1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥንታዊዉ የጀርመን ገዳም በዓለም ቅርስነት

ሐሙስ፣ ሰኔ 19 2006

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በ«UNESCO» ዘጠኝ መካነ ቅርሶችን እና አንድ የማይዳሰስ ቅርስን፤ በአጠቃላይ አስር ታሪካዊ ቅርሶችን አስመዝግባለች። ጀርመን ደግሞ ከስፔን እና ከጣልያን ለጥቃ 39 ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት በማስመዝገብ ሶስተኛዋ የዓለም ሀገር ናት።

https://p.dw.com/p/1CQMP
Schloss Kloster Corvey an der Weser
ምስል Kulturkreis Höxter-Corvey

ትናንት የተጠናቀቀዉ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት የ«UNESCO» 38 ኛዉ ዓመታዊ ስብሰባ በጀርመን በዘጠነኛዉ ክፍለ ዘመን የተገነባን አንድ ገዳም በዓለም ቅርስነት መዝግቦአል። ዘንድሮ ዶሃ ቃጣር ላይ በነበረዉ የ 10 ቀናት ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያም ተካፋይ ነበረች። በለቱ ዝግጅታችን በዓለም ቅርስነት የተመዘገበዉን የጀርመናዉያኑን ጥንታዊ ገዳም እየቃኘን፤ ዘንድሮ ዶሃ ቃጣር ላይ በተደረገዉ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ ለዓለም ቅርስነት መዝገብ ይዛ የቀረበችዉን ጥንታዊ የታሪክ መገለጫዎች እንዳስሳለን ።

Galerie - Kloster Corvey
ምስል Kulturkreis Höxter-Corvey gGmbH

ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ በተመ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት የዓለም ቅርስ መዝገብ ዉስጥ የሰፈረዉ በጀርመን ኖርዝ ራይን ዊስትፋልያ ግዛት የሚገኘዉ ጥንታዊዉ ገዳም፤ በመንግስታቱ ድርጅት የዓለም ቅርስ መዝገብ እንዲካተት ጥያቄ ከቀረበ 15 ዓመት በኋላ ለዓለም ቅርስ መዝገብ መብቃቱ ተገልፆአል። እንድያም ሆኖ የጀርመኑ ኮርቫይ ጥንታዊ ገዳም ታሪካዊ ስለመሆኑ «UNESCO»ን ለማሳመን የጀርመን ቅርስ ጥበቃ ቢሮ፤ ወደ 700 ገጾችን የያዘ ዝርዝር ታሪክን ጽፎ ለድርጅቱ በጎርጎረሳዊዉ 2012 ዓ,ም እንዳቀረበም ተነግሮአል። በዓለም ቅርስ መዝገብ የተመዘገበዉ የጀርመኑ «ኮርቫይ» ጥንታዊ ገዳም፤ በተለይ የሚታወቀዉ፤ ወደ ምዕራብ ባዘነበለዉና ከሸክላ ጡብ በዘጠኘኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን በተከነገባዉ ባለሁለት አስገራሚ ምሶሶ የካሮሊኖች ህንፃ ነዉ። በመካከለኛዉ ክፍለ ዘመን ንግሰታና መሳፍንቶች ከቦታ ወደ ቦታ ሲዘዋወሩ በማደርያነት ይጠቀሙበት እንደነበርም ተዘግቦአል።

በ 822 ዓ,ም በታላቁ ንጉስ ካርል ልጅ በሉድቪግ የተመሰረተዉ ይህ ገዳም የእዉቀትና የኃይማኖት ማዕከልም ነበር። በ1792 ዓ,ም ገዳሙ የመሳፍንቶቹ የሀገርና የኃይማኖት አስተዳደር ዋና ጽ/ቤት በመሆን ማገልገል ጀመረ። ዛሬ ይህ ህንፃ በግለሰብ ንብረትነት ሥር እንደሚገኝ ነዉ የተገለፀዉ። የሕንፃዉ በር ለጎብኝዎች ለመጀመርያ ግዜ መከፈት የጀመረዉ ደግሞ በጎርጎረሳዊዉ 1950 ዓ,ም ነዉ። በዚሁ በመሳፍንቶቹ ቤተ - መጻሕፍት ዉስጥ 74 ሽ ጥርዝ መጻሕፍት እንዲሁም፤ የመሳፍንቶቹ የእንግዳ መቀበያ እና የንጉሠ ነገስቱ አዳራሽ በዓመት ወደ 100ሽ ጎብኝዎችን ወደ ስፍራዉ ይጋብዛል። አሁን ይህ ጥንታዊ ገዳም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በ«UNESCO» የቅርስ መዝገብ ዉስጥ መስፈሩ የጎብኝዎችን ቁጥር ይበልጥ ከፍ ሊያደርገዉ እንደሚችልም ይታመናል። በመሆኑም ለአካባቢዉ የኤኮነሚ እድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረዉ ከወዲሁ ተገምቶአል።

Galerie - Kloster Corvey Arbeitszimmer Hoffmann von Fallerslebens
ምስል Kulturkreis Höxter-Corvey gGmbH

ዶሃ ቃጣር ላይ የተሰበሰቡት የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት የ«UNESCO» ኮሚቴዎች፤ በጀርመን ኖርዝ ራይን ዊስት ፋልያ ግዛት፤ ዌሰር ወንዝ አቅራብያ ፤ ረባዳ ሥፍራ ላይ የሚገኘዉን ማራኪና ጥንታዊ ገዳም በቅርስነት መመዝገቡን ይፋ ያደረገዉ ባለፈዉ ቅዳሜ ከቀትር በኃላ ነበር። ይህ ሰናይ ዜና በተሰማ ግዜ በተለይ አካባዉ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ደስታቸዉ ገልፀዋል። በገዳሙ የቤተ-መዘክሩ ዋና ተጠሪ ክላዉድያ ኮነራድም፤ ደስታቸዉን እንዲህ ነበር የገለፁት፤

« አንድ በሃሳብ እና በጉጉት ስንጠብቀዉ የነበረ ነገር ነዉ መፍትሄን ያገኘዉ፤ ይህን ታሪካዊ ህንፃ በቅርስነት ለማስመዝገብ ያደረግነዉ ከፍተኛ ትግል ዉጤት በማምጣቱ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ»

ዶሃ ቃጣር ላይ ትናንት በተጠናቀቀዉ በ38 ኛዉ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በ«UNESCO» ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያም ተካፋይ ነበረች። በዘንድሮ ስብሰባ ኢትዮጵያ መዝገቡ ላይ አለመካተትዋን የገለፁልን፤ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን፤ የህዝብና ዓለማቀፍ ግንኙነት ዳሪክቶሪት ረዳት ሃላፊ፤ አቶ ፈንታ በየነ፤ እስካሁን በአፍሪቃ ቅርስን በማስመዝገብ ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ መሆንዋን ገልጸዋል፤

Schloss Corvey bei Hoexter
ምስል imago/imagebroker

« ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በ«UNESCO» ዘጠኝ መካነ ቅርሶችን እና አንድ የማይዳሰስ ቅርስ በአጠቃላይ አስር ታሪካዊ ቅርስን አስመዝግባለች»

ዶሃ ቃጠር ላይ ለአስር ቀናት የዘለቀዉና ትናንት ረቡዕ የተጠናቀቀዉ የመንግስታቱ ድርጅት የዓለም የቅርስ ጥበቃ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ፤ በቅርስነት እንዲመዘገቡ ከተለያዩ የዓለም ሃገራት ታሪክና ባህልን የሚያመላክቱ ነገሮች በዝርዝር ቀርበዉ፤ ባጠቃላይ 40 የተለያዩ ጥንታዊ ታሪክን የሚያመላክቱ ነገሮች በእጩነት በመዝገቡ ለመመዝገብ መቅረባቸዉ ተመልክቶአል። ዘንድሮ በዓለም ቅርስ መዝገብ ከተመዘገቡ ነገሮች መካከል የኔዘርላንዱ እድሜ ጠገብ የፋብሪካ ህንፃ፤ ቶሞይካ በመባል የሚታወቀዉ ታሪካዊዉ የጃፓን የሃር ክር ፋብሪካ እንዲሁም በኢራቅ አርቢል ከተማ የሚገኘዉ ጥንታዊ የመሳፍንቶች ምሽግ ይገኝበታል።

«ኮርቫይ» በመባል በሚታወቀዉ ጥንታዊ የጀርመን ገዳም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት የቅርስ መዝገብ ዉስጥ መካተቱን ተከትሎ የፊታችን እሁድ በዚሁ ገዳም ዉስጥ በልዩ የቤተክርስትያን ደወል ሥነ-ስርዓት የታጀበ የፀሎት እንደሚደረግ ተነግሮአል። በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የህዝብና ዓለማቀፍ ግንኙነት ዳሪክቶሪት ረዳት ሃላፊ አቶ ፈንታ በየነ፤ በበኩላቸዉ የሲዳማ የዘመን መለወጫ፤ በሀሪሪ ህዝቦች ዘንድ የሚከበረዉ ባህላዊ በዓል፤ የአሸንድዪ በዓል ፤ የጥምቀት በዓል፤ የገዳ አከባበር ለዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ጥረት እየተደረገ ነዉ»

ከጎርጎረሳዉያኑ 1972 ዓ,ም ጀምሮ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት «UNESCO» በተለያዩ የዓለም ሀገሮች የሚገኙ ታሪካዊ ነገሮችን በዓለም የቅርስነት መመዝገብ መጀመሩ ይታወቃል። በአሁኑ ግዜ በዓለም ላይ ከሚገኙ 160 ሀገራት 981 መካነ ቅርችና፤ የማይዳሰሱ ታሪካዊ ቅርሶች በዓለም ቅርስ መዝገብ ሰፍረዉ ይገኛሉ። ጀርመን በዚህ የዓለም የታሪክ መዝገብ 39 ነገሮችን በማስመዝገብ ከስፔን እና ኢጣልያ ቀጥላ በመዝገቡ በርካታ ነገሮችን ያስመዘገበች ሶስተኛዋ የዓለም ሀገር ሆናለች። ኢትዮጵያ በዚህ መዝገብ ዘጠኝ መካነ ቅርስን አንድ የማይዳሰስ ቅርስን በአጠቃላይ አስር ታሪካዊ ቅርስን ማስመዝገብዋ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የህዝብና ዓለማቀፍ ግንኙነት ዳሪክቶሪት ረዳት ሃላፊ አቶ ፈንታ በየነ፤ በዓለማቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገቡ ጥናት ላይ ከሚገኘዉ የኢትዮጵያ መካነ ቅርሶች መካከል ደግሞ ይላሉ፤

« አንደኛ የጌዶ ባህላዊ እና መልካ ምድራዊ ቅርስ ሁለተኛ፤ የሶፎመር ዋሻ፤ መልካ ቁንጥሪን የመሳሰሉ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በ«UNESCO» መዝገብ እንዲሰፍሩ በግዝያዊ መዝገብ ጥናት እየተደረገባቸዉ ለመመዝገብ ተራቸዉን የሚጠብቁ ናቸዉ።

Schloss Kloster Corvey an der Weser
ምስል Kulturkreis Höxter-Corvey

ታሪካዊ ቦታዎችን ባህላዊ የህዝብ በአላትን በዓለማቀፉ የቅርስ ማህደር ማስመዝገቡ ምን ፋይዳ ይኖረዉ ይሆን? ኢትዮጵያ አስር ቅርሶችን በመንግስታቱ ድርጅት ማስመዝገቧ ምን ጥቅም ሰጣት፤ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የህዝብና ዓለማቀፍ ግንኙነት ዳሪክቶሪት ረዳት ሃላፊ አቶ ፈንታ በየነ፤« በአጠቃላይ ቅርሶቻችንን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በ«UNESCO» መመዝገባቸዉ በማህበራዊና በኢኮኖሚ አኳያ ብዙ ጥቅም አለዉ ። በሌላ በኩል መካነ ቅርሶቹ ለሚቀጥለዉ ትዉልድ እንዲተላለፍ እደሳም እንዲደረግለት ይዳርጋል፤ በተጨሪ ወደ ሀገር ቤት ጎብኝዎችን በመሳብ አኳያ ትልቅ ሚናን ይጫወታል።

ስለ ባህል መድረክ ዝግጅት ገንቢ አስተያየትም ሆነ ሂስ ካላችሁ በተለመዱት አድርሻዎቻችን ላኩልን፤ ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን ይከታተሉ!

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ