1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ክስየተሰረዘላቸዉ ተከሳሾች

ረቡዕ፣ ግንቦት 22 2010

እነፋሲል ሕጎችን ከመሻር፤መሻሻል ወይም አሰራሮችን ከመቀየር በተጨማሪ ሌላ ያልተመለሰ ጥያቄም አላቸዉ።በኢሳት ላይ የተመሠረተዉ ክስ ቢነሳም ራሱ ፋሲል እና ቢያንስ አንድ ሌላ ባልደረባዉ ላይ በሌሉበት የተላለፈዉ ፍርድ እንዳለ ነዉ።

https://p.dw.com/p/2yexd
Dish Network Übernahme Sprint Nextel
ምስል picture alliance/AP Photo

Reax on droped charges - MP3-Stereo

የኢትዮጵያ መንግሥት የመሠረተባቸዉን ክስ የሠረዘላቸዉ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ኃላፊዎች የክሱ መሠረዘ በሥራ እና አሰራራቸዉ ላይ ብዙም ለዉጥ እንደማያመጣ አስታወቁ።የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ESAT)፤ በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (OMN)፤ በአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ዶክተር ብርሐኑ ነጋ እና በOMN ዋና ኃላፊ አቶ ጀዋር መሐመድ  ላይ መስርቶት የነበረዉን ክስ ማንሳቱን ትናንት አስታዉቋል።የቴሌቪዥን ጣባዎቹ ኃላፊዎች እንዳሉት ክሱ መነሳቱ ጥሩ ነዉ።ይሁንና የጣቢያዎቻቸዉን እና የጋዜጠኞቻቸዉን ነፃነት ለማስከበር ሌሎች ተጨማሪ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸዉ።

ሰዎቹ የተከሰሱት «ሕገ-መንግሥቱን እና ሕገ-መንግሥታዊዉን ሥርዓት በኃይል የማስወገድ ሙከራ» በሚል የወንጀል ጭብጥ ነበር።ቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ ደግሞ ግለሰቦቹ የሚያስተላልፉትን ጥሪ በመቀበል፤ለሽብር ቡድን ድጋፍ በማድረግ-----»እያለ ይቀጥላል-የክሱ ጭብት።ትናንት በአራቱም ላይ የተነሳዉ ክስ ተነሳ።አራቱም ከኢትዮጵያ ዉጪ ናቸዉ።

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (OMN) መሥራች እና ዋና ሥራ-አስኪያጅ ጀዋር መሐመድ እንደሚሉት  ክሱ መጀመሪያያም የሕዝብን ትግል ለማፈን ያለመ ነበር።የESAT ዋና አዘጋጅ ፋሲል የኔዓለም ደግሞ «አንቺዉ ታመጪዉ---አንቺዉ----»ዓይነት ይላል።«እነሱ ከሰሱን፤ እነሱዉ ሠረዙት።»ያም ሆኖ ጋዜጠኛ ፋሲል እንደሚለዉ የክሱ መነሳት ጥሩ ነዉ። በቂ ግን አይደለም።አቶ ጀዋር መሐመድም ተመሳሳዩን ነዉ የሚሉት።የክሱ መነሳት ቢያንስ ሐገር ዉስጥ ያሉ ተመልካቾች ጣቢያዉን ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲከታተሉ ይጠቅማል-ጅዋር እንደሚሉት።ጣቢያዉ ሐገር ዉስጥ  በነፃነት ለመሥራት ግን አሁንም ብዙ ሕግጋትና አሰራሮች መለወጥ አለባቸዉ።

Antennen und Funk Anlage Schüssel Mond
ምስል Fotolia/Coburn

                                           

ፋሲልም «አፋኝ» ያላቸዉ ሕጎች መነሳት አለባቸዉ ባይ ነዉ።የመንግሥት የመጨቆኛ ተቋማት አሠራርም መለወጥ ይገባቸዋል። ይሕ ሲሆን-ነዉ ኢሳት ከሐገር ዉስጥ በነፃነት መዘገብ የሚችለዉ።እነፋሲል ሕጎችን ከመሻር፤መሻሻል ወይም አሰራሮችን ከመቀየር በተጨማሪ ሌላ ያልተመለሰ ጥያቄም አላቸዉ።በኢሳት ላይ የተመሠረተዉ ክስ ቢነሳም ራሱ ፋሲል እና ቢያንስ አንድ ሌላ ባልደረባዉ ላይ በሌሉበት የተላለፈዉ ፍርድ እንዳለ ነዉ።

                                  

ዶክተር ብርሐኑ ነጋ፤ አቶ ጀዋር መሐመድ እና ሁለቱ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሁን በተነሳላቸዉ የወንጀል ጭብጥ የተከሰሱት ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።በነዶክተር መረራ ጉዲና መዝገብ።