1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፍጥጫና ተቃዉሞ በቱኒዚያ

ሰኞ፣ ግንቦት 12 2005

ትናንት ቱኒዚያ ዉስጥ በፖሊስና በ አንሣር አል-ሻሪያ ቡድን ደጋፊዎች መካከል የተነሳዉ ዉዝግብ የአንድ ሰዉ ህይወት ቀጥፎ ለብዙዎች ጉዳት ምክንያት ሆኗል። ግጭቱ በዋና ከተማ ቱኒዝና አቅራቢያዋ በሚገኙ አካባቢዎችም መዛመቱ ሲገለፅ መንስኤዉ ቡድኑያ ሊያካሂደዉ የነበረዉ ስብሰባ በመንግስት መታገዱ ነዉ።

https://p.dw.com/p/18b7N
ምስል picture alliance/AP Photo

መንግስት ሁለት መቶ የሚሆኑ የቡድኑን አባላት ማሰሩን አስታዉቋል። ያሉበት ያልታወቀዉ የአንሳር አል ሻሪያ መሪ ግን እሳቸዉም ሆኑ ደጋፊዎቻቸዉ ምንም ዓይነት መጉላላትና ጥቃት ቢፈፀምባቸዉ አልተሸነፍንም እያሉ ነዉ። በሰሜን አፍሪቃ ብሎም በአረቡ ዓለም ህዝባዊ አመፅ ባቀጣጠለችዉ ቱኒዚያ ዛሬም ነገሮች የሰከኑ አይመስሉም ለአልቃይዳ ያለዉን ድጋፍ በይፋ የገለፀዉእና ከቱኒዚያዉ አብዮት ማግስት ገሃድ የወጣዉ አንሣር አልሻሪያ የተሰኘዉ እስላማዊ ቡድን ዓመታዊ ጉባኤዉን በሳምንቱ ማለቂያ ለማድረግ ተዘጋጅቶ ነበር።

መንግስት ለህዝቡ አደገኛነዉ ያለዉን የቡድኑን ስብሰባ ማገዱ በአንሣር አልሻሪያ ደጋፊዎች ዘንድ ቁጣን አስከተለ። ቡድኑ በርካታ ደጋፊዎች እንዳሉት በተነገረባት ከቱኒዝ 15 ኪሎሜትር ርቃ ወደምትገኘዉ ኤታድሃመን ከተማም የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች እንዳይገቡ አዉራ ጎዳናዎችን በመሰናክል በማጠር የራሳቸዉን ምሽግ ፈጠሩ። ስብሰባዉ ይካሄድበታል በተባለዉ ስፍራ ትናንት ፖሊሶች መሰናክሉን አልፈዉ ሲገቡ ጓዳ ሰራሽ ሮኬቶችን ጨምሮ ጠንከር ያለ ጥቃት ዘነበባቸዉ።

Unruhen in Tunis
ምስል picture-alliance/dpa

ፖሊሶቹ አስለቃሽ ጭስ እየረጬ የፕላስቲክ ጥይት ይተኩሱ ስለነበርም በሁለቱ ወተኖች መካከል ግጭቱ ተባባሰ። ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በወቅቱ በተነሳዉ ግጭት ከቡድኑ ደጋፊዎች አንዱ ህይወቱን አጣ፤ ወደአስራ አምስት የተገመቱ ፖሊሶችን ጨምሮም በርከት ያሉት ጉዳት ደረሰባቸዉ።

የአንሣር አልሻሪያ መሪ ቱኒዚያ ዉስጥ ባለፈዉ መስከረም ወር የአሜሪካን ኤምባሲ ላይ ፅንፈኛ ሙስሊሞች የሰነዘሩትን ጥቃት አቀነባብረዋል በሚል እየተፈለጉ ነዉ። አድራሻቸዉ ያልታወቀዉ ተፈላጊ ለተሰብሳቢዎች ካሉበት ሆነዉ ባስተላለፉት መልዕክት እሳቸዉ ሊገኙበት በፈለጉት ሆኖም በመንግስት ባልተፈቀደዉ የቡድኑ ዓመታዊ ስብሰባ ደጋፊዎቻቸዉ ታሪክ ይሰራሉ ብለዉ እንደሚያምኑ አመልክተዋል። በአልቃይዳ ተዋጊነት አፍጋኒስታን ዉስጥ መቆየታቸዉ የተገለፀዉ አቡ ላይድህ የሳላፊስት ንቅናቄን ቱኒዚያ ዉስጥ ማጠናከራቸዉን ምዘገባዎች ይገልፃሉ።

እዉነተኛ ስማቸዉ ሳይፍ አላ ቢን ሁሴን መሆኑ የተገለፀዉ የአንሣር አልሻሪያ መሪ ከተሰወሩበት ሆነዉ ባስተላለፉት መልዕክትም እሳቸዉም ሆኑ መሰል የቡድኑ አባሎች እንግልት ቢደርስባቸዉም እንደማይሸነፉ አስታዉቀዋል። የእርሳቸዉ ቡድንበ ርካታ ደጋፊዎች እንዳሉት ቢገመትም በተቃራኒዉ እኚህ ቱኒዚያዊ ከጥብቅ ሃይማኖታዊ ህጎች ይልቅ ዛሬ ሃገራቸዉ የምትፈልገዉ ይህን ነዉ ይላሉ፤

«እስላማዊ መንግስት ማን ፈለገ? እኛ የምንፈልገዉ መደበኛ ገቢ እና ፀጥታ ነዉ። በአረቡ ዓለም መረጋጋት ነዉ የምንፈልገዉ።»

Tunesien Auseinandersetzungen Salafisten Polizei
ምስል picture alliance/AP Photo

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን ቡድን አሸባሪ ሲሉ ተሰምተዋል። ጠ/ሚኒስትር አሊ ላርያዲህ ቀጠር ላይ በሰጡት መግለጫ በሽብር ተግባር ዉስጥ እጁ እንዳለ ባመለከቱት አንሣር አል ሻሪያ ላይ ርምጃ እንደሚወሰድም ዝተዋል። ፀጥታዉን ለማስከበር ወደስፍራዉ ከተላኩት ፖሊሶች አንዱ፤

«የቡድኑን ደጋፊዎች እንቅስቃሴ ከፍፃሜ ለማድረስ እዚህ እንገኛለን። አስፈላጊ ከሆነም ለአንድ ወር ያህል ልንቆይ እንችላለን። ህጎች መከበር ይኖርባቸዋል።»

ቀድሞ የቱኒዚያ የአገር ዉስጥ ሚኒስትር አሁን ደግሞ ለዘብተኛ የሚባለዉ ኢናዳህ ፓርቲ አባል የሆኑት ጠ/ሚኒስትር በአመጽ ተግባር ተሰልፏል የሀገሪቱን ህግ ይፃረራል ባሉት አንሣር አል ሻሪያ ላይ መንግስት በአፀፋ የሚወስደዉ ርምጃም እጅግ ጠንካራ እንደሚሆ ነዉ ያመለከቱት። በዛሬዉ ዕለት የወጡ ዘገባዎች እንደሚሉትም መንግስት ሁለት መቶ የቡድኑን ደጋፊዎች አስሯል። ተንታኞች የጠ/ሚኒስትሩን አገላለፅ የፖሊሲ ለዉጥ ይላሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ