1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥራት አልባ ሚሊዮን ኮንዶሞች

ዓርብ፣ ሰኔ 24 2008

የኢትዮጵያ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ 69 ሚሊዮን ኮንዶሞች የጥራት ደረጃቸው እጅግ ያሽቆለቆለ ነው በሚል ሰሞኑን እንዲወገዱ ማዘዙ የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኖ ቆይቷል። ስሙ ካልተጠቀሰ የህንድ ኩባንያ በ2 ሚሊዮን ዶላር ተገዙ የተባሉት ኮንዶሞች ጥራት ቀድሞውኑ ሳይረጋገጥ ወደ ሀገር መግባቱ በነበረው አሠራር ላይ ጥርጣሬ አጭሯል።

https://p.dw.com/p/1JH3D
Kondome
ምስል picture alliance / OLIVER BERG / APA / picturedesk.com

ጥራት አልባ ሚሊዮን ኮንዶሞች

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራት የሚገኙ ወጣቶች ከድኅነት ባሻገር የሚፈታተናቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። በሃገራቱ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት እና የአባላዘር በሽታዎች መስፋፋት ብሎም ያልተፈለገ እርግዝና የወጣቶች ዋነኛ ፈተናዎች ናቸው። እናም በየሃገራቱ ወጣቶች ጤንነታቸውን ለመጠበቅ እና ላልተፈለገ እርግዝና ላለመጋለጥ ከምንም በፊት ከጋብቻ በፊት ራሳቸውን እንዲጠብቁ አለያም ከልቅ የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዲቆጠቡ ይመከራል። ኾኖም በተያያዥ ኮንዶም በመጠቀም ከተጠቀሱት ችግሮች ራሳቸውን እንዲከላከሉም ከመምከር ባሻገር በየሃገራቱ ዘመቻዎች ይከናወናሉ።

የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁ ኮንዶሞችን ጉዳይ በተመለከተ በፌስ ቡክ እና በስልክ የደረሱንን አስተያየቶች አሰባስበናል። ከዛ በፊት ግን በዋትስአፕ የደረሰንን መልእክት እናስቀድም። ስርዓቱ ምን ያኽል በሙስና እንደተዘፈቀ ማሳያ ነው፤ ሁሉም በያለበት ቦታ፣ ባለበት የሥራ ድርሻ ዘረፋውን እያጧጧፈው ነው ሲሉ የድምጽ አስተያየታቸውን በዋትስ አፕ የላኩልን አድማጭ ግዢውን የፈጸመው አካል ተጠያቂ ሊኾን ይገባል ብለዋል።

የዋትስአፕ አስተያየት ሰጪው አድማጫችን ከሥራዬ ተቀራራቢነት አንፃር እንደማውቀው ከሆነ ግዢው ሲፈጸም ናሙና ተወስዶ ከታየ በኋላ በናሙናው መሠረት ነው ብለዋል። እናም ከግዢው አንስቶ ጥራቱ ይመጥናል በሚል መጀመሪያ ላይ ያረጋገጠው አካል በአጠቃላይ የሙስና ሰንሰለት ውስጥ የተያያዙ ግለሰቦች ሊጠየቁ ይገባል ሲሉ አክለዋል።

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲምክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በድረ ገፁ ላይ የሰፈረው ጽሑፍ፦ «ህብረተሰቡ ጥራቱና ደህንነቱ የተረጋገጠ የምግብና መድሃኒት አቅርቦት እንዲያገኝ ለማድረግ የቁጥጥር ስራ በዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የምግብ ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል።» ይላል። በፌስቡክ የደረሱን አስተያየቶችን እናሰማችሁ።

Kondom

ልዑል አለማየሁ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታያችን፦ የኢትዮጵያ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በቅርበት እንደሚያውቁት ገልጠዋል። «ቀደም ሲል ፋርሚድ የሚባል መጠሪያ የነበረው ሲሆን በዚያን ወቅት የተሻለ ጥራትና በአይነት አቅርቦት የነበረው ሲሆን ወደ መድኃኒት ፈንድና ና አቅርቦት ኤጀንሲ ከተቀየረ ወዲህ ግን ቀስ በቀስ አገልግሎቱ እያሽቆለቆለ ይበልጥ ፓለቲካዊ እየሆነ የሄደ መንግስታዊ ድርጅት ነው!!!! በአሁኑ ሰአት መሰረታዊ የሚባሉ መድኃኒቶችን ከ50% በላይ ማቅረብ ያልቻለ ጥራቱና ፈዋሽነቱ አጠራጣሪ እየሆነ የመጣ ፖለቲካዊ መስመር መከተል የጀመረ የመድኃኒት አይነትንና ጥራትን ሳይሆን ሽያጭን ወይም የገንዘብ ገቢን ብቻ ትኩረት ያደረገ ድርጅት ነው ስለሆነም ስለ ኮንዶም ብቻ ሳይሆን ከዚህ የሚበልጥ ያልተሰማ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያወጣ መድሃኒት የአገልግሎት ጊዜው አጭር በመሆኑ ምክኒያት የሚበላሹ ቤቱ ይቁጠረው!!!! ስለዚህ ተጠያቂው ሁሉም አገሪቱን የሚመሩት ሰዎች ናቸው ምክኒያቱም ሁሉም በሚመራው የህዝብ አገልግሎት ቦታ ሁሉ ለመስማት የሚሰቀጥጥ ወንጀል ታቅፎ ተቀምጦ ነው ያለ!! ወንጀል በሀገራችን ብርቅ አይደለም አይገርመንም!!!! ብርቃችን ጥሩ ስራ ነው ብርቃችን መልካምነት ነው!!» ብለዋል።

ሌላው የፌስቡክ ተሳታፊ ምስክር ሙሉቀን ይባላሉ፦ «እኔን የገጠመኝን ላካፍላችሁ» ሲሉም ጽሑፋቸውን ይጀምራሉ። «እኔ የገጠመኝኝ ነገር ላካፍላችሁ ከዛሬ አንድ ወር በፊት ነገሩ ሲጀምር እኔ የጤና ባለሙያ ነኝ በአንድ ደርጅት ዉስጥ ተቀጥሬ በሕክምና አገልግሎት እስጣለሁኝ እናም አንድ ደንበኛየ መቶ የተፈጠረዉን አጋጣሚ ነገረኝ ወሲብ ሳደርግ በአጋጣሚ ኮንደሙ ፈነዳ እናም ከጨረሰን በኀላ ልጅቷ ታወቃት በዚሁ በተፈጠረዉ ነገር በእጀጉ አዝኛለሁ ምክንያቱም ልጅቷ የቡና ቤት ሊዲ ነች ስለዚ hiv የምክር አገልግሎት ስጠኝ ብሎ መቷል ስለዚህ የደረሰዉ አደጋ በጣም ከባድ ነዉ የገንዘቡ ኪሳራ ቀላል ነዉ የህይወቱ አደጋ በምን ይተካል» ሲሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት አጠይቀዋል።

Kondome in unterschiedlichen Farben
ምስል picture-alliance/dpa/S. Schönberger

«እስከዛሬ ለተፈጠረው ምን ያኽል እርግጠኞች ነን?» ያሉት ደግሞ እንግዳህ ጉት ናቸው። ተጨማሪ የፌስቡክ አስተያየቶችን ወደ በኋላ ላይ እናሰማችኋለን። አቶ ፍትኅ ቶላ የዲኬቲ ኢትዮጵያ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናቸው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኮንዶሞች ጥራታቸውን አልጠበቁም ተብሎ እንዲወገዱ መታዘዙን ተከትሎ በተጠቃሚዎች ዘንድ ብዥታ መፈጠሩን ተናግረዋል።

ልቅ በሆነ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ የአባላዘር በሽታዎችን፣ ኤች አይ ቪን እና ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል ወጣቶች በተለይ በከተማ አካባቢ ኮንዶም በስፋት መጠቀማቸው ከበፊቱ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

ሌላው በስልክ ያነጋገርነው ወጣት ሱራፌል ኃይሉ ይባላል። ነዋሪነቱ ምሥራቅ ሐረርጌ ደደር የምትባል ከተማ ውስጥ ነው። የሲቪል ምሕንድስና የአራተኛ ዓመት ተማሪ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኮንዶሞች ኢትዮጵያ ውስጥ ከጥራት ማነስ የተነሳ እንደሚወገዱ መነገሩን ተከትሎ ከወጣት ጓደኞቹ ጋር በጉዳዩ ላይ እንደተነጋገሩበት ገልጦልናል። ሱራፌል ከምንም በፊት መቅደም ያለበት መታቀብ ነው ይላል።

በሁሉም ሃይማኖቶች ተከታታይ ትምህርት መስጠት እንዲሁም ወጣቱ ባሕሉን እና ትውፊቱን እንዲጠበቅ ማድረግ ያስፈልጋል ሲል አክሏል ወጣት ሱራፌል። ጥላሁን ጥላሁን ጥላሁን የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ «ጠያቂ ግን አለ እንዴ??» ሲሉ በማጠየቅ ይጀምራሉ፤ በመቀጠለም፥ «መንግስት እኮ ነው ተጠየቂ። ምክንያት የዜጎች ደህንነት በጣም ሊያሳስበው ይገባ ነበር። እናማ ሲጀመር ጥራት እንደሌለው እየታወቀ ለምን ተገዛ? አሁን ግዢ ከተፈፀመ በጛላ ቢወራ ዋጋ የለውም። ይህ የሚያሳየው ከውጭ ወደ ሀገር ቤት በሚገቡ ነገሮች ላይ ቁጥጥሩ በጣም የላላ መሆኑን ነው።» ሲሉ አስተያየታቸውን ደምድመዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ