1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጣናን ከእምቦጭ ለመታደግ የተሠማሩት የኦሮምያ ወጣቶች

ዓርብ፣ ጥቅምት 3 2010

ከተለያዩ የኦሮምያ ልዩ ዞኖች የተውጣጡ ቁጥራቸው ከ 200 የሚበልጡ ወጣቶች የጣና ሐይቅን ከእንቦጭ አረም ለመታደግ ባህር ዳር ከተማ ይገኛሉ። መሪ ቃላቸው «ጣና የኛ ነዉ» የሚል ነው። 

https://p.dw.com/p/2lmQ5
Wasserhyazinthen  Lake Tana Äthiopien
ምስል Adugnaw Admas

የኦሮምያ ወጣቶች

ከሰባት የተለያዩ የኦሮምያ ከተሞች ተውጣጥተው የጣናን ሐይቅ ከእንቦጭ ለመታደግ ሐሙስ ዕለት ጉዞ የጀመሩትን ወጣቶች በስልክ ያነጋገርኳቸው ፍቼ ከተማ ላይ ዕረፍት አድርገው ራሳቸውን በምግብ ሲያጠናክሩ ነው። ሚሊዮን ማማ የወጣቶቹን በጎ አድራጎት ጉዞ ከአዲስ አበባ ካስተባበሩት አንዱ ነው።  «የጣና ችግር የኛ ችግር መሆኑን አውቀን ነው ያስተባበርነው» ይላል።
ሚሊዮን እንደሚለው በጠቅላላው አስተባባሪዎቹን ጨምሮ 214 ሴት እና ወንድ የኦሮምያ ወጣቶች ባህር ዳር ከተማ ዘምተዋል። ከዛሬ ዓርብ ጀምሮም« ጣና የኛ ነው!» በሚል መሪ ቃል  የተሰባሰቡት ወጣቶች በአማራራ ክልል የሚገኘውን የጣና ሐይቅ ላይ የተንሳፈፈውን የውኃ አረም ለማጥፋት የመንቀል ርምጃቸዉን ያካሂዳሉ። « አረሙ እስኪወገድም ድረስ ወጣቶቹ ደግመው ሄደው ትብብራቸውን ለማሳየት ጥግጁ ናቸው።»
የሰበታ ወጣቶች ሊግ ምክትል ኃላፊ የሆነችው ከበቡሽ ቶሎሳ ወደ ባህር ዳር ከተጓዙ ሴት በጎ ፈቃደኞች አንዷ ናት። እሷም በአካባቢዋ ያሉትን ወጣቶች አስተባብራለች።  እንደምትለውም የጉዟቸው አላማ አረም ከመንቀል ያለፈ ነው።« ለባህርዳር ከተማ ወጣቶች ስራው ከብዶ ሳይሆን እኛ ከጎናቸው መሆናችንን ለማሳየት ነው » ስላለች የጉዞዋቸውን አላማ ስትናገር።
በባህር ዳር ከተማ የሚገኘው የጣና ሐይቅ በአረም ከተወረረ ሰነባብቷል። የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደገለፁልን ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት አረሙን ለማጥፋት የአካባቢው አርሶ አደሮች ጥረት አድርገዋል። የክልሉ መንግሥት ያለውን ችግር ለህዝቡ በይፋ በማሳወቁ አረሙ ትልቅ አጀንዳ መሆን እንደቻለ ይናገራሉ።
ጉዳዩ ይፋ መሆኑም እስካሁን በኦሮምያ ክልል በጎ አድራጎት ሥራ ላይ ይሳተፉ የነበሩት ወጣቶች ትኩረታቸውን ወደ አማራ ክልል እንዲያደርጉ የረዳ ይመስላል።በፍርዱ ወንድምሻው የሱሉልታ ከተማ የወጣቶች ሊግ ኃላፊ ነው።  እሱም በአካባቢው የሚገኙ ሶስት ሴቶችን ጨምሮ 31 ወጣቶች እንዲሰባሰቡ እና በጣና ሐይቅ ላይ እንዲዘምቱ አስተዋፅዎ አድርጓል። ከሱሉልታ ከተማ አራት ቀበሌዎች የተውጣጡትን ወጣቶች ለማሰባሰብ በፍርዱ እንደሚለው ቀላል ነበር። ሁሉም የተሰባሰቡት በአንድ ቀን ነው። 
የሱሉልታ ከተማ የወጣቶች ሊግ የሆነው በፍርዱ ከዚህ በፊት በአካባቢያቸው በተለይ በትምህርት ዘርፍ እና በአትክልት መትከል ሥራ እንደተሳተፉ ይገልፃል። ሩቅ ቦታ ሄዶ የበጎ አድራጎት አገልግሎት መለገስ ለነሚሊዮንም አዲስ ነገር አይደለም። ይሁንና የአሁኑን የጣናን ጉዞ ለየት የሚያደርገው ነገር አለ። ከለገጣፎ፤ ከዱከም፣ ከቢሾፍቱ ፣ ከቡራዩ፣ እና ሌሎች በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ አባባቢዎች የተሰባሰቡት ወጣቶች ጉልበታቸውን ተጠቅመው ጣናን ከአረም ከማፅዳት ጎን ለጎን ደግመው ደጋግመው ስለኢትዮጵያውያን  አንድነት ይመክራሉ። 
የወጣቶቹ ተሳትፎ በአማራ ክልልም በኩል ድጋፍ አግኝቷል። የክልሉ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ የእንቦጩን አረም ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል ሌሎች መንገዶች ላይም እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል።
በበጎ ፍቃደኝነት የጣናን ሐይቅ ከአረም ለማፅዳት ከኦሮምያ ክልል የተጓዙት ወጣቶች ከሁለት እስከ ሶስት ቀን በስፍራው በመቆየት ድጋፋቸውን ለማሳየት እየሞከሩ ይገኛሉ። ሌሎች ወጣቶች እንደነሱ ምን ማድረግ ይችላሉ? ሁሉም በዚህ ላይ ምላሽ አላቸው።
የጣና ሐይቅን ከእንቦጭ አረም ለመታደግ ከተለያዩ የኦሮምያ ልዩ ዞን የተውጣጡ ቁጥራቸው ከ 200 የሚበልጡ ወጣቶች ሰሞኑን ባህር ዳር በመገኘት ስለሚያደርጉት ድጋፍ የቃኘውን የወጣቶች ዓለም ዝግጅት በድምፅ ዘገባም ያገኛሉ።
ልደት አበበ
ሸዋዬ ለገሠ

Tanasee in Äthiopien
የጣና ሐይቅ ምስል picture alliance/Peter Groenendijk/Robert Harding
Wasserhyazinthen  Lake Tana Äthiopien
የእንቦጭ አረምምስል Adugnaw Admas