1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፈረንሳይ ላይ የደረሰዉ ጥቃት

ቅዳሜ፣ ኅዳር 4 2008

በፓሪስ ፈረንሳይ ለደረሰዉ አሰቃቂ የሽብር ጥቃት እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራዉ ጽንፈኛ ቡድን ኃላፊነት መዉሰዱን ይፋ አድርጓል። ምዕራቡ ዓለም ይህን የአሸባሪዎች ጥቃት በጥብቅ ለመከላከል ትክክለኛ የሆነ እቅድ እንደሚያስፈልገዉ ብራስልስ የሚገኘዉ የዶቼ ቬለዉ ቤርንድ ሪገርት ዘግቧል።

https://p.dw.com/p/1H5mm
Frankreich Terror in Paris Stade de France Polizei
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Spingler

ፈረንሳይ በአሸባሪዎች ጥቃት መመታትዋ አዉሮጳን እጅግ አስደናግጧል። የአሸባሪዎቹ የፈሪ ጥቃት ዓላማ ፓሪስ ዉስጥ በአጋጣሚ የተገኙ ሰለባዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በሁሉም ሲቪል ማኅበረሰብ ላይ ያነጣጠረ ነዉ። የዩኤስ አሜሪካዉ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የፓሪሱን ጥቃት አስመልክተዉ እንደተናገሩት ጥቃቱ በመላ የሰዉ ልጆች ላይ የተጣለ ነዉ።
አሸባሪዎቹ ፓሪስ ላይ በነሲብ ሕዝብ መኃል ገብተዉ ግድያና ጥቃት ሲፈጽሙ መመልከቱ የሚቆጭ የሚነድ ነዉ። አሁን ፈረንሳይ አዉሮጳም ሆነ መላዉ ዓለም ይህን የአሸባሪ ጥቃት በጋራ ለመመከትና አፀፋዉን ለመመለስ በአንድነት መቆም ይኖርበታል። የእስላማዊ ጽንፈኞ ጥቃት አድራሽ ወንጀለኞችን በሁሉም መንገድ መታገል ይኖርብናል። እንዲህ ያለዉን የጭካኔ ጥቃት ከበስተጀርባ ሆነዉ የሚያቀነባብሩ ፅንፈኛ መሪዎች ሶርያም ይሁኑ ኢራቅ ወይም ሌላ ቦታ በፍጥነት ከያሉበት ታድነዉ ሊወገዱ ይገባል። እራሱን እስላማዊ መንግስት እያለ የሚጠራዉ አሸባሪ ቡድን ፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን በመላ ዓለም በነፃነት የሚኖረዉ ሕዝብ ላይ ነዉ ጦርነት ያወጀዉ።
በፈረንሳይ የነፃነት የእኩልነትና ወንድማማችነት ስም ዓለም በሙሉ አሸባሪነትን በመቃወም መነሳት ይኖርበታል። ነገ እሁድ አንታልያ ቱርክ ላይ የሚጀምረዉ በኤኮኖሚ ያደጉት የዓለም 20ዎቹ አገራት ጉባዔም ለዚህ ጥሩ አጋጣሚ ይሆናል።
ዩኤስ አሜሪካ፤ ሩስያ ምናልባትም የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት የ«ኔቶ» ጦር ኃይሎች በጋራ በሶርያና በኢራቅ የሚንቀሳቀሰዉ እራሱን እስላማዊ መንግሥት የሚለዉ ጽንፈኛ ቡድን ላይ ነገ ዛሬ ሳይሉ በአስቸኳይ ርምጃ መዉሰድ ይኖርባቸዋል።
ባለፈዉ ጥር ወር ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ ጥቃት ሲደርስ የዓለም ፖለቲከኞች በጋራ መቆማቸዉንና በፓሪስ ጎዳና ላይም እጅ ለእጅ ተያይዘዉ ማሳየታቸዉ ይታወሳል። ግን አሸባሪዎቹ ምናልባትም ኃይል የቀላቀለ ርምጃ ብቻ ስለሚገባቸዉ እንዲህ ያለዉን ሰላማዊ ተቃዉሞ የተረዱት አይመስልም። በአዉሮጳ የሚገኙ ወጣቶች ለአሸባሪ ጥቃት ዓላማ መመልመላቸዉ ምንም መፍትሄ ያልተሰጠዉ ጉዳይ ነዉ።
አንድ የአዉሮጳ ዜጋ ወደ ሶርያ አልያም ወደ ኢራቅ ሄዶ ጀሃዳዊ ስልጠናን ካገኘ ቢያንስ ወደ አዉሮጳ መመለስ እንዳይችል የተቻለዉ ሁሉ መደረግ ይኖርበታል።
በሃገራት መካከል ያሉ አንዳንድ ያለመግባባቶች አሁን ወደጎን መተዉ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም የፓሪሱ ዓይነት ጥቃት ነገ በየአንዳንዱ ሀገር ላይ ሊደርስ የሚችል ነዉና። ዓርብ ዕለት ሩስያ የአሸባሪ ጥቃት ማስጠንቀቂያ መሰማቱ ይፋ ሆኗል። ባለፈዉ ጥቅምት ቱርክ የአሸባሪ ጥቃት ሰለባ መሆኗ ይታወሳል። ማድሪድ ላይ በ2004 ዓ,ም ብሪታንያ ላይ ደግሞ 2005 ዓ,ም የአሸባሪዎች ጥቃት ደርሶአል።
የስደተኞች ቀዉስ በአዉሮጳ አስከፊና አሳሳቢ ስጋት ሆኗል። የአዉሮጳ ሕዝብ ደህንነት በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛል። የኗሪዉ ሰላማዊ ኑሮም ተናግቷል። አዉሮጳ አሁን ይህን ሁሉ ችግርና ቀዉስ ለመወጣት በጋራ መቆምና መሥራት ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ የአዉሮጳ መሪዎች ዬኤስ አሜሪካና ሩስያ በአንድነት ድምፃቸዉን ከፍ አድርገዉ « ራሳችን እንከላለን» የሚል መልስ መስጠት ይኖርባቸዋል።

Riegert Bernd Kommentarbild App
ቤርንድ ሪገርት


ቤርንድ ሪገርት / አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ