1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥንታዊቷ የቲምቡክቱ ከተማ ጊዚያዊ ሁኔታ

ሰኞ፣ ግንቦት 5 2005

በተራቸው ተባራሪዎች ከሆኑ ሶስት ወራት አልፏል። ጂሐዲስቶቹ ቲምቡክቱን ለ10 ወራት ግድም ተቆጣጥረው የከረረ አመለካከታቸውን ነዋሪው ላይ በኃይል በመጫን አካባቢውን ስጋት፣ፍርሃትና አደጋ የወረረው ቃጣና አድርገውት ቆይተውም ነበር።

https://p.dw.com/p/18WzM
ምስል DW/K. Gänsler
Versorgung in Mali für den 8. Mai 2013
ምስል DW/K. Gänsler

ይሁንና ስጋት ፈጣሪዎቹ ኃይላት ከተወገዱ ሰንበትበት ቢልም ቅሉ በዛች ታሪካዊ ከተማ ግን የዕለት ተዕለት ኑሮው ገና የተረጋጋ አይመስልም።

በቲምቡክቱ ገበያ እንስት ቸርቻሪዎች እያጨበጨቡ ነው። ጭብጨባቸውም ጥብቅ እስልምናን የሚያራምደው አንሳር ዲን የተሰኘው ቡድን ከተማዋን መቆጣጠሩ ካከተመለት በኃላ ይህችን የበረሃ ጥግ ደፍረው ለመርገጥ ብቅ ላሉት እንግዶቻቸው ነው። ወርሃ ጥር መገባደጃው እስኪዳረስ አካባቢው ህይወት አልባ፣ የሙት ከተማ ይመስል ረጭ ብሎ ከርሟል። በተለይ ቲምቡክቱ ከሌላው አካባቢ ተነጥላ አደገኛ ቃጣና በመሆን ቆይታም ነበር። የከተማዋ ከንቲባ ሐለ ኦስማነ በትውስታ እንዲህ ወደኋላ ይመለሳሉ።

«ለራሳችን እንዲህ ስንል ጠይቀን ነበር። በእርግጥ ወዳጆች ይኖሩን ይሆን? ቲምቡክቱስ ዳግም የዘመናዊው ዓለም አካል ትሆን ይሆን? ለአስር ወራት ያህል ማንም ስለእኛ ያሰበ አልነበረም።»

Versorgung in Mali für den 8. Mai 2013
ምስል DW/K. Gänsler

ከተማዋ እንደቀድሞው ሁሉ አገር ጎብኚዎች ዝር ሳይሉባት ረዥም ጊዜያትን አስቆጥራ ሰንብታለች። በእርግጥ በጀሐዲስቶቹ ላይ የፈረንሣይ ጦር የከፈተው ጥቃት በጥር ወር መገባደጃ ላይ ከተጠናቀቀበት ጊዜ አንስቶ ቲምቡክቱ በርካታ ጋዜጠኞችን መሳቧ ባይቀርም ማለት ነው። የረድኤት ሰራተኞችም ቢሆኑ ቀስ በቀስ ተግባራቸውን በከተማው ውስጥ ማከናወን ጀምረዋል። እንዲያም ሆኖ ግን የዕለት ተዕለት ኑሮው ወደ ቀድሞው መስመሩ ሳይመለስ ረዥም ጊዜያትን ማስቆጠሩ አልቀረም። እንግዶችን ለመጀመሪያ ጊዜ መመልከታቸው ያስደነቃቸው አንዲት ቸርቻሪ ስቃያቸውን እንዲህ ይገልፃሉ።

«ለነገሩ አንድ ዓሣ የምሸጠው በ250 ፍራንክ ነው። ሆኖም ደምበኞች ተከራክረው ወደ 150 ፍራንክ ያወርዱብኛል። እዚህ ከወረራው በኋላ አንዳችም የተቀየረ ነገር የለም። የተቀየረ ነገር አለ የሚል ካለ እሱ ውሸታም ነው።ውሸታም ነው። ማንንም መጠየቅ ይቻላል።»

የከተማዋ ከንቲባ ሐለ ኦስማነም በእዚያ ይማማሉ። ከንቲባው እንግዶችን የሚቀበሉት ከገበያው ብዙም በማይርቀው ማዘጋጃ ቤት ውስጥ ነው። በክፍሉ መሀከል የተወሰኑ ወንበሮች ተደርድረዋል። ሆኖም መብራትም ሆነ ኮምፒውተር አለያም ማተሚያ የሚባል ነገር የለም። የቲምቡክቱ አስተዳዳሪ የሚኖሩት አንድ ሆቴል ውስጥ ሲሆን፤ የሚያስተዳድሩትም ከእዚያው ከሆቴሉ ሆነው ነው። የፖሊስ ጣቢያው ሰው አልባ ነው፣ መስኮቶቹ ተሰባብረዋል፣ በሮቹ ተገነጣጥለዋል። ለከንቲባ ሐለ ኦስማነ የከተማዋ አስተዳደር በከፋ ሁናቴ ላይ ከመገኘቱም በላይ ነዋሪው የኑሮ መሠረታዊ ነገሮችን አጥቶ እንደሚቸገር ነው የሚሰማቸው።

Mali Soldaten
ምስል picture-alliance/AP Photo

«ከነዋሪው 80 በመቶው ሠራተኛ ነው። ጠዋት ይሰራል ከሠዓት ደመወዙን ይቀበልና በእዚያ ቤተሰቡን ይመግባል። የተቀረው ቱሪዝም ነው። ጭራሽ አክትሞለታል፤ ስለእሱ ባናወራ ይሻለናል። ሆቴሎቹ ተከርችመዋል። እዚህ ቲምቡክቱ ውስጥ ይህ ነው የሚባል አንዳችም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የለም።»

በቲምቡክቱ ዕምብርት በምትገኘው ሳንኮሬ በተሰኘችው የከተማው አንድ ክፍል በጀርመንኛው Welthungerhilfe የተሰኘው የጀርመን ርዳታ ሰጭ ድርጅት ከአንድ አገር በቀል የዕርዳታ ተቋም ጋር በመተባበር ሩዝ በማደል ላይ ነው። ትርምሱ ለጉድ ነው። እንዲህ አናት በሚበሳው ጠራራ ፀሐይ ላይ የተሰጡት በርካታ ሴቶችና ወንዶች 50 ኪሎ ሩዝ ለማግኘት ነው ገና ከማለዳው አንስቶ ሰልፍ የያዙት።

ሩዝ ለመቀበል ከተሰለፉት ነዋሪዎች መካከል አባ ማይጋ ይገኝበታል። ከቡርኪናፋሶና ከመንግስት ተውጣጥተው በተዋቀሩት ወታደሮች ብዙም ዕምነት የለውም። ለእሱ የፈረንሳይ ወታደሮች ቢቆዩለት ነው ምርጫው፤ በእርግጥ የፈረንሳይ ወታደሮች ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኛዎቹ ከቲምቡክቱ ለቀዋል። አባ ማይጋ ቀሪዎቹም ወታደሮች ቢሆኑ ቢቆዩ ምርጫው ነው።

«እዚህ አሁን ሁናቴው አደገኛ ባይሆንም ፈጥነው እንዲሄዱ አንሻም። እንደእዚያ ከሆነ አደገኛ ነው የሚሆነው። ቦታውን የተቆጣጠሩት የፈረንሳይ ወታደሮች ናቸው። እጅግ ወሳኝ የሆኑ ነገሮች አሏቸው። በፍጥነት እንዲወጡ አንፈልግም። »

በቲምቡክቱ ስለ ድህነቱ ባይነገር ይሻላል። ገንዘብ በቀላሉ ማግኘት አይቻልም። በቂ ስራ ያለመኖሩ ብቻም አይደለም ህይወት በቲምቡክቱ አስቸጋሪ እንዲሆን ያደረገው። የደኅንነት ስጋትም አለ። በእርግጥ በአሁኑ ወቅት በቲምቡክቱ ጂሐዲስቶች የሉም ተብሎ ቢታሰብም ባለፉት ሳምንታት ሁለት ፍንዳታዎች ተከስተዋል። ከከተማዋ ወጣ ብለው የሚገኙት መንደሮች አሁንም ድረስ በስጋት እንደተዋጡ ነው። የርዳታ አቅርቦት እንኳን በቅጡ ሊከናወን የቻለው ጦሩ ስላለ ነው። የማሊ ወታደሮች በጭነት መኪናዎቻቸው ላይ ሆነው ሳያሰልሱ ከተማዋ ውስጥ ይመላለሳሉ። ልክ እንደ አባ ማይጋ ሁሉ አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች የፈረንሳይ ወታደሮች በቲምቡክቱ ለረዥም ጊዜ እንዲቆዩ ምርጫቸው ይመስላል። ታዲያ የፈረንሳይ ወታደሮች በትክክለኛው ለምን ያህል ጊዜ በቲምቡክቱ ጥበቃቻው ይቆያሉ? የሚታወቅ ነገር የለም።

በለንደኑ የሶማሊያ ጉባኤ ለጋሽ አገራት ለሶማሊያ የገቡት ቃልና ጥንታዊቷ ቲምቡክቱን ያስቃኘው የትኩረት በአፍሪቃ መሰናዶዋችን በእዚህ ይጠናቀቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

መስፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ