1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፀረ ፍልሰት ትግል

ቅዳሜ፣ የካቲት 18 2009

እጎአ በ2016 ዓም በሜድትሬንየን ባህር በኩል ወደ አውሮጳ ከመጡት መካከል ወደ 10,000 የሚጠጉት የሴኔጋል ዜጎች ናቸው። ሴኔጋል በአፍሪቃ ስደተኞች በብዛት ከሚሰደዱባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት።

https://p.dw.com/p/2YE5H
Symbolbild Flüchtlingsboot Mittelmeer
ምስል picture-alliance/dpa/AP/S. Diab

senegal - MP3-Stereo

በመሆኑም፣ ጀርመን እና የአውሮጳ ህብረት ለሴኔጋል ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ ብዙ ሚልዮን ገንዘብ በሚመደብላቸው የልማት ፕሮዤዎች አማካኝነት የስደት እና የፍልሰት መንስዔን ለመታገል በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። ይህ  ጥረታቸው በሴኔጋል ፖለቲከኞችም ላይ ጫና አሳርፏል።
    
ተስፋ መቁረጥ ምን ማለት እንደሆነ ወይም ሁኔታዎች እንደሚፈለገው ሳይሻሻሉ ሲቀሩ የሚፈጠረውን የባዶነት ስሜት እና የተሻለ ኑሮ ናፍቆትን ሴኔጋላዊው ማሴር ጌይ በሚገባ ያውቀዋል። በ30 ዓመት አጋማሽ ላይ የሚገኘው እና በመዲናይቱ ዳካር የሚኖረው  ማሴር ሙያው  ብረት ቀጥቃጭነት ነው። ከብዙ ዓመታት በፊት በተለይ ኃይል ቆጣቢ አነስተኛ የምግብ ማብሰያ ምድጃ በማምረት ስራ ላይ ተሰማርቶ ነበር። ሙያውን ተክኖበታል። ይሁን እንጂ፣ ከብዙ ጊዜ ወዲህ ገበያው በመቀዛቀዙ የሰራቸውን ምድጃዎች መሸጥ አልቻለም። እና ሁኔታው እጅግ እየከፋ በመሄዱ ከአስር ዓመት በፊት ውሳኔ መውሰድ እንደነበረበት ይናገራል።     
«በዚያን ጊዜ ወደ አውሮጳ ለመሄድ ወሰንኩ። ሁለት ጊዜ ወደ ስጳኝ ለመድረስ ሞክሬ ነበር። ይሁንና፣ የመጀመሪያውም  ሁለተኛውም ሙከራዬ ከሽፏል። የተጓዝንበት ጀልባ ሞሪታንያ ባህር ጠረፋ አቅራቢያ የመስመጥ አደጋ አጋጠመው፤ ያኔ የሆኑ ሰዎች ደርሰው ከሞት አትርፈውናል።»
በዚሁ አደጋ አብረውት ይጓዙ የነበሩ አንዳንዶቹ ተሳፋሪዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። እሱ እድለኛ  ሆኖ ተርፏል። እንዳጋጣሚ በሴኔጋል ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎችን ለማስፋፋት ማሴር ያደረገውን ጥረት የሰሙ  በዳካር የሚገኘው የጀርመናውያኑ ዓለም አቀፍ ድርጅት፣ «ጂ አይ ዜድ» የልማት ርዳታ ሰራተኞች  ለማሴር ተቋሙን ማቋቁም የሚያስችለውን የምክር እና ብድር ርዳታ ሰጥተውት፣ ማሴር ዛሬ  አነስተኛ ተቋም ከፍቶ 21 ሰራተኞችን ማስተዳደር ችሏል።

Senegalesen hoffen auf Zukunft in Europa
ምስል picture-alliance/ dpa

«እነዚህ ዓይነት ጥረቶች ወጣቶች በሀገሮቻቸው በመቆየት፣ በዚያው ስራ እየሰሩ ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን እንዲረዱ ያበረታታሉ።   ከዚህ  ወደ አውጳ የሚሰደዱት ወጣቶች በዚያ መደበኛ የሆነ ስራ የላቸውም።  እኔ  ያኔ ለመሰደድ በሞከርኩበት ጊዜ፣  የወደፊት እድሌን በተመለከተ ይህ ነው የሚባል ራዕይ አልነበረኝም።  እና  ወጣቶች ስራ የሚያገኙ ከሆነ በሀገሮቻቸው እንደሚቆዩ እርግጠኛ ነኝ። »
 በዳካር የ«ጂ አይ ዜድ» ቢሮ ኃላፊ ፍሪድሪከ ፎን ሽቲግሊትስ ድርጅታቸው ለማሴር ያደረገው ርዳታ ባስገኘው ውጤት ረክተዋል። እርግጥ፣ ፍሪድሪከ ፎን ሽቲግሊትስ እንደሚሉት፣ የምግብ ምድጃ ስራ ሴኔጋል ውስጥ አዲስ አይደለም። ይሁንና፣ ለወጣቶች በገዛ ሀገራቸው የተሻለ የወደፊት እድል መፍጠር የሚያስችል ይህን የመሰለው ፕሮዤ በብዙዎች ዘንድ ልዩ አመለካከት ማትረፉን ገልጸዋል።  የጀርመናውያኑ የልማት ትብብር ፖሊሲ በወቅቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ያለው መመሪያ የስደትን መንስዔ መታገል የሚሰኘው መሆኑን ነው ፎን ሽቲግሊትስ ያስረዱት። «በሴኔጋል ስኬታማ መሆን » የሚለው በጀርመን መንግሥት ጥያቄ መሰረት የተነቃቃው የ«ጂ አይ ዜድ» መርሀግብርም የፊታችን ሚያዝያ ይጀመራል ብለዋል።    

« ጉዳዩ፣  ወጣቶች የሚተማመኑበት ደሞዝ እና ስራ መፍጠር መቻልን   ይመለከታል። ማወቅ ያለብን፣  ከሴኔጋል ሕዝብ መካከል፣  ከ50 ከመቶ  የሚበልጠው በ19 ዓመት እና ከዚያ ባነሰ እድሜ ላይ የሚገኝ  ወጣት መሆኑን ነው።  በመሆኑም፣  የምናዘጋጃቸው ፕሮዤዎች  ሁሉ  ለወጣቶቹ   አስተማማኝ የወደፊት እድል የሚፈጥሩ ናቸው።»  
«ጂ አይ ዜድ» ከፀሀይ በሚገኘው ኃይል ርዳታም ወደ 10,000 ወጣት ለሚጠጉ የሴኔጋል ወጣቶች ስራ የመፍጠር እቅድ አለው። ይህንን እቅዱን በተግባር ለመተርጎምም ከመዲናይቱ ዳካር ራቅ ብለው በሚገኙት አካባቢዎች ጽሐፈት ቤቶቹን ለመከፈት ይፈልጋል። ምክንያቱም፣ የጀርመናውያኑ የልማት ተብብር ድርጅት እንደሚለው፣ ወደ አውሮጳ መፍለስ ከሚፈልጉት ወጣቶች  መካከል ብዙዎቹ የሚኖሩት በነዚህ አካባቢዎች ነው። በሁለት ገጾች የቀረበው የ«በሴኔጋል ስኬታማ መሆን » ፕሮዤ ማብራሪያ ፣  አዲስ ሙያ መጀመር የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠርን፣ በተለያዩ ትውልዶች መካከል ውይይት ማካሄድን እና ለውጥ የሚያመጡ ፕሮዤዎችን ባንድነት አጣምሮ የያያዘ ነው። ዓላማውም፣ ይላሉ ፍሪድሪክ ፎን ሽቲግሊትስ፣  ወጣቶችን ሀገራቸውን ለቀው እንዳይወጡ፣ በሀገራቸው አንድ ነገር የመፍጠር ወይም የመድረስ ራዕይ እንዲኖራቸው ለማድረግ ነው።    

Zentrale der Deutschen Gesellschaft für Internationale Zusammenarbeit GIZ Logo
ምስል picture-alliance/dpa

« እዚህ ወደፊት ምን ልሰራ እችላለሁ? የቤተሰቦቼን ፍላጎትስ እንዴት አሟላለሁ? የሚሉት ጥያቄዎች ለወጣቱ በጣም ወሳኝ ናቸው። ወደ ውጭ ሀገራት የሚፈልሱት ሁሉ የራሳቸው ራዕይ አላቸው፤ ሀገሩን ለቆ የሚወጣ ወጣት እንደ ጀግና ነው የሚታየው።  ታድያ ወጣቱ፣ ሳይሳካለት ቀርቶ ወደ ሀገሩ በሚመለስበት ጊዜ ግን፣  ትልቅ ውድቀት እና ችግር ነው የሚያጋጥመው። እና ተመላሾች በዚህ በሚደርስባቸው ክሽፈት እና ሀፍረት እንዳይጎዱ ለመርዳትም እየሰራን ነው። »
«በሴኔጋል ስኬታማ መሆን» የሚለው ፕሮዤ ጀርመንን ዘጠኝ ሚልዮን ዩሮ ያስወጣታል።  መርሀግብሩ ወጤታማ መሆኑ ከተረጋገጠ ፣ የገንዘቡን ድጋፍ ከፍ ለማድረግ የሚቻልበት መንገድ ሊኖር እንደሚችል ፎን ሽቲግሊትስ ገልጸዋል።
 ወጣቶች በብዛት በሚሰደዱባቸው አፍሪቃውያት ሀገራት ውስጥ ስራ የመፍጠሩን ፕሮዤ የጀመረችው ጀርመን ብቻ አይደለችም።  የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽንም የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል እና ደህና የስራ እድል መፍጠር የሚያስችሉ ሁለት ፕሮዤዎችን ይጀምራል። የነዚሁ ፕሮዤዎች ዓላማም ወጣቶችን በሀገራቸው ማቆየት ወይም እንዳይፈልሱ ማድረግ ነው።  የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ለነዚሁ ሁለት ፕሮዤዎች ካዘጋጀው የአፍሪቃ አስቸኳይ ርዳታ ፈንድ 60 ሚልዮን ዩሮ መድቧል። ጥያቄው ግን እቅዱ ይሰራል ወይ የሚለው ነው። ፈረንሳዊቷ የፍልሰት ተመራማሪ ሲልቪ ብረደሉ ፍልሰት በአካባቢው ባህሉ ውስጥ ስር የሰደደ መሆኑን ነው የሚያስረዱት።  
«የትኛውም ወጣት ዓለምን በራሱ መንገድ ለማወቅ እና የራሱን የወደፊት እድል ለመወሰን ይፈልጋል። ይህን   የጀብደኞች ፍልሰት ብዬ እጠራዋለሁ። በሌሎች ሀገራት የሚሆነውን ለማየት፣ ከቤተሰብ ነፃ ለመሆን፣ የራሱ ተሞክሮ እንዲኖረው እና ከተቻለ ተሻሽሎ ለመመለስ ይፈልጋል።  ወጣቱ የሚወጣው ራሱን ለማጠንከር እና ለማደግም ነው። »
ሲልቪ ብረደሉ ለልማት የሚሰጠው የገንዘብ ርዳታ ይህን አስተሳሳብ ይቀይራል ብለው አያምኑም። ብዙ የፍልሰት ተማራማሪዎችም ልክ እንደ ብረደሉ እቅዱ መስራቱን ተጠራጥረውታል። 
አንድ የተረጋገጠ ነገር ቢኖር፣ በፍልሰት ጉዳይ ላይ ከአውሮጳ ጋር ተባብሮ መስራቱ ለሴኔጋል ከያቅጣጫው ብዙ የልማት ርዳታ ማስገኘቱ ነው። 
ያም ቢሆን ግን የሴኔጋል ፕሬዚደንት ማኪ ሳል በሂደቱ ያን ያህል ደስተኛ አይደሉም። ምክንያቱም የልማቱ ርዳታ መሟላት ያለበት ቅድመ ግዴታንም አካቶ ይዟል። ኮሚሽኑ እቅዱን በማሳካቱ ረገድ የሴኔጋል ፕሬዚደንት ትብብርን ይፈልጋል። ሴኔጋል እንደሚፈለገው ካልተባባረች ኮሚሽኑ ርዳታውን ሊቀንስ እንደሚችል ዝቷል። ፕሬዚደንት ሳል ይህን ሊቀበሉት እንደማይችሉ ለ«ፍራንስ 24» በሰጡት ቀለ ምልልስ ላይ አስታውቀዋል። 

Macky Sall Präsident Senegal
ምስል picture alliance/augenklick/Minkoff
Brüssel Europäische Kommission Außenansicht
ምስል picture-alliance/dpa/D. Kalker

« ከአውሮጳ ህብረት ጋር በአጋርነት እንሰራለን። ይሁን እንጂ፣ ፍልሰት በቀነሰ ቁጥር አብረን የምንሰራበት ትብብር ይጠናከራል የሚለውን አስተሳሰብ  ሴኔጋል በፍፁም እንደማትቀበለው ነው የማስታውቀው።  ሴኔጋል አጋርነትን በዚህ መልክ አትመለከተውም።  ፍልሰትን እና ትብብርን ለማገናኘት የሚደረገውን አሰራር እኔም  በፍፁም አልቀበለውም። »

ፕሬዚደንት ሳል ይህን የማስፈራራት ያህል ቆጥረውታል። የሴኔጋል ፕሬዚደንት ከወጭም ከሀገር ውስጥም ጫና አርፎባቸዋል። የአውሮጳ ህብረትም ፍልሰትን ለመታገል የጀመረው ጥረቱን በተመለከተ ብዙ እየተጠበቀበት ነው። በሚልዮን የሚቆጠረው የቀረጥ ከፋዩ ሕዝብ ገንዘብ በርግጥ የሚፈለገውን ውጤት ያስገኛል ወይ? የወቅቱ ትልቅ ጥያቄ ነው። ማሴር ጌይ በኃይል ቆጣቢ ምድጃ ምርት የስራ ቦታ ፈጣሪ ሆኗል። ይሁን እንጂ፣ ወደ አውሮጳ የመፍለስ ህልሙን ዛሬም እርግፍ አድርጎ አልጣለውም፣ ልቡም ሀሳቡም ወደ አውሮጳ ነው። 

ማርክ ዱገ/አርያም ተክሌ

ልደት አበበ