ጣና ሐይቅን የማዳኑ ዘመቻ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:35
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:35 ደቂቃ
29.08.2017

ባለፈዉ ሳምንት የጀመረዉ ዘመቻ በዚህ ሳምንትም ይቀጥላል፤

ምሁራን እዉቀታቸዉን እያስተባበሩ ነዉ፤ ኅብረተሰቡ ደግሞ ጣናን እናድን ብሎ ተነስቷል። የጎጃምና ጎንደር ወጣቶች ከሌላ አካባቢ ያሉ ወገኖቻቸዉን አስተባብረዉ ጣናን ከወረረዉ አረም ለማላቀቅ ዘመቻቸዉን አንድ ብለዋል። ባለፈዉ ሳምንት ባህር ዳርና ጎርጎራ አካባቢ በአባይ ወንዝ እና በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋዉን የዉኃ ጠር አረም ሲነቅሉ ዉለዋል።

 የዉኃ ፀር የሆነዉ ምህረት የለሹ እንቦጭ የተሰኘዉ መጤ አረም በጣና ሐይቅ እና አካባቢዉ ለመንሰራፋት ከአምስት ዓመታት ያላነሰ ጊዜ መዉሰዱን ባለፈዉ ዝግጅት ያነጋገርናቸዉ ምሁራን መግለፃቸዉ ይታወስ ይሆናል። በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ከሰጡን ምሁራን አንዱ የኢትዮጵያ የአካባቢ እና የደን ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዉብዓለም ታደሰም፤  መጤዉ የዉኃ አረም የሐይቁን 50 ሺ ሄክታር የሚሆን አካባቢ መሸፈኑንም ገልጸዉልናል። የእምቦጭ አረም መስፋፋት የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስቦ መነጋገሪያ መሆኑም ከዚህ በፊት በተናጠል ምንድነዉ እያሉ ይጠይቁ የነበሩ ወገኖችን ጆሮ ሳበና እንደዜጋ የበኩላቸዉን ማድረግ እንዲችሉ አሰባሰባቸዉ። የጣና ሐይቅ እና አካባቢዉ እንክብካቤ እና ጥበቃ በጎ አድራጎት ማኅበርም ተመሠረተ። ቀደም ሲል ድምፁን የሰማችሁት ቃልኪዳን ፀና የዚህ ማኅበር የባህር ዳር አስተባባሪ ነዉ፤ ከአንድ ሳምንት በፊት የአካባቢዉን ሕዝብ በማስተባበር የሠሩት ገልጾልናል፤

Äthiopien Kampagne Save Lake Tana

«እኛ የሠራነዉ በባህር ዳር አንድ ያቋቋምነዉ የበጎ አድራጎት ማኅበር አለ፤ በአካባቢዉ ሰዉ እንዲሁም ደግሞ አዲስ አበባ እና ጎንደር ያሉ አባላቶችን አዋቅረን በጎ አድራጎት ማኅበሩ በክልሉ ተቋቁሟል። በጣናም እንዲሁም ደግሞ በአባይ ላይ በተከሰተዉ የእምቦጭ አረም በቀጥታ እኛን ይመለከተናል በሚል ሃሳብ ያንን ዘመቻ አድርገናል፤ አረሙን መንቀል ነዉ ያዉ በእጅ ያዉ ወንዝም ስለሆነ ያለዉ አማራጭ በእጅ መንቀል ነዉ። ከአካባቢ ጥበቃ እና ከወጣቶች ባህል እና ስፖርት ጋር በመተባበር እምቦጭ የመንቀል ሥራ ባለፈዉ ቅዳሜ ቀን አከናዉነናል። እንቦጩ በእጅ ተነቅሎም ዉጤታማ ሆነናል። በመቀጠልም አሁን ነሐሴ 25 ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ30 ላይ የከተማዉን ሕዝብ እንጠራለን ያን ቀንም ደግሞ ቀጣይ የአባይን ወንዝ ተፋሰስ ይዞ ያለዉን የእምቦጭ አረም ነቀላ ፕሮግራም እናካሂዳለን።»

ቃል ኪዳን እንደሚለዉ እምቦጭ አረም የጣናን ሐይቅ መዉረሩን እሱና መሰሎቹ ሲሰሙ ያን ያህል ጉዳት እንዳስከተለ አልተረዱትም ነበር። የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስቦ የምሁራን መነጋገሪያ መሆኑን ከተረዱ በኋላ እነሱም ለዚህ ተግባር ተነሳሱ።

«ያለዉን ነገር ስንሰማዉ ልክ እንደተራ ነገር ነበር የሚሰማዉ። አሁን ግን ያዉ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑ በተለያዩ ሚዲያዎች እየተነገረ ነዉ። እኛም የተለያየ ነገሮችን እያነበብን በመጣንበት ሰዓት ጉዳቱ አስከፊነቱ ከፍተኛ ሆኖ አግኝተነዋል። ስለዚህ ይህን ነገር ሁሉም ወጣቶች እንዲሰሙት የባህር ዳር ተወላጆች ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሀብት እና ንብረት ስለሆነ ሁሉም ሰዉ የእኔነት ስሜት ተሰምቶት ወደዚህ ነገር ሁሉም ትኩረት አድርጓል። ይህን ሲያደርግ ደግሞ እኛ እዚህ እንደመኖራችን ያለዉን ነገር በቅርብ እየተከታተልን ለአካባቢዉ ሰዉ እናሳዉቃለን ማለት ነዉ።»

Äthiopien Kampagne Save Lake Tana

የባህር ዳር ወጣቶች ባካሄዱት የእምቦጭ ነቀላ ዘመቻ ከተሳተፉት ወጣቶች መካከል ትዕግሥት ሁነኛዉ አንዷ ናት። «እንግዲህ እንደአጋጣሚ ይህ መጤ አረም የተከሰተዉ በጣና ሐይቅ ሰፊ አካባቢ ይዞ ሲሆን በተጨማሪም የአባይ ወንዝ ላይ ተከስቷል። ለጊዜዉ ለተሞክሮም እንዲሆን ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እና ከባህር ዳር ከተማ ወጣቶች ጋር በመተባበር የእኛ ማኅበር አባይ ላይ ወጥተን ነበር። የሕዝቡንም ንቅናቄ ለመፍጠር እንዲመች የእምቦጭንም ባህሪ አሰረጫጨቱንም ያለዉንም ሁሉን ነገር ተገንዝበን የተወሰነ አስወግደን ነዉ የተመለስነዉ።»

የእምቦጭ ፍሬ ወደ መሬት ሲወድቅ ከ10 ዓመት በላይ ለመኖር እንደሚችል ዶቼ ቬለ ከዚህ ቀደም ያነጋገራቸዉ ምሁራን ጠቁመዋል። ወጣቶቹ ይህን አረም በሚነቅሉበት ወቅት ጥንቃቄ አድርገዉ ይሆን?

«እንግዲህ ምንድነዉ አጋጣሚ ሆኖ አሁን እምቦጭ አበባም ገና ያላበበት ወቅት ነዉ። ግን እምቦጭ በአበባ እና በፍሬu ብቻ ሳይሆን ፤ በስሩም በቅጠሉም በግንዱም በብጣሽ ቅጠልም ቢሆን የሚራባ አይነት ባህርይ ነዉ ያለዉ።»

ትዕግሥት ከአፍሪቃ ሦስተኛ ከኢትዮጵያ ደግሞ አንደኛዉ ሐይቅ ጣና፤ የሀገር ሃብት በመሆኑ ሁሉም ሊጠብቀዉ እና ለትዉልድ ሊያስተላልፈዉ እንደሚገባም አሳስባለች። ከእሷ ጋር አብሮ በእምቦጭ ነቀላዉ የተሳተፈዉ ሌላዉ የባህር ዳር ወጣት ዮሐንስ ክንዴ በበኩሉ አረሙ ያካለለዉን አካባቢ እና የተሠራዉን ዘርዝሮልናል፤

Äthiopien Kampagne Save Lake Tana

ድየጣና ሐይቅ እና አካባቢዉ እንክብካቤ እና ጥበቃ በጎ አድራጎት ማኅበር አዲስ አበባ ላይ ቅርንጫፍ አለዉ። ክርስቲያን ታደለ የኮሚቴዉ ሰብሳቢ ነዉ። የእነሱ ተሳትፎ በምን ላይ እንደሚያተኩር ገልጾልናል?

«እኛ በዋነኝነት የምንሠራዉ አዲስ አበባ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማትን፣ ባለሀብቶችን እንዲሁም የማኅበሩን የበጎ አድራጎት ድርጅት እና አባላት በማንቀሳቀስ፤ በጎ አድራጊ ግለሰቦችን በማንቀሳቀስ አርሶ አደሮቹ ከታች የሚሠሩትን ሥራ ሊያግዙ የሚችሉ ግብዓቶችን የማሰባሰብ ሥራ ነዉ የምንሰራዉ በዋነኝነት። ፕሮጀክት ፕሮፖዛሎችንም በመቅረጽም በቀጣይነት ማኅበሩ ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስበት ሥራዎችን በመሥራት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ነዉ እያመቻቸን የምንገኘዉ።»

የጣና በእምቦጭ መወረር ጎንደርንም ቀስቅሷል። የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝደንት አቶ አበበ ገብረ ሚካኤል የእግር ኳስ አፍቃሪዎቹ ኅብረተሰቡ አካባቢ ተፈጥሮዉ ላይ የተከሰተዉን እንዲያዉቀዉ እየቀሰቀሱ መሆኑን ይናገራሉ።

Äthiopien Kampagne Save Lake Tana

በዚህ ዘመቻም ለአስተዳደር በሚመች መልኩ ሁለት መቶ ሰዎችን የፊታችን ዓርብ ይዞ ወደ ጎርጎራ የመጓዝ እቅድ መኖሩንም ገልጸዉልናል። ከእነሱ ጋር በመተባበር የበኩሉን በማድረግ ላይ የሚገኘዉ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኢንደርስትሪ እና ቴክኒዎሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፤ አቶ ሰሎሞን መስፍንም ባለፈዉ ዓርብ የተሄደበት የጎርጎራ አካባቢ ቀደም ብሎ በእምቦጭ ያልተወረረ ነዉ ተብሎ ታስቦ ነበር ነዉ የሚሉት።  

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእምቦጭ አረምን እያጨደ የሚፈጭ ማሽን እየሠራ መሆኑ ተነግሯል። አቶ ሰሎሞን

ከሁለት ሳምንት በኋላ ጎርጎራ አካባቢ የመጀመሪያ የሙከራ ሥራ የሚያከናዉነዉን ማሽን ለመገንባት እስካሁን ከ1,5 ሚሊየን የኢትዮጵያ ብር እንደፈጀም ገልጸዉልናል። ጣናን ያለ ሊደግፋቸዉ ይችላል።

የጣና ሐይቅን እና የአባይ ወንዝን ከእምቦጭ አረም ለማጽዳት የተጀመዉ ዘመቻ ነሐሴ 25 በአባይ ወንዝ ነሐሴ 26 ደግሞ በጣና ሐይቅ ላይ ይቀጥላል። ከእነዚህ ወገኖች ጎን መቆም የሚሻ ሁሉ በጉልበት፤ በገንዘብም ሆነ በዕዉቀቱ ሊረዳቸዉ ይችላል።  በቅርቡም ስኬታቸዉን ለመስማት ያበቃን ዘንድ ምኞታችን ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ተዛማጅ ዘገባዎች