1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

​​​​​​​ፎቶግራፍ እና ለውጥ-ከማኅደር ኃይለሥላሴ ጋር የተደረገ ቆይታ 

ሐሙስ፣ ሰኔ 6 2011

በቅንጡ ስልኮች ላይ የተገጠሙ ካሜራዎች እና እንደ ኢንስታግራም ያሉ ማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ለፎቶግራፍ ፍቅር ላላቸው ወጣቶች እና ለኢትዮጵያውያን አዲስ ዕድል ከፍተዋል። የ29 አመቷ ማኅደር ኃይለስላሴ ኢትዮጵያ የምታልፍባቸውን ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦች ጨምሮ በተለያዩ ኅብረተሰቦች ላይ ያተኮሩ ፎቶግራፎች ታነሳለች።

https://p.dw.com/p/3KNk9
Impressions DW Global Media Forum 2019
ምስል DW/P.Böll

ከማኅደር ኃይለሥላሴ ጋር የተደረገ ቆይታ 

ለረዥም አመታት በፎቶ ቤቶች እና በውጭ አገር ዜጎች እጅ ተወስኖ የቆየው የፎቶግራፍ ሙያ ባለፉት አመታት በኢንተርኔት አገልግሎት እና ዘመናዊ ስልኮች መስፋፋት እየተለወጠ ይገኛል። ማኅደር ኃይለሥላሴ ይኸ ለውጥ ካፈራቸው የትውልዱ የፎቶ ባለሙያዎች መካከል አንዷ ነች። የምኅንድስና ትምህርት እና ሥራዋን በመተው በወደደችው የሥራ ዘርፍ የተሰማራችው ማኅደር ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ለውጦች በማኅበረሰብ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ የሚዳስሱ ስራዎች አሏት። በኢትዮጵያ እና በውጭ አገራት ስራዎቿን ለዕይታ አቅርባለች። 

ተወልዳ ያደገችው በአዲስ አበባ ነው። ማኅደር በፒያሳ፤ በመርካቶ፣ በእሪ በከንቱ፤ በአራት ኪሎ፤ በካዛንቺስ አዲስ አበባ የምታልፍባቸውን ለውጦች የሚያሳዩ ፎቶግራፎች አንስታለች። ማኅበራዊው፤ ኤኮኖሚያዊው እና ፖለቲካዊው ለውጥ የማኅደርን ትኩረት የሳበ በፎቶግራፍ የሚነገር ታሪክ ነው። ማስቲካ እና ሲጋራ ነጋዴው፤ ዘበኛ፤ ፈጫይ፤ የቀን ሰራተኛ፤ የጎዳና ተዳዳሪ ...ሁሉም በማኅደር ካሜራ የሚነገር ታሪክ አላቸው።

Kafeeernte in Äthiopien
ምስል Reuters/M. Haileselassie

የ29 አመቷ ማኅደር ኃይለሥላሴ በኢትዮጵያ በፍጥነት በመስፋፋት ላይ በሚገኘው የፎቶግራፍ ሙያ ተቀባይነት ካገኙ ባለሙያዎች መካከል አንዷ ናት። በስራዋ እንደ ሴቶች፤ ሕፃናት እና እናቶች ያሉ ማኅበረሰቦችን የተመለከቱ ርዕሰ-ጉዳዮች ትኩረት ከምታደርግባቸው መካከል ይገኙበታል። 

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ!

እሸቴ በቀለ