤ እነዚህን የተለያዩ መስኮች በአንድ የሚጠቀልል ነው። በፕሮዤው እንድንተባበር የተጠየቅነው ከስድሥት ዓመታት ገደማ በፊት ነበር። እንግዲህ ይሄው ከዚያን ወዲህ በተግባሩ በመሳተፍ ላይ እንገኛለን”

ቀደም ሲል እንደጠቀስነው 725 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው፤ ወደፊትን በአካባቢው ከዚያ የሰፋ ግዙፍ የባቡር ሃዲድ መስመር ነው ሊዘረጋ የታቀደው። በመሥመሩ አኳያ የሚታነጹ ሕንጻዎችም ሆኑ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሳይታሰቡ የሃዲዱ መረብ ግንቢያ ብቻ በዛሬው ግምት ሶሥት ሚሊያርድ ዶላር የሚፈጅ ነው። በተለይም የክፍያ አቅም ከሌለው ከሣሃራ በስተደቡብ አካባቢ ይህ ቀላል ነገር አይደለም። ይህም ኩባንያው ምን የፊናንስ ዋስትና ይዞ ነው በፕሮዤው መሳተፉ የሚል ጥያቄን ማስነሣቱ አይቀርም። ይሁንና ገንዘቡ የሚቀርበው ሆገዳይን እንደሚሉት ከግል ዘርፍ በመሆኑ ለኩባንያቸው ብዙም አስቸጋሪ ነገር አልሆነም።

“የፊናንሱ ዋስትና ሰጪዎች እኛ ሣንሆን ወደፊት በባቡር አገልግሎቱም የሚሳተፍ አንድ የአሜሪካ የግል መዋዕለ-ነዋይ አቅራቢ ነው”

በሌላ በኩል ይህን መሰሉ ታላቅ ፕሮዤ የአካባቢውን የፖለቲካ ዕርጋታም በጣሙን ይጠይቃል። በሱዳን ደግሞ ሁኔታው በዚህ በኩል ቢቀር በቀቅቱ ተሥፋን የሚያጠናክር አይደለም። ለምሳሌ ለፊታችን ጥር የታቀደው የደቡብ ሱዳን ሕዝበ-ውሣኔና የአካባቢው ነጻነትን ማወጅ መቻል አዲስ ውዝግብን እንዳይጭር ማስጋቱና ማነጋገሩ አልቀረም። የተፈራው ከደረሰ ለባቡር መስመሩ ዕቅድም አደገኛ ሊሆን መቻሉ አንድና ሁለት የለውም። በሌላ በኩል የቱሰን-ክሩፕ የሃዲድ ቴክኒክ ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ ሃራልድ ቦገዳይን እንደሚሉት ቢቀር ገና የተወሰነ ጊዜ በሚፈጀው የዕቅድ ሂደት ወቅት አሁን በስፍራው በተግባር መሰማራቱ አስፈላጊ አይደለም። ተግባሩ ደረጃ በደረጃ የሚራመድ ነገር ነው።

“የግንቢያው ዝግጅት የተወሰነ ጊዜ ይፈጃል። መስመሩን ደግሞ በሁለት ከፍለን መመልክት አለብን። ኡጋንዳ ውስጥ ከቶሮሮ እስከ ጉሉ በቴክኒካዊ ሁኔታው ሊነዳበት የሚችል ባይሆንም የቆየ መስመር ሲኖር ሌላው ከጉሉ ወደ ጁባ የሚዘረጋው ሁለተኛው መስመር ደግሞ ሙሉ በሙሉ አዲስ የሚታነጽ ነው። ኡጋንዳ ውስጥ ላለው ከፊል መስመር የዕቅድ አወጣጡ ተግባር 12 ወራት ገደማ የሚፈጅ ይሆናል። ሌላው ክፍል ግን በመሉ አዲስ ግንቢያ በመሆኑ ሁለት ዓመት ያህል መጨረሱ አይቀርም። እና እንግዲህ ከመለካቱ፣ ከጂኦሎጂውና ከሃይድሮሎጂው ምርመራ በስተቀር አብዛኛው ተግባር የግድ በስፍራው መካሄድ የለበትም። ማለት በኡጋንዳና በደቡብ ሱዳን የግንቢያ ሠራተኞች በተግባር እስከሚሰማሩ ገና ጊዜ የሚወስድ ነገር ነው”

ቀደም ሲል የሃዲዱን ፕሮዤ ከደቡብ ሱዳንና ከኡጋንዳ ባሻገር ወደ ተጎራባቹ ሃገራት ወደ ኬንያና ወደ ኢትዮጵያ ለማራዘምም ታስቦ ነበር። ይሁንና የኬንያው ጽንሰ-ሃሣብ እንዳለ ሲቀጥል ኢትዮጵያ ግን በመሃሉ ተግባሩን ለቻይና ኩባንያዎች ሳትሰጥ እንዳልቀረች ነው የጀርመኑ ኩባንያ ተጠሪ የሚያምኑት።

“ጠቅላላውን ፕሮዤ፤ የመዋቅራዊ ግንቢያውን ጽንሰ-ሃሣብ ስንመለከት ይሄው 7,500 ኪሎሜትር ርዝመት ይኖረዋል። ተራ በተራ እየተገነባ የሚሄደውን ማለት ነው። በሞምባሣ፣ በኡጋንዳ፣ በኬንያ በኩል በግንቢያው ለመቀጠል ይታሰባል። እንደምታውቀው በዚያ ለወቅቱ ተስማሚ በሆነ ስፋት ተለውጦ መገንባት የሚኖርበት ጠባብ የቆየ የሃዲድ መስመር አለ። ከዚሁ በተጨመሪ በኬንያ-በላሙ አዲስ ወደብ ለመክፈትም የባቡር ሃዲድ ለመዘርጋት ነው የሚታሰበው። ይሄ ደግሞ በወቅቱ ጥናት እየተካሄደበትም ያለ ጉዳይ ነው። ከዚህ ሌላ ቀደም ሲል ከደቡብ ሱዳን ከጁባ ወደ ኢትዮጵያ ሃዲድ ለመዘርጋትም ሃሣብ ነበር። አሁን በመሃሉ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ከቻይና ኩባንያ ጋር በመስማማት መስመሩን ለዚሁ ሳይሰጥ አልቀረም”

በአጠቃላይ በደቡብ ሱዳን የተያዘውና ወደፊትም በአካባቢው አገሮች ሊስፋፋ የሚችለው የሃዲድ መስመር ግንኙነት ዕውን መሆን በአካባቢው የኤኮኖሚ ይዞታ ላይ ታላቅ ለውጥን ሊያስከትል የሚችል ነው።
“በደቡብ ሱዳን እየተዘዋወርክ ብትመለከት የምድር መገናኛው መረብና የባሕሩ መንገድ ለትራንስፖርት ያመች አለመሆኑን መታዘብ ትችላለህ። ስለዚህም የባቡሩ መስመር በኛ አመለካከት ለደቡቡ ክፍል የኤኮኖሚ ዕድገትን እንደሚያስከትል ጥርጥር የለውም። ይህ ደግሞ የጁባው የአካባቢ መንግሥት አስተሳሰብም ነው” እንዴት ቢባል፤

“መሥመሩ ቢዘረጋ ከውጭ ወደ ደቡብ ሱዳን ምርትን ለማስገባትም ሆነ ለወደፊት የሚታሰበውን የኢንዱስትሪ ግንቢያ ገቢር ለማድረግ ይበጃል። እንደሚታወቀው አካባቢው በነዳጅ ዘይት ሃብት የታደለ ነው። እና የዘይት ማጣሪያ (ሪፋይነሪ) በማቆም ምርቱን ወደ ውጭ፤ ማለት ወደ ኡጋንዳ፣ ኬንያና ከባሕር ማዶም ለመሸጥ ይቻላል። የባቡሩ መሥመር በአጠቃላይ ለኤኮኖሚው ዕድገት አስፈላጊ ቅድመ-ግዴታ ነው”

እርግጥ ግንቢያው እስኪያበቃ ገና የተወሰነ ጊዜ ማለፉ አይቀርም። በትክክል እንዲህ ብሎ ጊዜ መጥቀሱም በወቅቱ አስቸጋሪ ነው። በአጠቃላይ መስመሩ ከአምሥት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተሰርቶ ያበቃል ተብሎ አይታሰብም።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ