1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጤና እና አካባቢ ጥበቃ በ2015

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 19 2008

ጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም ከቀዳሚዉ 2014 በተረከበዉ የጤና እልክ እንደታጀበ ነበር የባተዉ። በዚሁ የዘመን ቀመር 2013 ማለቂያ ገደማ በምዕራብ አፍሪቃ የተቀሰቀሰዉ የኤቦላ ወረርሽኝ እስከ 2015 ግማሽ ዓመት ድረስ የሚቀጥፈዉ የሰዉ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ታይቷል።

https://p.dw.com/p/1HVmz
Großbritannien Sturm an der Küste von Wales 6. Januar
ምስል picture-alliance/AP Photo

[No title]

ያም ሆኖ በዚሁ ዓመት ነበር መጀመሪያ ግንቦት ወር መባቻ ላይቤሪያ፤ ከዚያም ሴራሊዮን በመጨረሻም ጊኒ ከኤቦላ ነፃ ለመሆን እየተፍጨርጨሩ የመሆናቸዉ ሰናይ ዜና የተሰማዉ። ቀደም ብላ ላይቤሪያ ከኤቦላ ነፃ መሆኗን ይፋ ብታደርግም ብዙም ሳይቆይ አዲስ በተሐዋሲዉ መያዛቸዉ የተጠረጠረ ሰዎች ለክትትል ተገልለዉ እንዲቀመጡ በመደረጉ ነፃ የመሆን ተስፋዋን አደብዝዞት ቆይቷል። እስካሁን በተደረጉ ክትትሎች መሠረትም በዛሬዉ ዕለት በበሽታዉ ክፉኛ ከተጎዱት ሶስት የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ጊኒ ከኤቦላ ነፃ የመሆኗ ዜና በዓለም የጤና ድርጅት አማካኝነት ዛሬ ይፋ መደረጉን ሮይተርስ ከኮናክሪ ዘግቧል። ይሁን እና ይህን የምስራች ህዝቡ የተቀበለዉ በተደባለቀ ስሜት መሆኑ ነዉ የተሰማዉ። በርካቶች ወገን ዘመዶቻቸዉን ወላጅ ልጆቻቸዉን አጥተዉበታል። ታመዉ በህይወት ለመትረፍ የታደሉት ደግሞ በወዳጆቻቸዉ የሚደረግላቸዉ አቀባበል አላስደሰታቸዉም፤ ዛሬም ያንን ገዳይ ተሐዋሲ እንደተሸከሙ ተደርገዉ ተፈርተዋል። የ26 ዓመቱ ካማራ ይህ ዓይነቱ መገለል ከገጠማቸዉ አንዱ ነዉ፤

«ከተሻለኝ በኋላ አስቸጋሪ የሆነብኝ ነገር ሰዎች እንደድሮዉ እኔነቴ እንዲቀበሉኝ ማድረጉ ነበር። አብዛኞቹ ይደግፉኝ የነበሩ ሰዎች ችላ አሉኝ።፤ ሌላዉ ቀርቶ አስተምርበት የነበረዉ ትምህርት ቤትም አልተቀበለኝም። በጣም ከባድ ነበር።»

Guinea von WHO für Ebola-frei erklärt
ከኤቦላ ነፃ የተባለችዉ ጊኒምስል picture-alliance/dpa/A. Jallanzo

ካማራ ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2014 መጋቢት ወር ነበር የታመመዉ። ጊኒ ዉስጥ የኤቦላ ወረርሽኝ 6,200 ልጆችን እጓለ ምዉታን አድርጓል። ሀገሪቱ ዛሬ በተመ የዓለም የጤና ድርጅት ከተሐዋሲዉ ነፃ መሆኗ የታወጀዉ በኤቦላ መያዙ የተጠረጠረ ሰዉ አለመኖሩ እና በዚህም ምክንያት ህይወቱ ያለፈ ሰዉ ባለፉት 42 ቀናት አለመከሰቱ ከተረጋገጠ በኋላ ነዉ። ወረርሽኙ ባጠቃላይ የ11,302 ሰዎች ሕይወት ሲቀጠፍ 28,041 የሚሆኑ ደግሞ በተሐዋሲዉ መያዛቸዉም ተመዝግቧል። ጊኒ ከ2,500 በላይ ዜጎቿን በዚህ አጥታለች። ከጊኒ ጎን ለጎን በኤቦላ የተጎዱት ሃገራት ተጎራባቾቿ ላይቤሪያ እና ሴራሊዮን ናቸዉ። ባለፈዉ ኅዳር ወር መባቻ ላይ ነበር ሴራሊዮን ከወረርሽኙ ነፃ መሆኗን ድርጅቱ ያረጋገጠዉ። ሴራሊዮን ከኤቦላ ነፃ ብትባልም 4,000 ገደማ ዜጎቿን ለዚሁ በሽታ ገብራለች። 13 ሺህ የሚሆኑት ከበሽታዉ የዳኑ ዜጎችም በየአካባቢያቸዉ የክፉዉን ቀን ማለፍ በደመቀ ድግስ ለቀናት ሲያከብሩ እንደነበር ተሰምቷል። በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ሴራሊዮን ከጎኗ የቆሙ የክፉቀን ደራሾቿን አልዘነጋችም። የዛሬ አስራ አንድ ቀን በኤቦላ በተጎዳችበት ወቅት የገንዘብ እና የሰዉ ኃይል ድጋፍ ያደረጉላትን ሃገራትና ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች ሸልማለች። ከተሸላሚዎቹ መካከልም የጋምቢያ ፕሬዝደንት ያህያ ጃማ የወርቅ ሜዳሊያ የተሰጣቸዉ ሲሆን የጤና ጥበቃ ሚኒስትራቸዉ በፍሪታዉን ቤተመንግሥት ተገኝተዉ በስማቸዉ ተረክበዋል። ኤቦላ ያደቀቃት ሴራሊሆን በክፉ ቀን ለደረሱላት ምስጋና ለማቅረብ 199 የወርቅ፤ ብርና ነሐስ ሽልማቶችን አቅርባለች።

Guinea Noubia - letzte Ebola-Patientin
ምስል Getty Images/AFP/C. Binani

አሁን በተስፋ ከዚህ ጨካኝ ወረርሽኝ ሙሉ ለሙሉ የመገላገሏን ዜና የምትጠብቀዉ ላይቤሪያ ናት። የመጨረሻዎቹ ሁለት የኤቦላ ታማሚዎች ድነዉ ከሃኪም ቤት ወጥተዋል። ያሸመቀ ተሐዋሲ ሳይኖር ቀርቶ እንደታሰበዉ ቀናት ያለኤቦላ ትንኮሳ በሰላም ካለፈዉም በመጪዉ ጎርጎሪዮሳዊ አዲስ ዓመት መባቻ ላይ በዓለም የጤና ድርጅት የምትጠብቀዉን ብስራት ላይቤሪያ ትሰማ ይሆናል። ይቅናቸዉ።

በተሰናባቹ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2015 ከተሰማዉ ሌላ ሰናይ የጤና ጉዳይ አንዱ ከእናት ወደልጅ HIV ተሐዋሲ እንዳይተላለፍ ማድረግ የተሳላካቸዉ ሃገራት ቁጥር እየተበራከተ የመሄዱ ዜና ነበር። በዘገባዎች መሠረት ኩባ ባለፈዉ ሰኔ ወር ነዉ በዓለም የጤና ድርጅት የHIV ተሐዋሲ እና የአባለ ዘር በሽታ የሆነዉ ቂጥኝ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ማድረግ የተሳካላት የመጀመሪያዋ ሀገር የመሆኗን ማረጋገጫ ያገኘችዉ። በተመሳሳይ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ካናዳ እና ቺሊን ጨምሮ በአሜሪካን አካባቢ የሚገኙ ሌሎች 16 ሃገራትና ደሴቶችም ይህን ማድረግ ሳይቀናቸዉ እንዳልቀረ የዓለም የጤና ድርጅት ያመለከተዉ ባለፈዉ ኅዳር ወር አጋማሽ ላይ ነዉ። የHIV ተሐዋሲ በደማቸዉ ለሚገኝ ወገኖችም ተጨማሪ የህክምና ስልቶች መገኘታቸዉ የተነገረዉ በዚሁ ዓመት ነበር። በተሐዋሲዉ አዲስ የሚያዙ ሰዎችም ቁጥር በ35 በመቶ መቀነሱ፤ ፀረ ኤድስ መድሃኒት የማግኘት እድሉ ያላቸዉ ታማሚዎችም ቁጥር 15,8 ሚሊየን መድረሱ፤ ከኤድስ ጋር የተገናኘ በሽታ ታማሚዎች ቁጥር በ42 በመቶ መቀነሱ ሁሉ የተሰማዉ በሚሰናበተዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ነዉ። በሌላ በኩል ደግሞ ፖሊዮን ለማጥፋት የሚደረገዉ ጥረት በተለይ አፍሪቃ ዉስጥ ለበሽታዉ እንደመጨረሻ ምንጭ በምትታየዉ ናይጀሪያም መጠናከሩ የተነገረዉ በዚሁ ተሰናባች ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ነበር። አፍጋኒስታን እና ፓኪስታን አሁም መድኃኒቱን በሚቃወሙ ወገኖች ምክንያት በፖሊዮ ተጠቂ ሕፃናት የበረከቱባቸዉ ሃገራት መሆናቸዉ ቀጥሏል። የዓለም የጤና ድርጅት በጦርነት የምትታመሰዉ የሶርያ ሕፃናት በሀገራቸዉም ሆነ በስደት በሚገኙባቸዉ ሃገራት የፖሊዮ ክትባት እንዲያገኙ እንደሚጥር አስታዉቋል።

Karte Ebola Neue Fälle 1. Juli 2015
በኤቦላ የተጎዱ አካባቢዎች በካርታ
Sierra Leone Ebola
ምስል DWD. Pelz

የባህር ላይ ማዕበል በንፋስ ተገፍቶ በየጊዜዉ የሚያጠቃት ፊሊፒንስ ዘንድሮም አልማራትም፤ በቅርቡ እንኳ 750ሺህ ዜጎቿ በዚሁ ስጋት አካባቢያቸዉን አደጋ ሳይደርስ አስቀድመዉ እንዲለቁ ተደርጓል።

በሞቃት ወራት የደን ሰደድ እሳት የሚያጠቃት አዉስትራሊያ በቅርቡ ሜልበርን አቅራቢያ 15 ቤቶች በእሳት መዉደማቸዉ ተሰምቷል። ኢንዶኔዢያ ዉስጥ የደረሰዉ የደን ሰደድ እሳት ደግሞ ከዚህ ቀደም ሱናሚ ማዕበል ካደረሰባት ጉዳት እጥፍ እንዳከሰራት የዓለም ባንክ የተናገረዉም በዚሁ ዓመት ነዉ። ከባድ የሙቀት ማዕበልም ደቡባዊ ፓኪስታንን በዚሁ ተሰናባች ዓመት አሰቃይቷል። የ2000 ሰዎችን ህይወትም ነጥቋል። ኔፓል ደግሞ በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ተመትታለች። በሚያዚያ ወር የደረሰዉ ርዕደ መሬት ከ8000 የሚበልጡትን መግደሉ ተመዝግቧል። አፍጋኒስታን ዉስጥ ደግሞ የ400 ሰዎችን ህይወት ወስዷል። በደቡብ ምሥራቅ እስያ የምትገኘዉ ቦርኒዮ ደሴት ታዋቂዉ የድንጋይ ተራራዋን ሊወጣጡ ወደዚያ የተጓዙ 80 ተራራወጪዎች በደረሰዉ የመሬት መንቀጥቀጥ እዚያዉ አስቀርታለች። የጨቀየ መሬት መናድ ደግሞ ጓቲማላ ዉስጥ 280ዎቹን ገድሏል። በአየር መበከል የምትወቀሰዉ ቻይና በተሰናባቹ 2015ዓ,ም ነዉ በይፋ ዋና ከተማዋ ለመተንፈስ በሚያዳግት ብክለት መታመቋን የተናገረችዉ።

ጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም በተፈጥሮ ረገድ ጥፋት ብቻ ሳይሆን አዎንታዊ ክንዉኖች የታዩበት ዓመትም ነበር። ከቀዳሚዉቹ ዓመታት በተሻለ በ2015ዓ,ም ብዙ የተደከመበት የአየር ንብረትን ለዉጥ የሚያስከትለዉ ሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት እንዲቀነስ ላለፉት ዓመታት አሻፈረኝ ብለዉ የተለያዩ ምክንያቶችን ያቀርቡ የነበሩ መንግሥታት ሳይቀሩ የተሰማሙበት በመሆኑም ዉጤት ታይቶበታል። ተግባራዊነትና ዘላቂነቱ አሁንም ከጥያቄ ባይዘልም።

የአየር ንብረት ለዉጥ ተመልካች ጉባኤዉ ቀደም ባሉት ጊዜያት ተብላልተዉና ተቀናብረዉ በቀረቡለት የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ለሁለት ሳምንታት ሲነጋገር ሲደራደር ከርሟል። በቀነ ቀጠሮዉ መሠረት የጉባኤዉ መጠናቀቂ ዕለት ቢደርስም ከእጅ የገባ ይህነዉ የሚባል መግባቢያ አልነበረም። ሌሊቱን አደሩበት ያለዕንቅልፍ እንደገናም ዋሉበት እና ቅዳሜ አመሻሹ ላይ ፈረንሳዮች እፎይ አሉ። የጉባኤ አስተናጋጅና ሊቀመንበርነቱንም የተሸከመችዉ ፈረንሳይ መሪዎች እንግዶቻቸዉን አላሳፈሩም ብዙ ተደክሞበት፤ ብዙም አከራክሮ ቢሆን የሀገሪቱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎሮ ፋቢዮ የ196ቱንም ሃገራት ይሁንታ ያገኘዉን የመግባቢያ ረቂቅ ሰነድ አፅድቁልኝ ሲሉ ጠየቁና፤ እነሆ ሲሉ በድካም ለተሰላቹት ተሰብሳቢዎች የሚያነቃ መልዕክት አስተላለፉ።

Frankreich Cop21 Klimagipfel in Paris Klimaabkommen beschlossen
የአየር ንብረት ለዉጥ ስምምነቲ ደስታምስል picture alliance/ZUMA Press/Z. Lei

በየዓመቱ በኅዳር ወር መገባደጃ የሚገባዉ የዚህ ዓመቱ የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የክረምት ወራት እርግጥም የመሬት የሙቀት መጠን መጨመሩን አለያም የአየር ንብረት ለዉጥ ከቃል አልፎ እዉን መሆኑን ያሳየ ክስተት ማስከተሉም ምናልባትም በየሃገራቱ የተገባዉ የሙቀት አማቂና በካይ ጋዞች ቅነሳ ቁርጥ መሆኑን ሳይጠቁማቸዉ እንደማይቀር ነዉ የሚገመተዉ። ለአየር ጠባዩ መለወጥ ደግሞ በግንባር ቀደምትነት የሚወቀሰዉ ኤሊኒኞ የተሰኘዉ በየአስር ዓመቱ የሚከሰተዉ የአየር ንብረት ለዉጥ ነዉ። በስጳኞች ትርጓሜ ልጁ ማለትም ኤሊኒኞ በተለይ የዘንድሮዉ ክስተት ከዚህ ቀደም በነበሩት 100ዓመታት ያልታየ ዓይነት መሆኑን የፈረንሳይ የአየር ንብረት ጠበብት ትናንት ተናግረዋል። የዘርፉ ተመራማሪ ከሆኑት አንዱ ዤሮም ሉኩ እንደሚሉትም እንዲህ ያለዉን የአየር ጠባይ ክስተት በትክክል መመዝገብ የተጀመረዉ በቅርቡ በ20ኛዉ ክፍለ ዘመን በመሆኑ ከዚያ በፊት ስለተከሰቱ ተመሳሳይ አጋጣሚዎች የሚያሳይ መረጃ የለም። ኤሊኒኞ ጎርፍ እና ድርቅ የሙቀት ማዕበልን ቅዝቃዜን በተለያዩ አካባቢዎች በአንድ ጊዜ እንዲከሰቱ እንደሚያደርግ ነዉ የዘርፉ ባለሙያዎች የሚያብራሩት። በዚህ ብቻም አያበቃም የሙቀት መጠኑ እንዲጨምርም ያደርጋል። እንደባለሙያዎቹ ከሆነም ፓስፊክ ዉቅያኖስ ልዩ ልዩ የንፋስ ዓይነቶች መመንጫ ነዉ። ነፋሶቹም ከምሥራቅ ወደምዕራብ የሚነሱ ሲሆን በሚነፍሱበት አቅጣጫ ሞቃቱን ዉኃ ወደተቃራኒዉ በኩል ይገፋሉ። በዚህም ሞቃቱ ዉኃ በፓስፊክ ምዕራብ በሚገኙ የእስያ እና አዉስትራሊያ አካባቢ ይጠራቀማል። ከወዲህ በኩል ማለትም ደቡብ እና ማዕከላዊ አሜሪካ የተገፋዉ የሞቃት ዉኃ አካባቢ ከታች በሚመጣ ቀዝቃዛ ዉኃ ይተካል። ሂደቱ የዘርፉ ባለሙያዎች አፕዌሊንግ የሚሉት ነዉ። ይህ ሂደት ነዉ በፓስፊክ አጋማሽ አካባቢ የአየር ጠባይ ልዩነት ፈጣሪዉ። በምዕራብ በኩል የተጠራቀመዉ ሞቃት ዉኃም በአካባቢዉ ባለዉ ግፊት ይበልጥ ተሟሙቆ በመትነን ዝናብ ያስከትላል። ሂደቱ ተከታትሎ ንፋሱ ሲጠናከረም በአማካኝ ከሁለት እስከ ሰባት ዓመታት ባሉ ልዩነቶች ኤሊኒኞ ይከሰታል፤ በአንድ ወገን ሙቀት በሌላ ወገን ደግሞ ቅዝቃዜ። በ2015ዓ,ም የተከሰተዉ ኤሊኒኞ ድርቅ ካስከተለባቸዉ አካባቢዎች ኢትዮጵያ በዋናነት ትጠቀሳለች። መረጃዎች እንደሚጠቁሙትም ባለፈዉ እና በተሰናባቹ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመቶች ከፍተኛ የሙቀት መጠን በፓስፊክ ዉቅያኖስ ላይ ተመዝግቧል። ይህ ደግሞ ምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪቃ፤ የፓስፊክ ደሴቶች፣ ደቡብ ምሥራቅ እሲያ እንዲሁም ማዕከላዊ አሜሪካ በሁሉም ረገድ የከፋ የአየር ጠባይ እንዲገጥማቸዉ ያደርጋል። በዓመቱ መገባደጃ ወራት በተለያዩ አካባቢዎች የታዩት የተፈጥሮ አደጋዎችም በራሳቸዉ ብዙ የሚናገሩ ናቸዉ። የዩናይትድ ስቴትሱ የቴክሳስ ግዛት የገና በዓልን በሚያከብሩበት ምሽት ለ20 ደቂቃዎች ብቻ የነፈሰዉ አዉሎ ንፋስ የ11ሰዎችን ሕይወት ቀጥፎ አካባቢዉን እንዳልነበረ አዉድሞታል። የንፋሱ ኃይል እንደቅዠት የሚታሰባቸዉ የጉዳቱ ሰለባ ያዩትን ለመግለፅ ከእንባ ጋር እየታገሉ ሞከሩ፤

USA Unwetter Tornado Texas
የቴክሳስ ዉድመትምስል picture-alliance/dpa/M. Stone
USA LaPorte, Texas, Chemieindustrie Chemifabrik DuPont
ምስል Reuters/E. Seba

«ይህ ሁሉ ጉዳት በሰላሳ ሴኮንድ ገደማ መድረሱን ለማመን ያዳግተኛል። ግን ደግሞ እድሜ ልክ የፈጀ ነበር የሚመስለዉ። አስተማሪ ነኝ፤ በዚህ አካባቢ ልጆች አሉ፤ ግን ደግሞ መኖሪያ ቤታቸዉ በሙሉ ወድሟል። የእኛም ቤቶች ፈራርሰዋል ማመን ያዳግተኛል። እንዲህ ያለ ነገር አያለሁ ብዬ አስቤም አላዉቅ። አስፈሪ ቅዠት ዓይነት ነዉ።»

በፖሊስ መረጃ መሠረት ዳላስ ዉስጥ 600 ቤቶች ወድመዋል። ዉድመት አድራሹ ንፋስ ጎዳና ላይ ሲሽከከሩ የነበሩ መኪኖችን እንደላባ ነዉ ያከነፋቸዉ፤ በዚህ ዓይነትም አምስት አሽከርካሪዎች ሕይወታቸዉን አጥተዋል። 25ሺህ የሚሆኑ ኗሪዎች ከእሁድ ጀምሮ መብራት አልነበራቸዉም። በነገራችን ላይ በተለያዩ ድሀ የሚባሉ ሃገራት በአንድ ዓመት የሚጠቀሙትን የኤሌክትሪክ ኃይል በገና በዓል ሰሞን አሜሪካኖች በየዛፉ ጣራዉያና በየመንገዱ ለበዓሉ ለማድመቅ ሲሉ በቀናት ዉስጥ የሚጠቀሙበትን በጣም እንደሚበልጥ የበዓሉ ሰሞን የወጣ ጥናት ጠቁሟል።

ሰሞኑን በአሜሪካን የታየዉ የተፈጥሮ ቁጣ በንፋሱ ብቻም አልበቃም፤ ከባድ ዝናብ እና በረዶም እንቅስቃሴዉን ማስተጓጎላቸዉ አሁንም እየተነገረ ነዉ። የከፋዉ የአየር ሁኔታም በዓመት አንዴ ያዉም በክረምት ጭለማ እየመጣ የቀዘቀዘዉን የሰዉ መንፈስ የሚያሞቀዉ የገና በዓል በዚህ እና በሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች በመታጀቡ ደብሮ እንዲያልፍ ግድ ሳይል አልቀረም። የብሪታንያዋ ታሪካዊ ከተማ ዮክም እንዲሁ በጎርፍ ታጥባ ነዉ አዲሱን ዓመት ልትቀበል የተዘጋጀችዉ። ከባድ ዝናብ ግድባቸዉን እንዲጥሱ ያደረጋቸዉ ሁለት የከተማይቱ ወንዞች ዙሪያ ገባዉን ያጥለቀልቁ ሲሆን በተመሳሳይ ቀደም ባሉት ቀናትም ሊድስ እና ማንቸስተር ከተማዎችም በጎርፍ ጉዳት ደርሶባቸዋል። የአየር ትንበያ መረጃዎች አሁን ተጨማሪ የጎርፍ አደጋዎች በብሪታንያ እና ዌልስ ሊከሰቱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የክረምት ወራት የሚታየዉ የሙቀት መጠንም የክረምት ስፖርትን በማስተናገድ ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሪ ትዝቅ ለነበረዉ ስዊትዘርላንድ የመርዶ ያህል ሳይሆን አልቀረም። ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ሃገሪቱ ይህን የክረምት ቱሪዝም ማስተናገድ ከጀመረችበት ከ150ዓመት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነዉ ሙቀቱ ከፍ በማለቱ ምክንያት የአልፕስ ተራሮች በንጣቱ ከሚያስዉባቸዉ በረዶ ተጋልጠዉ ሲታዩ። የበረዶ ሸርተቴ ስፖርት አፍቃሪና አዘዉታሪዎች ብቻ ሳይሆኑ እነሱን የሚያስናግዱት የመዝናኛ ስፍራዎችም በዚሁ ምክንያት ሳይሳቀቁ አልቀሩም። የስዊዝ የአየር ትንበያ ጽሕፈት ቤት ከሳምንታት በፊት ይፋ እንዳደረገዉ 2015ዓ,ም ከበድ ያለ ሙቀት የታየበት ሲሆን ሀገሪቱም በረዥም ዓመታት ታሪኳ ሞቅ ያለ የታኅሳስ ወርን እያሳለፈች ነዉ። ይህ ሁሉ ታዲያ የጉልበተኛዉ ኤሊኒኞ መዘዝ ነዉ ተብሏል።

Faces of climate change Olafur Eliasson
የሚናፈቀዉ በረዶምስል DW/T.Walker

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ