1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ ከንግድ ዘርፉ ጋር ያደረጉት ዉይይት  

Merga Yonas Bula
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 9 2010

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር መወያየታቸዉን እንደቀጠሉ ነዉ። ትላንት ከነጋዴዎች እና ባለሃብቶች ጋር ተወያይተዋል። የገንዘብና የመሬት አቅርቦት፣ ከታክስና ከሌሎች መልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸዉን ተሳታፊዎች ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/2wCzO
Abiye Ahmed in Addis Ababa
ምስል Reuters/Stinger

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ከባለሐብቶቹ ጋር ባደረጉት ዉይይት የዉጭ ምንዛሪ እጥረት፤ የመሬት አቅርቦት፤ ታክስ፣ ሙስናና ሌሎች ጉድለቶች ላይ ተሳታፍዎች ያላቸዉን ቅሬታ እንዳነሱም ተሳታፍዎች ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። በመድረኩ ላይ የንግድ ዘርፉ አባላት አነሱት ከተባለዉ ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የሕዝብ ግኑኝነትና ኮሙኒኬሼን ዳይሬክተር አቶ ደበበ አበበ እንዲሕ ሲሉ ለዶይቼ ቬሌ ይናገራሉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አቢይ የንግድ ዘርፉ አባላት ያቀረቡትን ቅሬታ ለመፍታት ለየት ያለ አቀራራብ ይዘዉ መምጣታቸዉን አቶ ደበበ ይናገራሉ። ይሄን በተመለከተም ሁለት ምሳሌዎች አንስተዋል።

ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉት የኢኮኖሚ ባለሙያዉ አቶ ጌታቸዉ ተክለማርያም፤ ጠ/ሚ አቢይ ከባለሃብቶች ጋር ያደረጉት ዉይይት የፖሊሲ አቅጣጫ እንደሚጎድለዉ ይናገራሉ። እንደ እኮኖሚ ባለሙያዉ ምልከታ ትላንት የነበረዉ መድረክ በመንግስትና በንግድ ዘርፍ አባላት መካከል የነበረዉን የእምነት ክፍተት በመሙላት ረገድ ሚና እንደነበረዉ ግን ሳይጠቅሱ አለለፉም። የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የሕዝብ ግኑኝነትና ኮሙኒኬሼን ዳይሬክቴሩ አቶ ደበበ መድረኩ የትዉዉቅ በመሆኑ ብዙ ጉዳዮች አለመነሳቱን ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

ባለሐብቶቹ ቅሬታቸውን ለንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እንድያስመዘግቡ፣ ቅሬታቸዉም በጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ታይቶ መልስ ይሰጥበታል የሚል ተስፋ አላቸዉ።
የኤኮኖሚ ባለሙያዉ አቶ ጌታቸዉ ግን  የሚከተለዉ አስተያየት አላቸዉ።

የግል ዘርፉም በዉይይቱ ወቅት ለዉጥ የሚሹ ነገሮችን በማመላከት ረገድ ደካማ እንደነበረ አቶ ጌታቸዉ ይናገራሉ። እንደ እሳቸዉ አባባል የተነሱት ነጥቦች  ባጠቃላይ ጥቃቅንና ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ያነጣጠሩ እንደነበሩ እና  በፖሊሲ  ሊመጡ የሚችሉ ለዉጦችን የማያያመለከቱ መሆኑንም አክሎበታል። አቶ አበበ በበኩላቸዉ ችግሮች ያሉት በግሉ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በመንግስት በኩሉም እንዳለ በዉይይቱ ወቅት መነሳቱን ይናገራሉ። 

በመንግስት ባለስልጣናትና በግል ባለሃብቶች መካከል ያለዉ የጥቅም ትስስር የሐገሪቱን  የንግድ ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዳይሆንና ወደ ፊት እንዳይጓዝ አድርጓል በማለት የሚተቹ አሉ። ትስስሩ ረጅም ጊዜ የቆየ በመሆኑ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ከፍተኛ ፈተና እንደሚሆንም የኢኮኖሚዉ ባለሙያ አቶ ጌታቸዉ ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል።

መርጋ ዮናስ

ነጋሽ መሐመድ