1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠንካራ ተማሪዎች የተገኙበት የባሕር ዳሩ ማዕከል

ሐሙስ፣ ጥር 25 2015

የ2014 ዓ.ም ፈተና ቦታ አዲስ መሆኑ የተወሰነ መደናገጥ ቢፈጥርም ተማሪዎቹ በሰላም ፈተናቸውን መውሰዳቸውንም አመልክተዋል፡፡ “የእኛ ተማሪዎች ዘንድሮ ፈተና የወሰዱት ዩኒቨርሲቲ ነው ተፈተኑት፣ ተቀላቅለው አዳራሽላይ ስለነበር የተፈተኑት ትንሽ መደናገጥ ነበር፣ ግን ፈታኞቹና የፀጥታ አካላት ተንከባክበዋቸው ተረጋግተው በሰላም ተፈትነዋል፡፡”

https://p.dw.com/p/4N1sO
Äthiopien | Bahir Dar STEM-Inkubationszentrum
ምስል Alemenew Mekonne/DW

የባህር ዳር ሰቴም ኢንኩቤሽን ሴንተር

በ2014 ዓ.ም የ12ና ክፍልን አስፈትነው በአገር አቀፍ ደረጃ ሁሉንም ተማሪዎች ካሳለፉ 7 ትምህርት ቤቶች መካከል የባሕር ዳር ስቴም ኢንኩቤሽን ሴንተር (STEM- Science, Technology, Engineering and Mathematics) አንዱ ነው፣ ትምህርት ቤቱ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እየታገዘ ነው ሥራውን የሚያከናወነው፣ ዘንድሮ ያስፈተናቸው 43 ተማሪዎች ሁሉም ማለፋቸውን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፣ ተማሪዎች በበኩላቸው ብቃት ባላቸው የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ በተሟላ የቤተ ሙከራ እየታገዙ እንደተማሩ አስረድተዋል፡፡
የባሕር ዳር ስቴም ኢንኩቤሽን ሴንተር የተመሰረተው በፈረንጆች አቆጣጠር በ2012 ማርክ ጌልፋንድ በተባለ ግለሰብ ነው፣ ከዚያም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኃላፊነቱን ወስዶ ማስቀጠሉን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ዶ/ር ተስፋ ተገኝ ገልፀዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ የተቋቋመበት ዓላማ ተማሪዎች ሂሳብን ጨምሮ በሳይንስ ትምህርቶች ብቁ ሆነው እንዲወጡ ነውም ብለዋል፡፡ 7ኛና 8ኛ ክፍል አጠቃላይ ውቴት 85 እና ከዚያ በላይ ያላቸው ተማሪዎች ከተፈተኑ በኋላ የሚያልፉ 50 ተማሪዎችን በየዓመቱ እየተቀበለ ትምህርት ቤቱ በዩኒቨርሲቲ መምህራን እየታገዘ እስከ 12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ድረስ እንደሚያስተምር ተናግረዋል፡፡
የ2014 ዓ.ም ፈተና ቦታ አዲስ መሆኑ የተወሰነ መደናገጥ ቢፈጥርም ተማሪዎቹ በሰላም ፈተናቸውን መውሰዳቸውንም አመልክተዋል፡፡ “የእኛ ተማሪዎች ዘንድሮ ፈተና የወሰዱት ዩኒቨርሲቲ ነው ተፈተኑት፣ ተቀላቅለው አዳራሽላይ ስለነበር የተፈተኑት ትንሽ መደናገጥ ነበር፣ ግን ፈታኞቹና የፀጥታ አካላት ተንከባክበዋቸው ተረጋግተው በሰላም ተፈትነዋል፡፡”
ትምህርት ቤቱ ሚጠበቀው ውጤት አሁን ከተመዘገበው የተሻለ የነበረ ቢሆንም ከፍተኛው ውጤት 621 መሆኑን ገልጠዋል፤ ተፈታኞቹ በሙሉ ያለፉ ቢሆንም በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ከ600 በላይ ያስመዘገቡ ተማሪዎች ካለፉት ዓመታት ሲነፃፀር ያነሰ መሆኑን ም አብራርተዋል፡፡
“የምንጠብቀው ውጤት ትልቅ ነበር የምንጠብቀውን ያክል አላገኘንም፣ የተሸለ ቢሆንም ትልቁ ውጤት 621 ነው፣ ካሁን በፊት 631 ነበር ከዚያ በፊትም 624 ነበር፣ ባለፈው ዓመት 11 ልጆች ከ600 በላይ አስመዝግበዋል ዘንድሮ በነበረው ወቅታዊ ሁኔታና የፈተና ቦታ አዲስ ከመሆኑ አኳያ 3 ልጆች ናቸው ከ600 በላይ ያስመዘገቡ፣እስከ 590 10 ልጆች አሉ፣ ውጤቱ ጥሩ ነው የወደቀ ተማሪ የለንም ያስፈተንናቸው 43 ተማሪዎች በሙሉ ከ50 ከመቶ በላይ ያስመዘገቡ ናቸው፣ 27ቱ ሴቶች ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡ በትምህርት ቤቱ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበው ናትናኤል ሽታዬ በፈተና ወቅት ምንም የተፈጠረ የፀጥታ ችግር እንዳልነበር ገልጧል፡፡
“የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ስለሆንኩ ከማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች በኋላ ነበር የተፈተንነው፣ ፈተናው እዚሁ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፖሊቲክኒክ ነው ነበረው፣ ችግር የነበረው በማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ጋ ነው፣ በእኛ ጊዜ የፀጥታ ችግር አልነበረም፡፡ ” በዚሁ ትምህርት ቤት 516 ያስመዘገበችውና በህክምና ትምህርቷን ለመቀጠል የምትፈልገው ህሊና ማስተዋል በትምህርት ቤቱ የሚሰጠው ትምህርት እውቀት ባዳበሩ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና በተግባርም የተደገፈ በመሆኑ ውጤታማ እንዳደረጋቸው ተናግራለች፡፡
“ቤተ ሙከራ ውስጥ ነው ትምህርት የምንወስደው፣ ፊዚክስ ክፍለ ጊዜ ካለን ወደ ፊዚክስ ክፍል ሄደን እዛው እንማራለን፣ ለሌሎችም ትምህርቶች ክፍል አለ፣ ቀድሞ ከነበርኩበት ትምህርት ቤት የሚለየው፣ በቤተ ሙከራ ነው፣ ሁሉንም በተግባር ነው የምንማረው፣ ትንሽ ጠንከር ይላል ትምህርቱ፣ ያ ረድቶናል ብየ አስባለሁ፡፡”
621 ያስመዘገበውና ሁለቱም ወላጆቹ የጤና ባለሙያዎች መሆናቸውን የሚናገረው ናትናኤል የሚሰጠው የተግባር ትምህርትና የመምህራን ትጋት ለውጤቱ መመዝገብ አስቷፅኦ አለው ብሏል፣ ትምህርቱን በፋርማሲ ለመቀጠልም ሀሳብ አለው፡፡
“621 ነው እኔ ያመጣሁት ከ700፣ ለማጥናት ያሰብኩት ፋርማሲ ነው ግን ልቀይር እችላለሁ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ናቸው የሚያስተምሩት፣ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ነው የሚያስተምሩት፣ በተጨማሪ በተግባር እየን እንድንማር ያግዙናል፣ ሁሉም ነገር የተሟላ ነው፣ መጽሀፍትም ቢሆን፣ መማሪያ ክፍሎችም፣ 43 ሆነን በሁለት መማሪያ ክፍሎች ነበር የምንማረው፣ በስርዓት ቁጥጥር የነበረበት ትምህርት ቤት ነው፡፡ ”
መምህር አባቷና የጤና ባለሙያ የሆኑት እናቷ ክትትልና ድጋፍ ያደርጉላት እንደነበርም ህሊና አመልክታለች፡፡
“ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው አቡነ ጎርጎሪዮስ ነው የተማርኩት፣ ፈተና ተፈትኘ አልፌ ባሕር ዳር ስቴም ኢንኩቤሽን ሴንተር ገባሁ፣ አባቴ መምህር ነው በሌሎች የቤተሰቦቼ ግፊትና ክትትል፣ ጥሩ ውጤት አስመዝግቤያለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡”
የባህር ዳር ሰቴም ኢንኩቤሽን ሴንተር ባለፈው ዓመትም 44 ተማሪዎችን አስፈትኖ ሁሉም ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባታቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በ2014 ዓ.ም ለፈተና ከተመዘገቡ 985ሺህ 354 ተማሪዎች መካከል፣ 896 ሺህ 520 ተማሪዎች ተፈትነው 29ሺህ 909 ብቻ ከ50 ከመቶ ማስመዝገባቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አሳውቋል፡፡

Äthiopien | Bahir Dar STEM-Inkubationszentrum
ምስል Alemenew Mekonne/DW
Äthiopien | Bahir Dar STEM-Inkubationszentrum
ምስል Alemenew Mekonne/DW

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ