1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠ/ሚ ዐቢይ የኖቤል የሰላም ሽልማታቸዉን ተቀበሉ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 30 2012

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በኦስሎ የኖቤል የሰላም ሽልማታቸውን ተቀበሉ። ዐቢይ የኢትዮ ኤርትራ ወደ ሰላም መምጣት ዋናዉ መሃንዲስ ተብለዉ ተሞግሰዋል። በሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ጥሩ ንግግር ማሰማታቸዉን የዓለም ብዙኃን መገናኛዎች እየዘገቡ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3UZ2M
Norwegen Verleihung des Friedensnobelpreises
ምስል Ethiopian prime minister office

የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በኖርዌይ፣ ኦስሎ የኖቤል የሰላም ሽልማታቸውን ተቀበሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱን የአፍሪቃ ህዝቦችና የዓለም ህዝቦችን ወክዬ ነው የምቀበለው ሲሉ ባሰሙት ንግግር ለኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሰላም ቁርጠኝነት ወሳኝ እንደነበር አልሸሸጉም።  ከ20 ዓመታት በፊት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የሬድዮ ኦፕሬተር እንደነበሩ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣  ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆንኩ በኋላ የሁለቱ አገራት ጠብ መቆም እንዳለበት ወሰንኩ ብለዋል።
« ከ 18 ወራት በፊት ጠቅላይ ሚንስትር እንደሆንኩ በኢትዮጵያና ኤርትራ ያለዉን ዉጥረት መለወጥ አስፈላጊ   መሆኑ ተሰማኝ።  በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለዉ ሰላም  እሩቅ እንዳልሆነ  ሁለቱን ሃገራት የከፋፈለዉ የሃሳብ ግንብ መዉደቅ እንዳለበት አምን ነበር። በዚህ ምትክ በሁለቱ ሃገራት መካከል የዘመናት የወዳጅነት የትብብር እና የጥሩ ፍላጎት ድልድይ መተካት እንዳለበትም አምን ነበር። በዚህም ሃሳብ ነዉ ከአጋሬ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሰላም ድልድይን መገንባት የጀመርኩት። ሁለታችንም ሰላምን ለመገንባት ዝግጁ ነበርን።»      
መደመር አገር በቀል ሀሳብና በጋራ ብልጽግና ላይ ያተኮረ ፍልስፍና ነዉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመደመር ጽንሰ ሃሳብ እኛና እነሱ የሚባል ነገር የለም ሲሉ በኖቤል ሽልማት ሥነ ስርዓት ላይ የነበረዉን ተጋባዥ እንግዳ አስደምመዋል። ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆማችን ለዓመታት ነፃ አገር ሆነን ቆይተናል፤  የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ቀጠና እንጂ የኃያላን መሻኮቺያ፣ የአሸባሪዎች መመሸሸጊያም እንዲሆን አንፈልግም ብለዋል ዐቢይ። በኢትዮጵያ በቅርቡ የሚካሄደዉን ምርጫ በተመለከተ ለዴሞክራሲ ግንባታ መንገድ ዘርግተናል፤ ነፃና ፍትሓዊ ምርጫ እናካሂዳለን ፤ ለሁሉም ዜጎች እኩልነት መረጋገጥ አብረውኝ እንዲሰሩ ለኢትዮጵያውያን ጥሪ አቀርባለሁም ብለዋል። 

Norwegen Verleihung des Friedensnobelpreises
ምስል Ethiopian prime minister office

የኖርዌ የሰላም ኖቤል ኮሚቴ ኃላፊ ቤሪት ራይስ አንደርሰን ቀደም ሲል ባሰሙት ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን እንደመጡ የኤርትራና ኢትዮጵያን ዉዝግብ በፍጥነት ለመፍታት በመወሰን ከኤርትራ ጋር የሰላም ጥረቱ መሳካቱን ተናግረዋል። የኢትዮ ኤርትራ ወደ ሰላም መምጣት ዋናዉ መሃንዲስ ሆነዋልም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን አሞግሰዋቸዋል።  እንድያም ሆኖ የኤርትራዉ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አወንታዊ ምላሽ ባይኖር ኖሮ ይህ የሰላም ጥረት ባልተሳካ ነበር ሲሉ ኖርዊ የሰላም ኖቤል ኮሚቴ ኃላፊ ቤሪት ራይስ አንደርሰን ተናግረዋል።   
« የሰላም ጥረቱን ያነሳሱና ከሰላም ድርድሩ ጀርባም ዋና መሃንዲስ ነበሩ። ከኤርትራ ጋር ሰላም ለማዉረድ የተደረገዉ ጥረት በአመርቂ ሁኔታ ዉጤታማ ሆንዋል። ይሁንና የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መልካም ይሁንታ ባይኖር ኖሮ የሰላም ጥረቱ ባልተሳካ ነበር።  ይህ ርምጃ አመርቂ ለዉጥን አስገኝቶአል። የሁለቱ ሃገር ሕዝቦች ሰላምን አዉጀዋል። ይህ በራሱ ለወደፊት ርምጃ ትልቅ ግብዓት ነዉ። »            
በሃገሪትዋ ተደንግጎ የነበረዉን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በአስቸኳይ ማንሳት ለዐቢይ ዋንኛ ስራ ነበር ያሉት ኖርዊ የሰላም ኖቤል ኮሚቴ ቤሪት ራይስ አንደርሰን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን እንደመጡ በሽዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን መልቀቃቸዉንም አስታዉሳወዋል። በሃገሪቱ ለተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ወይም ለተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ እዉቅና መስጠት አንዱ ጤናማ የዴሞክራሲ ክፍል መሆኑንም አሳይተዋል። በነጻ ሃሳብን የመግለጽ መብትም አንዱ የዴሞክራሲ ክፍል መሆኑንም አሳይተዋል ብለዋቸዋል። በሽልማጥ አሰጣጡ ላይ የኖርዌ ንጉሳዉያን ቤተሰቦች ባለስልጣናት ኢትዮጵያዉያን ተገኝተል። የሽልማት አሰጣጥ ስነስርአቱ በኢትዮጵያ ወጣት ሙዚቀኞችም የታጀበ ነበር። ዶይቼ ቬለን «DW» ጨምሮ የዓለም የመገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር የሰላም ኖቤል ሽልማት መቀበላቸዉን እና በሽልማት አሰጣጡu ሥነ-ስርዓት ላይ ጥሩ ንግግር ማስተላለፋቸዉን እየዘገቡ ነዉ።

Norwegen l Verleihung des Friedensnobelpreis an Abiy Ahmed in Oslo
ምስል picture alliance/dpa/NTB scanpix/H. M. Larsen
Norwegen Verleihung des Friedensnobelpreises
ምስል Ethiopian prime minister office

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ