1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠለፋና ያለ ዕድሜ ጋብቻ በኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 6 2008

የዛሬ 15 ዓመት አርሲ ዉስጥ የተጠለፈችዉ የያኔዋ የ13 ዓመት ታዳጊ ከአስራ አምስት ዓመት በኋላ ፍርድን አገኘች ይላል ከአንድ ወር በፊት የወጣ አንድ ዘገባ። ጉዳዩን ሲከታተለዉ የነበረዉ የአፍሪቃ ሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት፤ ጠለፋና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ለፈፀመባት ልጅ ኢትዮጵያ 150 ዶላር ካሳ እንድትከፍል መወሰኑም ተያዪዞ ተጠቅሶአል።

https://p.dw.com/p/1IVIf
Äthiopien Mädchen beim Wasserholen
ምስል picture alliance/Ton Koene

ጠለፋና ያለ ዕድሜ ጋብቻ በኢትዮጵያ

በጠለፋ የሚፈፀም ጋብቻ ኢትዮጵያ ዉስጥ ከኖሩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አንዱ ነዉ። ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕጻናትን የትዳር ኃላፊነት ዉስጥ የማስገባትን ጎጂነት በማስረዳት የሴቶች የወጣቶች ማኅበራት ድርጊቱ እንዲቆም እያስተማሩ መሆኑ ይነገራል። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ተቋማት እንደሚሉት ጠለፋ እና አስገድዶ ጋብቻ በተለይ በአንዳንድ የገጠር ማኅበረሰብ ዉስጥ በመለመዱ ሁኔታዉን ለመቀየር አስቸጋሪና ጊዜን የሚጠይቅ ይሆናል። በዚህ ዝግጅታችን በኢትዮጵያ ጠለፋና በለጋ ዕድሜ የሚፈጸም ጋብቻን የመሳሰሉ የቆዩ ጎጂ ልምዶችን ለመቅረፍ ምን እንደሆነ ይፈትሻል።

Ethiopian Women Lawyers' Association
ምስል Ethiopian Women Lawyers' Association

የጠለፋ ጋብቻ በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት ብሎም በአንዳንድ የእስያ ሃገራት እንደሚታይ ጽሑፎች ያመለክታሉ። በኢትዮጵያ በተለይ በአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች አንድ ጎልማሳ ለትዳር የፈለጋትን ልጃገረድ ጠልፎ ጋብቻን መፈፀም ሲያስብ ፈርጠም ፈርጠም ያሉ ጓደኞቹን አሰባስቦ እንስራዋን ተሸክማ ዉኃ ለመቅዳት ወደ ወንዝ ስትወርድ አልያም ከገበያ ስትመለስ ካሰባሰባቸዉ ጓደኞቹ ሆኖ መንገድ ላይ ይጠብቅና ይተነኩላታል፤ ከዚያም እንደ አዉሬ ስርቅ አርጎ በፈረስ ጀርባ አስቀምጦ ይሰወራል። የዛሬ አስራ አምስት ዓመት ተጠለፋ ያልዉዴታዋ ጋብቻ እንድትፈጽም የተደረገችዉ የያኔዋ የ 13 ዓመት ታዳጊ ሕጻን፤ከተያዘችበት ቤት አምልጣ መዉጣት በመቻልዋ ነበር ዛሬ ከአፍሪቃ ሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት ፍትህ ያገኘችዉ። ከመገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያ መንግሥት 150 ሺህ ዶላር ካሳ እንዲከፋላት እንደተወሰነላት ሰምተናል ያሉን፤ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር ፕሬዝደንት ወ/ሮ ዝናዬ ታደሰ፤ የተጠለፈችዉ የዚህችን ልጅ ጉዳይ ማኅበራችን ቀደም ሲል ይከታተለዉም ነበር ሲሉ ገልፀዉልናል።

«ልክ ነዉ ፤ ተወሰነ የተባለዉን ነገር እስካሁን አላገኘነዉም። እኛ ጉዳዩን የሰማነዉ በሚዲያ ነዉ። መሥርያ ቤታችን በፊት የጀመረዉ ነገር ቢኖርም በአሁኑ ወቅት የስዋን ልጅ ጉዳይ እየተከታተልን አይደለንም። እኔም ብሆን ግን ይህን ማኅበር የተቀላቀልኩት በቅርቡ ነዉ፤ ታሪኩ እንዲህ ነዉ። የጠለፋ ጥቃት የተፈፀመባት ልጅ የ 13 ዓመት ልጅ ስትሆን ጉዳዩ የተከሰተዉ አርሲ ዉስጥ ነዉ። ጠለፋን ተከትሎ የሚመጣዉ ደግሞ ጋብቻና አስገድዶ መድፈር ነዉ። እነዚሁ ሁሉ ነገሮች ተፈፅመዉባታል። ያን ግንኙነት እንዲቀጥል ስላልፈለገች ከዛ በኋላ በማምለጥዋ ማለት እንደሚታወቀዉ ብዙዎች ከጠለፋ በኋላ በትዳር ተስማምተዉ ይቀጥላሉ፤ እሷ ግን ይህን ነገር በማሳወቅዋ፤ የጠለፋት ሰዉና ግብራበሮቹ በወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዉ ነበር። ወንጀሉ በመጀመርያ ብይን ተሰጥቶት ነበር፤ በኋላ ግን ሰዎቹ በነጻ ተለቀቁ። እዚህ መፍትሄ ማግኘት አልተቻለም ነበር። ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ነገሩን የአፍሪቃ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዲያዉቀዉ ተደርጎ ጉዳዩ እዝያ ሲታይ ቆየ። የኢትዮጵያ መንግሥትም ስምምነት አድርጎ ካሳ እንደሚገባና የነበረዉ የፍትህ ሥርዓት ስህተት እንደተፈፀመ፤ ሰዎቹም ላይ የዲሲፕሊን ርምጃ ዝግጁ እንደሆነ እንደዚህ በመሳሰሉ ነገሮች ላይ ጥሩ ርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቶ ነበረ። በኋላ ግን እንዴት እንደሆነ አላዉቅም ተቋረጠ። በኛ በኩል ግን በኢትዮጵያ የሕግ የሴቶች ማኅበር ቀደም ሲል ጉዳዩ አካባቢዉ ላይ ይታይ በነበረ ጊዜ ይከታተለዉ ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ልጅቱም ከአገር ስለወጣች እንድንወክላት ፈቃደኛም ስላልነበረች፤ ከጎርጎሳዉያኑ 2011 ዓ.ም በኋላ ጉዳዩን ተከታትለነዉ አናዉቅም። አሁን ግን በሚዲያ እንደተነገረዉ የአፍሪቃ የሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት የኢትዮጵያ መንግሥት 150ሺህ ዶላር ካሳ እንዲከፍላት ዉሳኔ መሰጠቱን በሚዲያ ሰምተናል»

Äthiopien Mädchen
ምስል Reuters/T. Negeri

በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች ጠለፋን ከፈጸሙ በኋላ ጠላፊው ወደ ተጠላፊዋ ወላጆች ዘንድ ሽማግሌዎችን መርጦ በመላክ ሽማግሌዎቹ እንዲያስታርቁ ለተጠላፊዋ ቤተሰቦች ካሳ ማለትም እንደ ገንዘብ እና ጥቂት ከብቶችን እንዲወስዱ በማድረግ ጋብቻው ሕጋዊ እንዲሆን ጥረት ያደርጋሉ። አንዳንዴም የሴትዋ ቤተሰቦች ከወንዱ ማለት ከትዳር ፈላጊዉ ጋር በመስማማት ጠለፋዉ እንደሚፈጸም ይነገራል። የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዝናዬ በመቀጠል እንደተናገሩት፤

« ይህ ነዉ ፤ ጠለፋዉ ከሆነ በኋላ ነዉ ብዜ ጊዜ የቤተሰብ ስምምነት የሚመጣዉ። ጠለፋዉ ከተካሄደ በኋላ ለልጅቷ ቤተሰቦች አማላጅ ሽማግሌ ይላካል። ቤተሰቦችም ምርጫ የላቸዉም ልጅቱ አንዴ ተጠልፋለች፤ ተደፍራለች ስለዚህ ያ ግንኙነት ቢቀጥል ነዉ የሚሻለዉ፤ ማለያየትም የሚያመጣዉ ፋይዳ ከእንግዲህ አይኖርም። ከዝያ ያ የጠለፋ ድርጊት እንደጋብቻ ሆኖ ይወሳዳል። ስለዚህ ጠለፋዉ ከተፈፀመ በኃላ በቀጣይ ሽማግሌ በመሃል ስለሚኖር ብዜ ጊዜ በስምምነት ነዉ የሚቀጥለዉ። ግን እዚህ ላይ ጥፋት የሚያደርገዉ ነገር የሚጠለፉት ሴቶች እድሜያቸዉ በፍላጎት ላይ የተወሰነ ዉሳኔ ለመስጠት በሚችሉበት ዕድሜ ላይ አይደለም የሚሆኑት። ስለዚህ ልጆቹ ትዳሩን ፈለጉት አልፈለጉት፤ ይሄንን ነገር ወላጆቻቸዉ እስከተስማሙ ጊዜ ድረስ ይገፉበታል። ነገር ግን ልጆቹ ትዳር ዉስጥ ያለ ፍላጎታቸዉ ያለ ዕድሜያቸዉ ሲገቡ ተያያዥ የሆኑ ብዙ አሉታዊ ዉጤቶች ይመጣሉ ማለት ነዉ። ይህ ማለት ትምህርታቸዉን መከታተል አይችሉም፤ ለጤና ችግር ይጋለጣሉ፤ ያለ ዕድሜያቸዉ ያረግዛሉ፤ ይወልዳሉ፤ እና ደግሞ በማይፈልጉት ሕይወት ዉስጥ ለመኖር ይገደዳሉ።»

Ethiopian Women Lawyers' Association Logo

በሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ቢሮ ያገለገሉት አቶ ደረጀ ታምራት በግዳጅ የሚፈፀም ጋብቻ ላይ በተለይ በአማራና በኦሮምያ ክልል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራን ለረጅም ጊዜ እንደሠሩ ገልጸዉልናል።

« አስገድዶ ጋብቻ ማለት ጎጂ ልማድ የሚባሉት በሦስት ይከፈላሉ። ያለ ዕድሜ ጋብቻ፤ አስገድዶ መድፈርና፤ ጠለፋ የሚባሉት ሲሆኑ፤ አስገድዶ ጋብቻን ስንመለከት ብዙ ጊዜ ገጠር አካባቢ ላይ ነዉ የሚታየዉ። እኔ በሰራሁት በአማራ ክልል ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ላይ ቦታዉ ላይ ስንገኝ፤ ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዳለዉ ይታያል ግን ተማሪዎቹ ራሳቸዉ ዕድምያቸዉ 15 ዓመት የሆኑ ሴቶች 21 ዓመታችን ነዉ ብለዉ ትዳር የመያዝ ነገር ይታያል። ትምህርት አንማርም የማለት ነገር ይመጣል። ከዚህ በተጨማሪ በጣም አሳሳቢ የሆነዉ ነገር ጠለፋ በተከናወነበት ሰዓት ላይ የአገር ሽማግሌዎች የኃይማኖት መሪዎች ናቸዉ ወደ ሴትዋ ቤተሰቦች የሚላኩትና ነገሩን በሕግ ለመከላከል እጅግ አስቸጋሪ ነዉ የሆነዉ። ምክንያቱም እርስ በርስ የተያያዙና የሚተዋወቁ በመሆናቸዉ ነዉ። ሌላዉ በአስገድዶ ጋብቻ ላይ ስንመለከት ለምሳሌ በኦሮምያ ክልል ሰዎች ጨፊ ሳር ወይም አረንጓዴ ቅጠል በመያዝ ወደ ሴትዋ ቤተሰቦች በመሄድ ልጃችሁን ለልጃችን አለበለዝያ ሰብሉ ይደርቃል የተዘራዉም አይለመልምም ምንም ዓይነት ምርት የለም የሚል የተዛባ ግንዛቤ እነሱ ላይ በመጫን አስገድዶ ጋብቻ ይከናወናል ማለት ነዉ»

Äthiopien Mädchen beim Wasserholen
ምስል Ethiopian Women Lawyers' Association

ይህን ለዘመናት የዘለቀ ጎጂ ልምድ ለመቅረፍ የተለያየ ትምህርትና ስልጠና ብንሰጥም ቅሉ ቶሎ ይቀየራል፤ ማኅበረሰቡም ግንዛቤ አግኝቶ በሥራ ላይ ያዉለዋል ተብሎ አይጠበቅም ሲሉ አቶ ደረጀ ታምራት በመቀጠል አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር ፕሬዝደንት ወ/ሮ ዝናዬ ታደሰ በበኩላቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በግዳጅ የሚፈፀም ጋብቻ ማለትም ጠለፋ አልያም ያለ ዕድሜ ጋብቻ አሁንም ይታያል እንድያም ሆኖ ብዙ ቀንሶአል ሲሉ ተናግረዋል። ቃለ ምልልስ የሰጡንን በዶቼ ቬለ ስም እያመሰገንን ሙሉ መሰናዶዉን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ