1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፑቲን የዩክሬይን ውጥረትን ለማለዘብ ዝግጁ ነኝ አሉ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 11 2006

የሩስያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬይን ቀውስን ተከትሎ ሀገራቸው ከምዕራባውያን ጋ የገጠማትን አለመግባባት ለማረቅ ዝግጁ መሆናቸውን ገለጡ።

https://p.dw.com/p/1Bl8Y
Russland Präsident Wladimir Putin 18.04.2014
ምስል Reuters

ፑቲን ግንኙነቱን ለማሻሻልና አብሮ ለመስራት መንገዶች ሁሉ የተዘጉ አይደሉም ሲሉ በአንድ የቴሌቪዥን ቃለመጠይቅ ላይ ተናግረዋል። ይሁንና ውጥረቱን ማለዘቡ በሩስያ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በምዕራባውያን ጭምር ነው ብለዋል። ፑቲን ይህን ቢገልፁም፤ ምሥራቅ ዩክሬይን ውስጥ የሚገኙት መፍቀሬ-ሩስያ ታጣቂዎች ግን አሁንም ድረስ መሣሪያቸውን መፍታት፣ የተቆጣጠሩዋቸውን ሕንፃዎችም መልቀቅ እንደማይፈልጉ ጠቅሰዋል። ውጥረቱን ለማርገብ ታጣቂዎቹ ሕንጻዎቹን መልቀቅ ብሎም የጦር መሳሪያቸውን መፍታት እንዳለባቸው ሐሙስ ጄኔቫ ውስጥ በተደረገው የዩክሬይን ጉባኤ መወሰኑ ይታወቃል። ሩስያ በመፍቀሬ ሩስያ የዩክሬይን ታጣቂዎች ላይ ያላትን ተፅዕኖ ተጠቅማ ታጣቂዎቹ እንዲያፈገፍጉ እንድታደርግ ዩናይትድ ስቴትስ ጠይቃለች። ሩስያ ይህን ካላደረገች ግን «ሌላ ነገር ሊከተል ይችላል» ስትል ዩናይትድ ስቴትስ በመንግሥት ቃል አቀባዩዋ በኩል አስጠንቅቃለች

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ከሩሲያ የፖለቲካ አቻቸው ሰርጌይ ላቭሮብ ጋር በምሥራቅ ዩክሬይን የሚገኙት መፍቀሬ ሩሲያን ጠመንጃቸውን እንዲያስረክቡ እና በቁጥጥራቸው ስር ያሉትን ሕንፃዎች እንዲለቁ በስልክ ተወያይተዋል። የሀገሪቱ የደህንነት አማካሪ ሱዛን ራይስ ዩናይትድ ስቴትስ ሰሞኑን በዩክሬይን የሚካሄዱትን ነገሮች በጥብቅ እንደሚከታተሉ አሳስበዋል።

ልደት አበበ
ማንተጋፍቶት ስለሺ