1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፌስቡክ የቢሊየነርነት አቋራጩ መንገድ

ሰኞ፣ ግንቦት 13 2004

ተጠቃሚዎቹ በቁጥር ወደ 900 ሚሊዮን አሻቅበዋል። ሀገር ቢሆን ኖሮ ቻይናና ህንድን ተከትሎ በዓለማችን ሶስተኛውን ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የያዘው ባስባለ ነበር። ፌስ ቡክ! የሚሊዮኖችን መረጃ እንደያዘ ሰሞኑን ለአክሲዮን ገበያ መቅረቡ በኒውዮርክ

https://p.dw.com/p/14zZx
ፌስቡክ የአምደመረቦች ሁሉ ቀዳሚ
ፌስቡክ የአምደመረቦች ሁሉ ቀዳሚምስል picture-alliance/dpa

ተጠቃሚዎቹ በቁጥር ወደ 900 ሚሊዮን አሻቅበዋል። ሀገር ቢሆን ኖሮ ቻይናና ህንድን ተከትሎ በዓለማችን ሶስተኛውን ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የያዘው ባስባለ ነበር። ፌስ ቡክ! የሚሊዮኖችን መረጃ እንደያዘ ሰሞኑን ለአክሲዮን ገበያ መቅረቡ በኒውዮርክ አደባባይ ይፋ ሆኗል። በዛሬው የዜና ማኅደር ጥንቅራችን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በአንድ ወጣት ተማሪ ተፀንሶ ተጠቃሚዎቹ በቁጥር ወደ 900 ሚሊዮን አሻቅበዋል። ሀገር ቢሆን ኖሮ ቻይናና ህንድን ተከትሎ በዓለማችን ሶስተኛውን ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የያዘው ባስባለ ነበር። ፌስ ቡክ! የሚሊዮኖችን መረጃ እንደያዘ ሰሞኑን ለአክሲዮን ገበያ መቅረቡ በኒውዮርክ አደባባይ ይፋ ሆኗል። በዛሬው የዜና ማኅደር ጥንቅራችን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በአንድ ወጣት ተማሪ ተፀንሶ ዛሬ በቢሊዮናት የሚቆጠሩ ዶላሮችን ማሳፈስ ስላስቻለው ፌስቡክ የምንለው ይኖረናል።

በማኅበራዊ የመገናኛ ዘርፎች ሁሉ በግዝፈቱ የሚስተካከለው የለም። አንድ ቢሊዮን ሊጠጋ ጥቂት የቀሩት አባላትንም ይዟል፤ ፌስቡክ። ከስምንት ዓመታት በፊት እንደዋዛ በዩኒቨርሲቲ መኝታ ክፍል ውስጥ ሲጀመር ለጥቂት ተማሪዎች ታስቦ ነበር። ያኔ ታዲያ የዳቦ ስሙን „thefacebook“ አሰኝቶ ብቅ ሲል በመጀመሪያው ቀን ወዲያውኑ 650 ሰዎች ተሽቀዳድመው ለአባልነት እጃቸውን አነሱ። ዛሬ ይኸው ፌስ ቡክ 900 ሚሊዮን አባላት እንዳሉት ይነገራል። ይህ አኃዝ የአሜሪካ የሕዝብ ብዛትን በሶስት እጥፍ የሚልቅ ነው። ያም ብቻ አይደለም፤ ግዙፍ ድርጅት ለመሆን በቅቶ አጠቃላይ ዋጋው 104 ቢሊዮን ደርሷል። ፌስቡክ ከቀናት በፊት ኒውዮርክ ውስጥ በአክሲዮን ገበያ ለህዝብ ሲቀርብ ሰዉ በሽሚያ ነበር ሲገዛው የዋለው። የዋል ስትሪቱ የአክሲዮን ደላላ ሉዊስ ሱልሴንቲ የአክሲዮን ሽያጩን ስኬት ቀድመው ነበር የተነበዩት

ናስዳቅ የአክሲዮን ገበያ ኒውዮርክ
ናስዳቅ የአክሲዮን ገበያ ኒውዮርክምስል AP

«ፌስቡክ እኮ ነው። በፌስ ቡክ ደግሞ የማይቻል ነገር የለም። መዋዕለ ንዋይ አፍሳሹ ማኅበረሰብ ስለ ፌስቡክ ጠንቅቆ ያውቃል፤ የተጠቃሚዎችን መሰረታዊ ፍላጎትም ይረዳል። የአክሲዮን ጨረታ መነሻው ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ነው የሚሆነው። ፌስቡክ ለመዋዕለ ንዋይ አፍሳሹ ማኅበረሰብ ታላቅ የስራ መስክ ነው።»

ፌስቡክ በዝርግ ኮምፒውተር
ፌስቡክ በዝርግ ኮምፒውተርምስል picture alliance/dpa

እንደተገመተውም የአክሲዮን ሽያጩ ኒውዮርክ በሚገኘው ናስዳቅ የቴክኖሎጂ ገበያ አርብ ዕለት ሁለተኛ ቀኑን ሲይዝ ፌስቡክ 15 ቢሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ እንደቻለ ተዘግቧል። ያም ብቻ አይደለም የፌስቡክ የንግድ ምልክት 100 ዓመታትን ካስቆጠሩት አንጋፎቹ የማክዶናልድ እና የኮካ ኮላ አርማዎች ተርታ ሊሰለፍ በቅቷል። በ8 ዓመት ጨቅላ ዕድሜው መሆኑ ነው። የ900 ሚሊዮን አባላቱ የግል ማኅደር፤ የእያንዳንዱን ሰው ፍላጎት፣ አዝማሚያ እና የኑሮ ዘዬ ልቅም አድርጎ ያካተተ መሆኑ ደግሞ ለፌስቡክ ሌላ የገበያ ምንጩ ነው። እንዴት ቢሉ ማስታወቂያ አስነጋሪዎች ይህን መረጃ በቀላሉ አያዩትምና። ፌስ ቡክ 82 በመቶ ገቢውን የሚሰበስበው ከማስታወቂያ ሽያጭ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ሁኔታ ደግሞ የበርካታ አክሲዮን ገዢዎችን ልብ ሳያማልል አልቀረም። አንዳንድ የመረጃ ጠበብት እንደሚያስጠነቅቁት ከሆነ ግን ከማስታወቂያ የሚገኘው ገቢ ዘላቂነቱ አጠያያቂ በመሆን ላይ ነው።

«በሂደት ሰዉ ኢንተርኔትን በተንቀሳቃሽ ስልኮቹ የመጠቀም ልማድ እያዳበረ መምጣቱ ህልውናቸው በማስታወቂያ ገቢ የተወሰነ ኩባንያዎችን ትርፍ ማናጋቱ አይቀርም። እናም ኩባንያዎቹ እየጨመረ ከመጣው በተንቀሳቃሽ ስልኮች የመጠቀም ልማድ አንፃር ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማየቱ ያጓጓል።»

በእርግጥም ማስታወቂያዎችን ተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይ ማስነገር አለያም ማኖር አስቸጋሪ ነገር ነው። ተንቀሳቃሽ ስልኮች ከኮምፒውተሮች አንፃር ሲታዩ የማሳያ መስታወታቸው እጅግ ጠበብ ያለ በመሆኑ ለጊዜው ለማስታወቂያ የሚመቹ አይነት አይደሉም። ጠበብቱ እንደሚገልፁት ከሆነ ህልውናው በማስታወቂያ ላይ የተመሰረተው ፌስቡክ ከቅርብ ጊዜያት አንስቶ የማስታወቂያ ገቢው እየቀነሰ በመምጣት ላይ ነው። በተለይ ከቅርብ ጊዜያት አንስቶ ሰዉ ስማርት ፎን ለሚባሉት ሁለ-ገብ የእጅ ስልኮች ትኩረት የመስጠት አዝማማሚያ በማሳየት ላይ ይገኛል። ለአብነት ያህል ከግማሽ በላይ የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች ፌስቡክን ከኮምፒውተር ይልቅ በእጅ ስልኮቻቸውና በዝርግ ኮምፒውተሮቻቸው ማለትም ታብሌቶች ላይ እንደሚገለገሉ ታውቋል። በህዝብ ብዛቷ በዓለማችን ቁጥር አንድ በሆነችው ቻይና ፌስቡክ የታገደ መሆኑ ደግሞ ለድርጅቱ ሌላ የገቢ ምንጭ ስጋት ተደርጎ ተወስዷል። ቻይና 500 ሚሊዮን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች እንዳሏት ይነገራል።

የፌስቡክ ማዕከል ካሊፎርኒያ
የፌስቡክ ማዕከል ካሊፎርኒያምስል DW

«የፌስ ቡክ አጋር መሆን የሚፈልጉ በርካታ የቻይና ኩባንያዎች እንዳሉ ማሰባችን አይቀርም፤ ይሁንና ፌስቡክ ለአጭር እና ለመካከለኛ ጊዜያት ያለ እነዚህ የቻይና ኩባንያዎች ስኬታማ እንደሆነ መዝለቅ ይችላል፤ ሆኖም በተለይ ከረዥም ጊዜ ዕቅድ አንፃር ይህን ሰፊ የኅብረተሰብ ክፍል ሳይዙ መጓዙ ሊታሰብበት ይገባል።»

ፌስቡክ እገዳ ከተጣለበት ቻይና በስተቀር በመላው ዓለም ያለ ተቀናቃኝ በመስፋፋት ላይ የሚገኝ የማኅበራዊ መገናኛ ዘርፍ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ 157 ሚሊዮን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች እንዳሉ ይጠቀሳል። በዓለማችን አሜሪካን ተከትሎ በሁለተኛ ደረጃ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የሚገኙት ብራዚል ውስጥ ሲሆን፤ ቁጥራቸውም 47 ሚሊዮን እንደሆነ ይነገራል። ህንድ በ45.8 ሚሊዮን፣ ኢንዶኔዢያ በ42.2 ሚሊዮን፣ እንዲሁም ሜክሲኮ በ33.1 ሚሊዮን የተጠቃሚ ቁጥር ከሶስት እስከ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በብራዚል ኦርኩት የተሰኘውን መሰል አምደ-መረብ፣ በሩሲያ ቭኮንታክቴን፣ በጀርመን ደግሞ ስቱዲ ቫው ሴትን ወደ ኋላ ጣጥሎ ዛሬ ፌስቡክ ብቻውን እየሸመጠጠ ይገኛል።

የፌስቡክ መስራች ማርክ ሱከርበርግ
የፌስቡክ መስራች ማርክ ሱከርበርግምስል Reuters

«በአሁኑ ወቅት በጀርመንም ሆነ በመላው ዓለም በእርግጥም የፌስቡክ ዋነኛ ተፎካካሪ ሆኖ ብቅ ያለ አንድም ተወዳዳሪ አልታየም። እንግዲህ ይህ ተጠቃሚዎችን የሚያስተሳስረው አምደ መረብ ነፀብራቅ ነው። ሰዉ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ያካተተ፣ እርስ በእርስ የሚያገናኘው እንደ ፌስቡክ ያለ የኢንተርኔት መድረክ ካገኘ ሌላ የሚፈልግበት ምክንያት አይታየኝም። ከዚያ አንፃር ስንመለከተው አሁን ፌስቡክ መድረኩን በሞኖፖል ለብቻው ተቆጣጥሮታል። ከዚያ አንፃር ስንመለከተው አሁን ፌስቡክ መድረኩን በሞኖፖል ለብቻው ተቆጣጥሮታል።»

ለመሆኑ ከአንዲት የዩኒቨርሲቲ መኝታ ክፍል እንደዋዛ ተነስቶ ዛሬ ከዓለማችን ዋነኛ ቢሊየነሮች ተርታ ሊሰለፍ የቻለው የዚህ የፌስቡክ ፈጣሪ ማን ነው?። 28ኛ የልደት በዓሉን ካከበረ ጥቂት ቀናት ነው የተቆጠሩት። እንደ ህልቆ መሳፍርት ትሩፋቱ ሳይሆን ለአለባበሱ እምብዛም ይመስላል። ሰርክ በጂንስ ሱሪ፣ በባለኮፍያ የሹራብ ጃኬት እና የስፖርት ጫማው ነው ከአደባባይ የሚውለው። ማርክ ሱከርበርግ ይባላል። የዛሬ ስምንት ዓመት፣ የዕድሜው ሃያዎቹ መንደርደሪያ ላይ ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ መኝታ ቤቱ ውስጥ ሆኖ ኮምፒተሩን እንደታቀፈ ያሰላስል ነበር። በእርግጥ ህልሙ ገንዘብ አልነበረም። ብቻ ገና ከልጅነቱ አንስቶ በኮምፒውተር ንድፍ የተነካው ስሜቱ ይዞ ይንጠው ነበር። የተናጠው ውስጡ ቅቤ ጠብ የማይለው ማሰሮ ሆኖ ግን አልቀረም። በቆይታ ከዓለማችን ጥቂት ቢሊየነሮች ተርታ ያሰለፈውን ፌስቡክ እውን እንዲያደርግ አስችሎታል።

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖ አይደለም። ገና ከመነሻው አንስቶ የዩኒቨርሲቲ ጓደኞቹ ሁለቱ መንትዮች፤ ታይለር እና ካሜሮን ዊንክሌቮስ የፌስቡኩ ሱከርበርግን እንደ ከሀዲ ነው የተመለከቱት። ወንድማማቾቹ ሱከርበርግ የሚያግዘን መስሎ እኛ ለዩኒቨርሲቲው ያቀድነውን አምደመረብ ንድፍ በመስረቅ ለፌስቡክ በህገ ወጥ ተጠቅሞበታል ሲሉ አሁንም ድረስ ይከሳሉ። ስለ መረጃ አጠባበቅ ጉዳይ የሚከራከሩ ተቋማት ደግሞ የተጠቃሚዎችን የግል ማኅደር ለማስታወቂያ ገቢ በማዋል የፌስቡኩ ባለቤት ትክክለኛ ነገር እየሰራ አይደለም ሲሉ ይወቅሳሉ። በዚህም አለ በዚያ ሰውዬው ዛሬ ቢጠሩት የማይሰማ፣ ቢገፉት የማይንቀሳቀስ ሃያል ቱጃር ሆኗል።

ማርክ ሱከርበርግና ፕሪሲላ ቻን
ማርክ ሱከርበርግና ፕሪሲላ ቻንምስል AP

የፌስቡክን 15 በመቶ ድርሻ አርብ ዕለት ለአክሲዮን በማቅረብ 15 ቢሊዮን ዶላር ያስገባው ማርክ ሱከርበርግ በማግስቱ ደግሞ ቻይናዊቱ ፕሪሲላ ቻንን በማግባት በትዳር መጠቃለሉ ታውቋል። ሱከርበርግ እና ቻን ፍቅራቸው የተጠነሰሰው ፌስቡክ ገና ሳይታሰብ እዛው ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሳሉ ነበር። ችግርሽ ችግሬ፣ ሀዘንሽ ሀዘኔ፣ ደስታሽ ደስታዬ ይሏል ይሄ ነው።

እንደው ከርዕስህ ወጣህ አትበሉኝ እንጂ፤ ሱከርበርግ ከሚለው ስያሜ ሁለት የጀርመን ቃላትን መዞ ማውጣት ይቻላል፤ ሱከር እና በርግን። በጀርመንኛ ሱከር ስኳር፣ ጣፋጭ እንደማለት ሲሆን፤ በርግ ደግሞ ተራራ የሚል ትርጓሜን ይይዛል። እንግዲህ የዚህን ወጣት ቢሊየነር ስያሜ በጀርመንኛ አሳብረን ወደ አማርኛ ብናመጣው የስኳር ተራራ፣ ወይንም የስኳር ቁልል የሚል ይሆናል ማለት ነው። ስምን መለዓክ ያወጣዋል አይደል ከነብሂሉስ? ቸር ያሰንብተን!

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ