1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፓሪስ/ አቢዣን፤ ባግቦ ተያዙ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 3 2003

በምርጫ አልተሸንፍኩም በማለት ዓለም ዓቀፍ እውቅና ከተሰጣቸው ከአላሳን ዋታራ ኃይሎች ጋር ሲዋጉ የከረሙት የአይቮሪ ኮስት ፕሬዝዳንት ሎሮን ባግቦ ተያዙ።

https://p.dw.com/p/RH5y
ሎረን ባግቦምስል picture alliance/abaca

የተቀናቃኛቸውን የአላሳን ዋታራን ቃል አቀባይ ጠቅሶ የጀርመን ዜና አገልግሎት DPA እንደዘገበው ባግቦ አቢዣን ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ከቤተሰባቸው ጋር መያዛቸውን ቃል አቀባይ ማማዱ ቱሬ አስታውቀዋል። በፈረንሳይ የኮት ዲቯር አምባሳደርም የባግቦን መያዝ አረጋግጠዋል።

ቱሬ እንዳሉት ለደህንነታቸው ሲባልም ባግቦና ቤተሰባቸው ጎልፍ ወደተባለው ሆቴል ተወስደዋል። ሆቴሉ የኮትዲቯሩ ምርጫ ከተካሄደበት ከህዳር ወዲህ የዋታራ መቀመጫ ሆኖ እያገለገለ ነው። በኮት ዲቯር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዑክ ዩሱፉ ባምባ ፣ ባግቦ በህይወት እንደተያዙና በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀው ለፍርድ እንደሚቀርቡም ተናግረዋል። ባምባ እንዳሉት ባግቦን ለመያዝ በተወሰደው እርምጃ የኮት ዲቯር ኃይሎች ብቻ ናቸው የተሳተፉት። ባግቦ በቁጥጥር ስር መዋላቸው የተሰማው የፈረንሳይ ታንኮች ወደ መኖሪያቸው መገስገሳቸው ከተነገረ በኋላ ነው። የዓይን ምስክሮች እንደተናገሩት ዛሬ ጠዋት ወደ ባግቦ መኖሪያ የገሰገሱት ታንኮች ብዛት ከ30 በላይ ነው። ይሁንና ባግቦን ማን እንደያዛቸው ግልፅ አልነበረም። ባግቦን የያዙት የፈረንሳይ ወታደሮች እንደሆኑ የተጠየቁት አንድ የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንጭ ይህን የሚያረጋግጥ ማስረጃ የለንም ማለታቸው ተዘግቧል።

ሂሩት መለሠ

አርያም ተክሌ