1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥቂት ስለ ዲዮክሲን

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 27 2003

ያለጥንቃቄ ፣ ሥጋና እንቁላል በገፍ የማምረት ሂደት፣ በጤንነት ላይ የሚያስከትለው አደገኛነት እስከምን ድረስ ሊሆን እንደሚችል፥ ሰሞኑን የጀርመንን ኅብረተሰብ ከድንጋጤ ጋር በማነጋገር ላይ ያለ ዐቢይ ጉዳይ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/Qnwu
ጀርመን ውስጥ ፣ የምግብ ዓይነቶች፣ ዲዮክሲን አላባቸው፤ የለባቸውም?-በቤተ-ሙከራ፣ሲፈተሹ---ምስል picture-alliance / dpa/dpaweb

ከሚቃጠል የቁሻሻ ክምርም ሆነ ከአንዳንድ የቅመማ አንዱስትሪ ዎች የሚገኘው መርዘኛ ንጥረ ነገርም ሆነ ጋዝ ዳዮክሲን ወይም ዲዮክሲን፣ በተመረዘ ምግብ ሳቢያ ፣ የሰዎችን ጤንነት ክፉኛ ሊያናጋ፣ እንደሚችል እንደ አዲስ ጉዳይ በሰፊው በመነገር ላይ ነው። ዲዮክሲን እጅግ አደገኛውን በሽታ፣ ነቀርሳን(ካንሠር)ን ጭምር ሊያስከትል የሚችል፣ ነፍሰጡሮችንም የሚያስወርድ መሆኑ የተረጋገጠለት ነው።

ጤናይስጥልኝ እንደምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ፤ ቅንብራችን ፣ በአጭሩ ስለመርዛኛው ቅመም (ዲዮክሲን)አንድ አጭር ዘገባ ካቀረብን በኋላ፣ በ 2010 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት ያጋጠሙትን የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ክንዋኔዎች በተመለከተ፣ ታኅሳስ 13 ቀን 2003 ዓ ም ካሠራጨነው ከፊሉን በድጋሚ እናቀርባለን።

በተባበሩት መንግሥትት ድርጅት ፣ የሥነ ቅመማ መታሰቢያ ዘመን በተባለው በአዲሱ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ፣ 2011 ፣ ፍቱን ስለሆነ የሥነ -ቅመማ ተግባር ሳይሆን ስለመርዘኛ ቅመም( ዲዮክሲን )አደጋ በሰፊው መነገር መጀመሩ ፣ ለቀሪዎቹ 11 ወራት መጥፎ ገድ እንደማይሆን ተስፋ እናድርግ።

ስለዲዮክሲን አደገኛነት ጥቂት ሰፋ አድረገን ከማውሳታችን በፊት ፤ ራሱ ዲዮክሲን ከምን እንደሚገኝ እስቲ እንመልከት። ዲዮክሲን፣ የተቀጠሉ ነገሮች፣ የሃይድሮጂን፣ የኦክስጂንና የክሎሪን ቅልቅል የሆነ መርዘኛ ቅመም ነው። የሥነ ቅመማ መለያውም፣ --ካርበን 12 ፣ ሃይድሮጂን 4፣ ኦክስጂን 2 እና ክሎሪን 4 ፣ እነዚህን ሁሉ አጠቃሎ የሚይዝ የንጥረ-ነገሮች ቅልቅል ነው። ዲዮክሲንን ፣ ለምሳሌ ያህል፣ የቆሻሻ ክምር ሲቃጠል፤ ብረታ-ብረት ከሚያቀልጡ፣ የግድግዳ ቀለም ከሚያመርቱም ሆነ ከድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ቤንዚን ከሚያጣሩ ኢንዱስትሪዎች ማግኘት ይቻላል። በተፈጥሮም ፣ ከእሳተ ገሞራ ፍንዳታና ሰደድ እሳት ከሚያስነሳው የደንም ሆነ ቁጥቋጦ ቃጠሎም ሊገኝ ይችላል። በአጠቃላይ 200 ያህል የተለያዩ የዲዮክሲን ዓይነቶች የሚገኙ ሲሆን እንደሚታወቀው ሽታም ቀለምም የላቸውም። ከእነዚህ ሁሉ እጅግ አደገኞች የሚባሉት 17 ናቸው። ዲዮክሲን ጥቅም አለው ተብሎ የሚቀመም አይደለም። ዲዮክሲን በውሃ አይሟማም። ዘይትን በመሰለ ቅባት ውስጥ ይገኛልና!።

ታዲያ ለሰዎች ጠንቅ የሚሆነው፣ ለእርድ የሚውሉ ከብቶች፣ በጎች፣ አሳማዎችና ዶሮዎች እንዲመገቡት በአንዱስትሪ በሚሰናዳ መኖ ነው። ዲዮክሲን ፣ በአካል ውስጥ በሚገኝ ቅባት (ጮማ) ወይም በእንቁላል አስኳል ውስጥና በወተት ቅባት ክፍል ነው እየተጠራቀመ የሚገኘው። ሰዎች 95 ከመቶ፣ ዲዮክሲን በሰውነታቸው ውስጥ ሊገኝ የሚችለው፤ አሣ፤ ሥጋና ወተትና የወተት ውጤቶችን በመመገብ ነው። አየር በመተንፈስ ወደ ሰውነት የሚገባው የዲዮክሲን ጋዝ መጠን እጅግ አነስተኛ ነው። ዲዮክሲን ፣ አንድ ጊዜ ሰውነት ውስጥ ከገባ ደግሞ ማስወገዱ እጅግ ከባድ ነው። በተለይ እጅግ መርዛማ የሚሰኘውን የዲዮክሲን ዓይነት (2,3,7,8 TCDD)-ቴትራ ክሎሮ ዳይቤንዞ ዳዮክሲን )ን ሙሉ-በሙሉ ከሰውንት ውስጥ ለማስወገድ 7 ዓመት ያህል ሊወስድ ይችላል። ከዚህ መለስተኛ የተባለው መርዘኛ ዲዮክሲን፣( 2,3,4,7,8 ፔንታክሎሮዳይቤንዞፈራን) የተሰኘው ደግሞ፣ ከፊሉን ብቻ ከሰውነት ለማስወገድ 20 ዓመት እንደሚፈጅ ነው ጠበብት የሚናገሩት። የዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅት(WHO) ከ 14 ዓመት ገደማ በፊት በይፋ ባስታወቀው መሠረት ፣ 2,3,7,8, TCDD በሰዎች አካል ውስጥ ከተገኘ አደገኛውን የነቀርሳ በሽታ ሊያስከትል ይችላል። ሌሎቹ የዲዮክሲን ዓይነቶችም ተማሳሳይ ሳንክ ሳይፈጥሩ እንደማይቀሩ ጥርጣሬ አለ። በመሆኑም የጀርመን የምግብ ቁጥጥር ነክ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ወ/ሮ ክሪስቲያነ ግሮስ ፣ በያመቱ ይህን መሰል የቅሌት ተግባር ስለመፈጸሙ መስማት የሚያናድድ መሆኑን በመጠቆም እንዲህ ብለዋል።

«በያመቱ ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ፣ ዲዮክሲን በምግብ ውስጥ ፣ በእንስሳት መኖ ስለመገኘቱ ሲዘገብ እንሰማለን። እዚህ ላይ በእውነት መጠየቅ የሚገባን እንዴት ትክክለኛ እርምጃ አይወሰድም? ብለን ነው። በዚህ ረገድ ሊወሰድ የሚችለው እርምጃ ደግሞ ይህን ያክል የተወሳሰበ ሊሆን ባልቻለ ነበር። ሊቀርብ የሚገባው ደንብ፣ የእንስሳት መኖ የሚያዘጋጁ ክፍሎች ፣ መጠኑን ያለፈ ፤ አንዳች ዲዮክሲን በመኖ ውስጥ እንዳይጨምሩ የሚከለክል መሆን አለበት። »

(ሙዚቃ)

(የታኅሳስ 13 ቀን 2003 ዝግጅት በከፊል)

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ