1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠንቃቃ የውሃ አስተዳደር ለዕድገት ያለው ትርጓሜ

ሐሙስ፣ መጋቢት 23 1996

ባለፈው ሣምንት የተከበረውን ዓለምአቀፍ የውሃ መታሰቢያ ቀን መነሻ በማድረግ፤ የአውሮጳው ኅብረት ኣባል-ሀገሮች በሚደረጁት ሀገራት ውስጥ የንፁሕ ውሃ አቅርቦት ለሚነቃቃበት መርሐግብር በ፭፻ ሚሊዮን ኦይሮ የሚሸፈን ግምጃ-ቤት እንዲመሠረት ወስነዋል። ከዚሁ የውሃ ልማት ገንዘብ ፪፻፶ ሚሊዮኑ አሁኑኑ ዝግጁ እንደሚሆን ነው የተገለፀው። የተባ መ ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን በበኩላቸው ስለ ውሃ ልማት ጉዳይ ለድርጅቱ ማሻሻያ ሐሳብ የሚያቀርብ አንድ አማካሪ ኮሚቴ ሰይ

https://p.dw.com/p/E0fr

�ዋል። የውሃ ጠንቃቃ ኣያያዝና ቀልጣፋ አስተዳደር ለብሔራዊው ልማት ከፍተኛ ትርጓሜ ነው ያለው።

እንደሚታወሰው፣ በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ የሚገኙት የአሥሩ አፍሪቃውያት ሀገሮች ልዑካን ከቅርብ ጊዜ በፊት በናይሮቢ/ኬንያ ተሰብስበው፣ ስለ አባይ ውሃዎች ክፍፍል አዲስ ስምምነት የሚኖርበትን ሁኔታ አውስተውት ነበር። አዲሱ ስምምነት ተሳክቶ ከፀደቀ፣ እጎአ በ፲፱፻፳፱ እና ፲፱፻፶፱ በተደረሱት አለቅጥ ያጋደሉ ስምምነቶች ቦታ የሚተካ ይሆናል። ዛሬ አፍሪቃውያን ባለፈው ዘመን ለተደረገው ትውቂያ አይሰጡም፥ አሁን ፍትሕን ነው የሚሹት። ይኸው ፍትሕ በጋራ ጠቀሜታ ላይ የተመሠረተውን ርትአዊ የውሃ ክፍፍል የሚመለከት መሆን አለበት። በ፲፱፻፳፱ (እጎአ) ብሪታንያ በሱዳን ስም ከግብጽ ጋር የደረሰችው ያጋደለ ስምምነት በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ ያሉት ሀገሮች የግብጽንና የሱዳንን ፈቃድ ሳያገኙ ወደ ሁለቱ ሀገሮች የሚፈሰውን ውሃ ይዘት የሚቀይር ርምጃ እንዳይወስዱ የሚያግድ ነው። ያው አጋዳይ ስምምነት ከ፴ ዓመታት በኋላ፥ እጎአ በ፲፱፻፶፱፥ ቢከለስም፣ አሁንም ለግብጽና ለሱዳን እንዳዳላ ነው የሚገኘው።

የአባይ ተፋሰስ ሀገሮች አበክረው እንደሚያስገነዝቡት፣ አዲሱ ስምምነት በዚያው አካባቢ ድህነትንና ረሃብን ለመግታት፣ ፫፻ ሚሊዮን የሚደርሱትን ያካባቢውን ነዋሪዎች የኑሮ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚረዳ ይሆናል። ይህንኑ በመመልከት ነው በዚያው የአባይ ተፋሰስ አካባቢ አንዳንድ ሀገሮች ልማታቸውን ለማነቃቃት አሁን ፕሮዤዎችን ለመዘርጋት የተነሳሱት። ለምሳሌ ኬንያ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መድባ፣ ሐይቀ-ቪክቶሪያ አጠገብ አንድ የውሃ አያያዝ ፕሮዤ መዘርጋት ጀምራለች። ይኸው ፕሮዤ በአካባቢው የግብርናውን እንቅስቃሴ ለማሻሻል እንዲያስችል የታሰበ ነው። የኬንያ ጎረቤት ታንዛኒያም ወደ ፴ ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ውዒሎተንዋይ መድባ፣ በስተሰሜን በኩል ረሃብ ለሚያጠቃው አካባቢ የውሃውን አቅርቦት ለማዳረስ የሚያስችል ፕሮዤ ዘርግታለች። ታንዛኒያ የምታቀርበው የአንክሮው ጥያቄ፥ ረሃብ የሚፈራረቅበት ቦታ ነዋሪዎች አጠገባቸው አባይ እያለ፣ ውሃ ፍለጋ ከ፳፭ ኪሎሜትር የሚበልጥ ርቀት ሲኳትኑ እንዲኖሩ ቢገደዱ ትክክል--ፍትሐዊ ነውን? ይላል። ታዛቢዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ ባለፉት ዓመታት በተካሄዱት ውይይቶች ላይ ቁጣዋን ስታገነፍል የነበረችው ግብጽ አሁን አቋሟን ለማለስለስ ዝግጁ የሆነች ነው የሚመስለው።
በመጭው ግንቦት በካምፓላ/ኡጋንዳ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው፣ በተፋሰስ ሀገራቱ መካከል
የአባይ ውሃዎችን ክፍፍል የሚመለከተው ቀጣዩ የሚኒስትሮች ውይይት፣ በውሉ ዝርዝር ላይ ስምምነትን የሚያስገኝ እንደሚሆን ነው ተሥፋ የሚደረገው።

የልማት ጠበብት እንደሚያስገነዝቡት፣ የውሃ ድልድልና አስተዳደር በመጭዎቹ ዓመታት አፍሪቃ ውስጥ የጉዞውና የቱሪዝሙ እንዱስትሪ ልማት እንዲነቃቃ በሚደረግበት ርምጃ ረገድ ዓቢይ ሚና የሚኖረው ሆኖ ነው የሚታየው። የተባ መ ልዩ ቅርጫፍ የሆነው የዓለም ቱሪዝም ድርጅት በሚያቀርበው ግምት መሠረት፣ እጎአ በ፪ሺ፳--በሚቀጥሉት ፲፭ ዓመታት ውስጥ ማለት ነው--አፍሪቃን የሚገበኙት የውጭ ቱሪስቶች አሃዝ በ፫ እጅ ጨምሮ ፸፯ ሚሊዮን እንደሚደርስ ነው የሚጠበቀው። ይኸው ግብ እውን ሊሆን የሚበቃው ትክክለኞቹ ቅድመ-ሁኔታዎች ሲሳኩ ብቻ ነው፥ ከእነዚሁ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል የውሃው አቅርቦት አንዱና ዋነኛው መሆኑ ነው። የዘንድሮው ቱሪዝም ማስተዋወቂያ ትርኢት በርሊን ውስጥ በተካሄደበት ወቅት እንደተገለፀው፣ ወደ አፍሪቃ ከሚደረገው የቱሪስቶች ጉዞ ፵ በመቶውን የሚስበው የአህጉሩ ሰሜን በንጽጽር ጥሩ የውሃ አቅርቦት ነው ያለው። ግን ወደ አህጉሩ ከሚዘልቀው የቱሪስቶች ጉዞ አንድ-ሦሥተኛውን የሚ,ያማልለው ደቡባዊው የአፍሪቃ ከፊል ያለው የውሃ አቅርቦቱ ይዘት በቂ አይደለም። ከአህጉሩ ጎብኝዎች ፴ በመቶውን እንደሚስብ የሚጠበቀው ምሥራቃዊው ከፊልም ያለው የውሃው አቅርቦት የተሻለ አይደለም። ገና ጉልህ የቱርዝም መስሕብነት በሌለው በአፍሪቃውም ምዕራብ የውሃው አቅርቦት በጣም የተጓለ ነው። በተባ መ የተፈጥሮ ጥበቃ ድርጅት መግለጫ መሠረት፣ የአፍሪቃው አህጉር ከጠቅላላው የዓለም ንፁሕ ውሃ አቅርቦት የሚይዘው ድርሻ ፱ በመቶ ያህል ብቻ ነው።

አፍሪቃ ውስጥ የንፁሕ ውሃው ሐብት ያለውም ስርጭት አለቅጥ የተዛነፈ ነው፥ በዝናም አጣጣሉ ይዘት ረገድ ምዕራባዊውና ማዕከላዊው የአፍሪቃ ከፊል ከሰሜን አፍሪቃ፣ ከአፍሪቃው ቀንድና ከደቡባዊው አካባቢ የተሻለ ዕድል ነው ያለው። አፍሪቃ ውስጥ እጅግ እርጥብ ሀገር የምትሰኘው ዴሞክራታዊት ሬፑብሊክ ኮንጎ፣ በኣማካይ አሃዝ ከአህጉሩ ዓመታዊ ታዳሽ የውሃ ሐብት ወደ ፳፭ በመቶ የሚጠጋውን ከፊል ነው የምትይዘው። በተቃራኒው ደግሞ፣ እጅግ ደረቅ ሀገር የምትባለው ሞሪታንያ ከአፍሪቃው ጠቅላላ ዓመታዊ ታዳሽ የውሃ ምንጭ 0.01 በመቶውን ብቻ ነው የምታገኘው።

የተባ መ የተፈጥሮ ጥበቃ መርሐግብር ድርጅት የቱሪዝም ጉዳይ ክፍል እንደሚያስገነዝበው፣ ባሁኑ ጊዜ ከ፪፻ ሚሊዮን የሚበልጡ አፍሪቃውያን ንፁሕ ውሃ በሚቸግራቸው ወይም ብርቅ በሚሆንባቸው ሀገሮች ውስጥ ነው የሚኖሩት። ይኸው አሃዝ በሚቀጥሉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ሕዝብ እየበዛ ሲሄድ ወደ ፯፻ ሚሊዮን የሚወጣጣ እንደሚሆን ነው የሚታሰበው።

ከሃምሳ ዓመታት በፊት፣ እያንዳንዱ አፍሪቃዊ ይዳረስ የነበረው ውሃ ከዛሬው ድርሻ በአራት እጅ የላቀ እንደነበር ይታወቃል። የዓለሙ ድርጅት የተፈጥሮ ጥበቃ መርሐግብር ክፍል እንደሚለው፣ በዛሬው ጊዜ በተለይ አፍሪቃ ውስጥ ለሰብልና ለከብት፣ ለእንዱስትሪው ዘርፍና ለከተሞች ንጽሕና መጠበቂያ፣ በያለበት ከባድ የውሃ እጥረት ነው ያለው። ብዙ አፍሪቃውያን መንግሥታት በየጊዜው እየጨመረ በሚሄደው በንፁሕ ውሃ ፍላጎትና ንጽሕና በሌለው፣ በመንማናው የውሃ አቅርቦት የሚፋጠጡበት ሁኔታ በብሔራዊ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም-አቀፍ ደረጃም ነው መፍትሔውን ማግኘት ያለበት። በመንደርና በብሔራዊ ደረጃ ለውሃ ልማት የሚወሰደው ርምጃ፣ የውሃው አቅርቦት ብቻ ሳይሆን የውሃው አያያዝና አስተዳደርም የሚሻሻልበትን መርሐግብር የሚመለከት መሆን አለበት።

የተባ መ የተፈጥሮ ጥበቃ ድርጅት እንደሚለው፣ የቱሪዝም ዕድገት በተፈጥሮ ሐብቶች ላይ ግፊት ይፈጥራል። ስለዚህም፣ የኃላፊነት ስሜት የተመላበት የውሃ አጠቃቀም ፀባይና መርሕ እጅግ አስፈላጊ ነው የሚሆነው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው አፍሪቃ ውስጥ ቱሪዝም ዘላቂ የዕድገት እድል ሊኖረው የሚችለው።

ሰሞኑን ከአዲስ አበባ እንደተመለከተው፣ በድርቅና በኃይል ምንጭ እጥረት አንፃር ትግሉን ለማጠናከር የምትሻው ኢትዮጵያ፣ በአባይና በሌሎችም ወንዞች ላይ የማኅቶታዊ ኃይል ግድቦችን ለመገንባትና የመስኖ ፕሮዤዎችን ለመዘርጋት ታስባለች። ዜናምንጮች እንደዘገቡት፣ በአባይ ውሃ አያያዝ ረገድ ከግብጽ ጋር በተደረገው ንግግር መሠረት ነው አባይ ላይ አንድ ግድብ ለመገንባት ስለሚቻልበት ሁኔታ መገምገሚያው ጥናት የሚንቀሳቀሰው። እንደሚታወቀው፣ ጥቁር አባይ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ሱዳን ከደረሰ በኋላ ከነጭ አባይ ጋር ተቀላቅሎ ወደግብጽ ነው የሚፈሰው።

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም ቢሆን በልይዩ ወንዞች ላይ የተተከሉ ኣያሌ የውሃ ማኅቶታዊ ኃይል ግድቦች አሉ፤ በዚህ ረገድ አሁን በቅርቡ ተገንብቶ የተከናወነው፣ በዓይነቱ እጅግ ዘመናይ የሆነው የግልገል ግቤ ግድብ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው የሚሆነው። አሁን የሚንቀሳቀሰው መገምገሚያ ጥናት ሀገሪቱ ለኤኮኖሚያዊው ዕድገት ከወንዞቿ የበለጠ ጠቀሜታ ለምታገኝበት ግብ መጀመሪያው እርከን ሆኖ ነው የሚታየው። የኢትዮጵያ የውሃ ልማት መሥሪያቤት እንደሚለው፣ ጥናቱ የተከዜን፣ የባሮ-አኮቦን እና የአንገር-ደዴሳን አካባቢዎችም ነው የሚመለከተው። የውሃ ማኅቶታዊ ኃይል ግድቦቹ ግንባታ ለእንዱስትሪዎችም የኃይል ምንጭ እንዲሆን ነው የታቀደው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለፕሮዤ ጥናቱ ማራመጃ ከአፍሪቃው ልማት ባንክ እና ከሌሎችም ተቋማት የፊናንስ ርዳታ በመሻት ላይ መሆኑ ተመልክቷል። ከዓመታት ወዲህ እጅግ ከባድ ሆኖ ከተገኘው የድርቅ አደጋ አሁን በማንሰራራት ላይ ያለችው ኢትዮጵያ፣ በአባይና በሌሎቹም ወንዞች ውሃ በመጠቀም፣ ወደ ፸ ሚሊዮን ለሚጠጋው ሕዝቧ የምግቡን ምርት ለማበርከት እንደምትበቃ ከፍተኛ ተሥፋ ነው የሚደረገው።