1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፓንክረስት እና ሥራዎቻቸዉ

ሐሙስ፣ የካቲት 16 2009

«ሲያሳድገን ለኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ ያለዉን አክብሮት አስተላልፎአል። እኔን አሉላ ብሎ ሲሰይመኝ እህቴን ደግሞ ታሪክ ብሎ ስም አወጣላት። ከዚህ ባሻገር በኢትዮጵያ በኋያላን ቅኝ ገዥ ሃገራት የተዘረፉ ቅርሶችን በተለይ ታቦታት መስቀሎችን ብራና ወዘተ ለማስመለስ ያላሰለሰ ጥረት ያደርግ ነበር።»

https://p.dw.com/p/2Y74V
Professor für Geschichte Richard Pankhurst gestorben
ምስል Alula Pankhurst

Kultur_230217_Zum Tod des großen Äthiopisten Richard Pankhurst - MP3-Stereo

« የኢትዮጵያ ታሪክ ተማሪ ነበርኩ። ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የሄድኩትም  1943 ዓ.ም ነዉ። ኢትዮጵያ ለመኖር ወስኜ ጓዜን ጠቅልዩ ኢትዮጵያ የገባሁት በ 1948 ዓ.ም ነዉ። በዝያን ጊዜ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አስተማሪ ነበርኩ። ባለቤቴ ሪታ ደግሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መጻሕፍት ዉስጥ ትሰራ ነበር። በዝያን ጊዜ ታድያ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለዘጠኝ ወር እንቀመጥና ትምህርት ቤት ሲዘጋ የበጋ እረፍታችንን ለሁለት ወራት ገደማ እናሳልፍ የነበረዉ የነበረዉ ብሪታንያ ለንደን ዉስጥ ነበር።»    

ሪቻርድ ፓንክረስት እና የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት መስራችና ባለቤት አቶ ኤልያስ ወንድሙ
ሪቻርድ ፓንክረስት እና የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት መስራችና ባለቤት አቶ ኤልያስ ወንድሙ በቀደሙት ዓመታት የተነሱት ፎቶግራፍምስል TSEHAI Publishers/E. Wondimu

የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪና ኢትዮጵያን ወዳጁ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በጎርጎረሳዊዉ 2007 ዓ.ም በለንደን ለሚገኘዉ የኢትዮጵያ ቅርፅ ማበልጸግያ ማኅበር ከሰጡት ሰፊ ቃለ-ምልልስ የተወሰደን ነበር ያደመጥነዉ።  ዘለግና ቀዝቀዝ ብለዉ በመናገራቸዉ የሚታወቁት የኢትዮጵያ ወዳጁ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የኢትዮጵያን ማንነት በድምቀት ለዓለም ያሳወቁ ታሪክዋን የተናገሩና ስለኢትዮጵያ የተከራከሩ ትልቅ ምሁርና የኢትዮጵያም ኃብት ናቸዉ። በዚህ ዝግጅታችን የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትን ማንነት እንዘክራለን ።   

ዉለታቸዉ በኢትዮጵያዉያን ዘንድ ሲታወስ የሚኖረዉ ፕሮፊሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ለኢትዮጵያ የነበራቸዉን አላማና ከናታቸዉ ከሲልቭያ ፓንክረስት የተቀበሉትን ቃል ኪዳን ለኢትዮጵያ ታማኝ አገልጋይ በመሆን አልፈዋል። በዬኤስ አሜሪካ መዲና ነዋሪ የሆኑት የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት መስራችና ባለቤት አቶ ኤልያስ ወንድሙ ሬቻርድ ፓንክረስትንና ቤተሰቦቻቸዉን የሚያዉቋቸዉ ገና በልጅነት እድሜያቸዉ ነዉ።

ሪቻርድና ሪታ ፓንክረስት በለንደን ነዋሪ ከሆኑት የኢትዮጵያ ቅርፅ ማበልጸግያ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ አለባቸዉ ደሳለኝ
ሪቻርድና ሪታ ፓንክረስት በለንደን ነዋሪ ከሆኑት የኢትዮጵያ ቅርፅ ማበልጸግያ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ አለባቸዉ ደሳለኝ ምስል DW/A. Desalegn

« የምንተዋወቀዉ አገርቤት እያለሁኝ ከልጃቸዉ ከአሉላም ጋር እተዋወቅ ነበር የኢትዮጵያ የቅርስ ባለአደራ ማኅበር በሚቋቋምበት ጊዜ ከመስራች አባላቱ አንዱ ነበርኩኝ። እንደዉም እሳቸዉ ከአቶ ደበበ ኃብተ ዮኃንስ ጋር ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ነበሩ፤እኔ ደግሞ የአባላት ፀሐፊ ነበርኩኝ። እዛ ነዉ ትዉዉቃችን። ከዝያ ቀደም ብዬ ከአንድ ዓመት በፊት አዉቃቸዋለሁ።

በህትመት ሥራ ሞያ ላይ ሳሉ ከፈረንጅም ከአበሻም በርካታ ምሁራንን ለመተዋወቅ እድሉ ነበረኝ እንደ ሪቻርድ ፓንክረስት አይነት ምሁር ግን አላየሁም ያሉን የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ባለቤት አቶ ኤልያስ በመቀጠል

ፕሮፊሰር ፓንክረስት በጋዜጠኝነት በሰራሁባቸዉ ብዙ ዓመታት ከዚያም በኋላ ደግሞ አሁን በአሳታሚነት ለረጅም ዓመታት በምሰራበት ጊዜ ብዙ ሰዎችን ለማግኘት እድሉ አጋጥሞኛል ፤ እንደ እሳቸዉ ዓይነት ሰዉ አጋጥሞኝ አያዉቅም። የሚሰሩት ስራ ደግሞ እስከመጨረሻዉ ድረስ አላቆመም። ከማረፋቸዉ አምስት ቀናት በፊት ደብዳቤ «ኢሜል» ልከዉልኝ ነበር። ያ ኤሜላቸዉ ምንድን ነዉ የሚለዉ አንድ በመጨረሻ ያሳተምንላቸዉ መጽሐፍ አለ። ይህ መጽሐፍ ኬንያ በቅኝ ግዛት ስር በነበረችበት ወቅት የጻፍዋት ትንሽ መጽሐፍ ነች። የመጽሐፍዋን አዲስ መግብያ ጽፈዉ እንድናሳትምላቸዉ ጠይቀዉኝ አሳትሜላቸዉ ነበር፤ እና የመጽሐፍዋን ቅጂ ደርስዋቸዉ ነበር ያንን ኤሜል የላኩልኝ። እና ፓንክረስት በኤሜላቸዉ እናቴ በፋሺስት ኢጣልያ ወቅት የጻፈቻቸዉ ጽሑፎች  አሉ እነሱን በመጽሐፍ መልክ እያዘጋጀሁ ነዉ ልላክልህ ወይ ሲሉ ነበር የጻፉልኝ። ለዝያ ደብዳቤያቸዉ መልስ ከሰጠኹ ከአምስት ቀናት በኋላ ነዉ ያረፉት። እስከዚህ ሰዓት ድረስ ይሰሩ ነበር። ሌላም መጽሐፍ እንዲሁ እየሰራን ነዉ የኢትዮጵያ ትዝታዎቻችን የሚለዉ መጽሐፋቸዉ እሳቸዉና ባለቤታቸዉ ሪታ ፓንክረስት የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ ያሳተምነዉ መጽሐፍ አለ የሱን ሁለተኛ ክፍልም እየሰሩ ነበር። እና እንደሳቸዉ መሆን ቢቻል የምለዉ ትልቅ ነገር ነዉ። ትልቅ ሰዉ ነዉ ያጣነዉ።»

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፅዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፅዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስምስል DW/A. Wabella

የታዋቂ ኢትዮጵያዉያን ሕይወት ታሪክ በፊልምና በፎቶ በመቅረፅና በማስቀመጣቸዉ የሚታወቁት በለንደን የኢትዮጵያ ቅርፅ ማበልጸግያ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ አለባቸዉ ደሳለኝ በበኩላቸዉ ከሪቻርድ ፓንክረስት ጋር የሩቅ ጊዜ ትዉዉቅ አላቸዉ። ልበ  ኢትዮያዊዉን የታሪክ አዋቂን በተለያዩ ጊዜያት  በመቶዎች የሚቁጠሩ ፎቶግራፎችን አንስተዋቸዋል።  የኢትዮጵያን ታሪክ እንደ ሬቻርድ ፓንክረስት በጥልቅ የተመራመረ ምሁር የለም ሲሉም ነዉ፤ አቶ አለባቸዉ ሪቻርድን የሚገልጹዋቸዉ።  

ሪቻርድና ሪታ ፓንክረስት
ሪቻርድና ሪታ ፓንክረስት ምስል Alula Pankhurst

 «የኢትዮጵያን ታሪክ በተመለከተ እንደ እኔ የግንዛቤ ደረጃ እንደ ሪቻርድ ፓንክረስት ያህል በርካታ መጽሐፎችን የጻፈና በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ በጥልቅ የተመራመረ ያለ አይመስለኝም። ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ በተለያዩ ትኩረቶች በባህል በኤኮኖሚ በታሪክ የተለያየ የማኅበረሰቡን አኗኗር መጠነ ሰፊ ምርምር በማድረግ  በርካታ ጥናታዊ ጽሑፍን ያበረከቱ ታላቅ ምሁር ናቸዉ። ከምርምር በተጓዳኝ ፕሮፊሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በተለይ በባዕዳን የተዘረፉትን የኢትዮጵያን ቅርሶች ለማስመለስ ጠንክረዉ የሰሩ ለዉጤትም የበቁ ፕሮፊሰር ናቸዉ። የአክሱም ሃዉልት አስመላሽ ኮሚቴ ሆነዉ ባገለገሉበት ወቅት የመቅደላ ታሪካዊ ቅርሶች አስመላሽ ማኅበር ብለዉ በብሪታንያ መስርተዉ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታላቅ ምሁር ናቸዉ።     

አቶ አለባቸዉ ሪቻርድ ፓንክረስትን የተረጋጉ ነገርን በጥሞና የሚያጤኑ ሰዉ ሲሉ ይገልጹዋቸዋል፤ ትዉቃቸዉም ሪቻርድ ፓንክረስት የአክሱምን ሃዉልትን ለማስመለስ ዘመቻ ላይ ሳሉ ነበር።

«ከኔም ጋር ልብ ለልብ የተግባባነዉ በአንድድ ወቅት የአክሱም ሃዉልትን ለማስመለስ እሳቸዉ ባደረጉት ዘመቻ ለንደን ላይ አብሪአቸዉ በጣልያን ኤንባሲ ዉስጥ ነበርኩ።  ከፍተኛ ተቃዉሞአችንን በሰልፍ ካሰማን በኋላ እሳቸዉ መኖርያ ቤት በግል ተገናኝተን  ብዙ ነገሮችን ተጨዋወትን እኔም መኖርያ ቤቴን ከባለቤታቸዉ ከሪታ ፓንክረስት ጋር ሆነዉ እንዲጎበኙ ጋበዝኳቸዉ። ፕሮፊሰሩ በጣም ጥልቅ የሆኖ ሰዉ ናቸዉ ፤ በጣም የተረጋጉ ሰዉ ናቸዉ ሳይጣደፉ ጊዜ ወስደዉ  የሰበሰብኩዋቸዉን ቅርሶች ካዩ በኋላ  የተሰማቸዉን ጥልቅ ደስታ ገለፁልኝ የት እንደገዛኋቸዉ እንዴት እንደተሰበቡ የገዛሁበትን ካርኒ ሳይቀር አሳየኋቸዉ በጣም በጣም እጅግ በጣም ተደነቁ ፤ ብዙዎቹን በታሪክ ባዉቃቸዉም ለማየት ፈልጌ አላየኋቸዉም ነበር ፤ ድንቅ ስራ ነዉ የሰራኸዉ በማለት እኔንም አደነቁኝ ደስ ብሎአቸዉ ተለያየን ። በነጋታዉ ጠዋት ስነሳ የጻፉዋቸዉን መጽሐፎች በሙሉ ማለት ይቻላል ፤ አንዳንድ ቅጂ አድርገዉ መጽሐፋቸዉ ላይ ደግሞ እየፈረሙ በካርቶን ሙሉ አሽገዉ በታክሲ አድርገዉ እቤቴ ድረስ ላኩልኝ። እጅግ በጣም ማመን እስኪያቅተኝ ድረስ ነበር የተደሰትኩት፤ እና ከዝያ በተቸማሪ እንድበረታ ተስፋ እንዳልቆርጥ ጠንክሪ ደግሞ የኢትዮጵያን ቅርስና ታሪክ እንድሰበስብ አደራ ጭምር ያለበት እጅግ የሚያበረታታ የጽሑፍ ደብዳቤ አክለዉ ነበር የላኩኝ፤ ከዝያ ወዲህ ነዉ ወዳጅነታችን እየቀጠለ የሄደዉ። ከዝያ ልጃቸዉ ዶክተር አሉላ ፓንክረስትም ባለቤታቸዉም ወ/ሮ ቆንጅትም እንዲሁም የልጅ ልጆቻቸዉን ጨምረዉ ወደኔ ቤት ላክዋቸዉ፤ ቅርሶቹን ጎበኙ። ፕሮፊሰሩ በተለያዩ ጊዜያት ለንደን በሚደረግ ዝግጅት ይመጡ ነበረ በዝያ አጋጣሚ የሕይወት ስራቸዉን እንድሰራና ቃለ ምልልስ እንድናደርግ ጠየኩዋቸዉ ፍቃደኛ ሆኑ፤ እንግዲህ የዛሬ 10 ዓመት ገደማ ነዉ ጥያቄዬን አዘጋጅቼ በቪዲዬ የቀረስኳቸዉ»   

ፕሮፊሰር መስፍን ወ/ማርያም በቀብር ሥነ-ስርዓቱ ላይ
ፕሮፊሰር መስፍን ወ/ማርያም በቀብር ሥነ-ስርዓቱ ላይ ምስል DW/G. Tedla

አቶ አለባቸዉ ደሳለኝ ሪቻርድ ፓንክረስትን ቃለምልስ በማድረግ የቀረጽዋቸዉን የቪዲዮ ምስል ከአምስት ቀናት በፊት በዩቲዩብ ድረገፅ ላይ ለተመልካች ለቀዋል። ፕሮፊሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ኢትዮጵያን ከመዉደድ ባሻገር ከአብራካቸዉ የወጡትን ልጆች ስም ኢትዮጵያዊ አድርገዋል ፤ ልጃቸዉም ኢትዮጵያዊት ሴትን ነዉ ያገቡት። በዚህም እንደሚኮሩ ሪቻርድ ፓንክረስት እንዲህ ሲሉ ተናግረዉ ነበር።

« ኢትዮጵያዊት ሚስት ስላለዉ በጣም ኩራት ይሰማኛል። በገሚስ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የልጅልጆችም አሉን። እንደኔ እምነት በመጀመርያ ኢትዮጵያን የተዋወቀችዉ እናቴ በኢትዮጵያ ባህል፤ ጥንታዊ ጽሑፎች  በመማረክዋ ይመስለኛል። ይህን ሁሉ ነገር ብታዉቅ በጣም ደስ ይላት ነበር። ግን በጣም ነዉ ቀድማ የሞተቸዉ። »

ባለፈዉ ማክሰኞ በተፈፀመዉ የቀብር ስነስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የፕሮፊሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ልጅ አሉላ ፓንክረስት “አባቴ ከእግዜብሄር የተሰጠው ተልዕኮ ኢትዮጵያን ማገልገል ነበር” ሲሉ መናገራቸዉ ለኢትዮጵያዊዉራት ኩራት ወዲህም የታሪክ ተመራማሪዉ በሞት መለየትን አሳዝኖአል። 

«ሲያሳድገን ለኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ ያለዉን አክብሮት አስተላልፎአል። እኔን አሉላ ብሎ ሲሰይመኝ እህቴን ደግሞ ታሪክ ብሎ ስም አወጣላት። አባቴ ሕይወቱን በሙሉ  ያሳለፈዉ  በጥናትና ምርምር ነበር። ከዚህ ባሻገር በኢትዮጵያ በኋያላን ቅኝ ገዥ ሃገራት የተዘረፉ ቅርሶችን በተለይ ታቦታት መስቀሎችን ብራና ወዘተ ለማስመለስ ያላሰለሰ ጥረት ያደርግ ነበር። ለበለጠና ለተሻለ እዉቀት መጣር እንዳለብን እየመከረን ገና ብዙ ስራ እንደሚጠብቀን ያስተምረን ነበር።»

ዶክተር አሉላ ፓንክረስት በቀብር ሥነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ሲያደርጉ
ዶክተር አሉላ ፓንክረስት በቀብር ሥነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ሲያደርጉምስል DW/G. Tedla

ወ/ሮ ሲልቪያ ፓንክረስት እንግሊዛዊትዋ የኢትዮጵያ ጀግና ሲሉ የፕሮፊሰር ሲልቪያ ፓንክረስት እናት የጭር የሕይወት ታሪክን የፃፉት በሰሜን አሜሪካ ነዋሪ የሆኑትና በዓለም አቀፉ ኅብረት ለፍትህ የኢትዮጵያ ጉዳይ ተጠሪና የጣልያን መንግሥት ለኢትዮጵያ ካሳ እንዲከፍል በመሟገት ላይ የሚገኙት አቶ ኪዳኔ አለማየሁ የፕሮፊሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እናት ሲልቪያ ፓንክረስት አዲስ አበባ መስከረም 27 ቀን 1960 ዓ,ም  ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸዉንና ወለተ ክርስቶስ ተሰኝተዉ እንደ ታላላቅ አርበኞች በመንበረ ፀባዎት ቅድስ ሥላሴ ካቴድራል አስክሪናቸዉ ማረፉን ተናግረዋል። የ 50ኛ ሙት ዓመታቸዉም መስከረም 17 ቀን 2003 ዓ,ም ነበር የዋለዉ።

«ከፕሮፊሰር ርቻርድ ፓንክረስት ጋር የቅርብ ግንኙነት ነበረኝ። እናታቸዉ ሲልቪያ ፓንክረስት 50ኛዉ ሙት ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲዘከር ጥረት አድርጌ ነበር። በዝያ ምክንያት በሪቻርድ ፓንክረስት ጋር በጣም በጣም ተቀራርበን ነበር ። የሙት ዓመት ዝግጅቱም የተሰናዳዉ በልዩ ልዩ የዓለም ሃገሮች ነበር በዩኤስ አሜሪካ ለንደን አዲስ አበባም ቅድስት ስላሴ ቤተክርስትያን  ነዉ ተከናዉኖ የነበረዉ። ሁሉም ዝግጅት ሪቻርድ ፓንክረስት በተገኙበት ነዉ የተከናወነዉ። የሲልቪያ  ፓንክረስትን ታሪክ ከ 20 ዓመት በላይ ነዉ፤ እንደማንናዉም ጀግና ነዉ በፋሺስት ኢጣልያ ወረራ ጊዜ የተፈፀመዉን ከዝያም በኋላ በልዩ ልዩ መንገድ ፤ ሃኪም ቤት እንዲቋቋም ነርሶች እንዲሰለጥኑ የሴቶች መብት እንዲሻሻል ብዙ ብዙ እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል። ሲልቢያ ጣልያን ሃገር ሄደዉ ፋሺስቶች የፈፀሙትን በደል ካዩ በኋላ በቻም ተቆጭተዉ የኢትዮጵያ ጠበቃ ሆነዉ ጄኔቫ እና ልዩ ልዩ ቦቻዎች ድረስ እየሄዱ ይከራከሩ ነበር። ልጃቸዉንም ፓንክረስት ብለዉ በራሳቸዉ ስም የሰየሙት ይህንኑ ተከትሎ ነዉ»

በቀብር ሥነ-ስርዓቱ ላይ ዶክተር አሉላ ፓንክረስት ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር
በቀብር ሥነ-ስርዓቱ ላይ ዶክተር አሉላ ፓንክረስት ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር ምስል DW/A. Wabella

አቶ አለማየሁ ባቀረቡት በዚህ ጽሑፍ ሙሉ ሕይወታቸዉና ዓላማቸዉ ኢትዮጵያን ያደረጉት ሲልቪያ ፓንክረስት እንግሊዝ ሃገር በስደት ይኖር ከነበረ ኢጣልያዊ ከሲልቪዮ ኮሪዮ ጋር ተፋቅረዉ ሪቻርድ ፓንክረስት መወለዳቸዉን አስቀምጠዋል። 

የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት መስራችና ባለቤት አቶ ኤልያስ ወንድሙ፤ ፕሮፊሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ኢትዮጵያን አንግበዉ በዓለም መድረክ ያቀረቡ እንደ ቴዮድሮስ አይነት ወኔ አልያም የምኒሊክን ዓይነት ብልሃት ያላቸዉ ይሏቸዋል።

«ኢትዮጵያ ባለፉት 50 ዓመታት ምናልባት ብዙ ምሑራንን አፍርታለች። ግን ነች ሆነዉ ልባቸዉ አበሻ የሆኑ ሰዎች ምናልባት የቴድሮስን አይነት ወኔ የምኒሊክን ብልሃት ኖርዋቸዉ በዝምታ ለዘብ ብለዉ በቀስታ አነጋገር ግን በዉስጣቸዉ ባለ ትልቅ እሳት የኢትዮጵያን ማንነት በዓለም ላይ ያቀጣጠሉ ችቦዋን ያበሩ ታሪክዋን የተናገሩ ትልቅ ትልቅ ምሁር ናቸዉ። ስለዚትዮጵያ ቅርስ መመለስ ከእንጊሊዝ ከትዉልድ ሃገራቸዉ ጋር ወይም ደግሞ ከጣልያን ከአባታቸዉ ሃገር ጋር ከእንጊሊዝ ከናታቸዉ ሃገር ጋር ሲፋተጉ የቴዮድሮስ አይነት ወኔ ነዉ ነዉ የሚታይባቸዉ። በለጋ እንድሜዬ እንደዝያ አይነት ሰዉ አግንቼና ተዋዉቄ ቤተሰብ ሆኜ ለማደግ መቻሌ ፤ የሰጡኝንም ዉርስ ለመቀጠል ሙከራ ማድረጌ መቼም ትልቅ እድለና ነኝ ብዬ አምናለሁ። 

የፕሮፊሰር ሪቻርድ ፓንክረስት አስክሪን በመንበረ ፀባዎት ቅድስ ሥላሴ ካቴድራል የእናታቸዉ መካነ መቃብር አጠገብ አርፏል።
የፕሮፊሰር ሪቻርድ ፓንክረስት አስክሪን በመንበረ ፀባዎት ቅድስ ሥላሴ ካቴድራል የእናታቸዉ መካነ መቃብር አጠገብ አርፏል። ምስል DW/A. Wabella

የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት መስራችና ባለቤት አቶ ኤልያስ ወንድሙና በለንደን የኢትዮጵያ ቅርፅ ማበልጸግያ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ አለባቸዉ ደሳለኝስለ ሪቻርድ ፓንክረስት አንድ ከአዕምሮአቸዉ የማይፍቁት ትዉስታ አላቸዉ። 

የአንድ ሴትና ልጅና የአንድ ወንድ ልጅ አባት የሆኑት ታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ባደረባቸዉ የሳምባ ሕመም አርብ የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ጠዋት በ 89 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸዉን ልጃቸዉ አሉላ ፓንክረስት የሰጡን መረጃ ያመለክታል። የፕሮፊሰር ሪቻርድ ፓንክረስት አስክሪን በመንበረ ፀባዎት ቅድስ ሥላሴ ካቴድራል የእናታቸዉ መካነ መቃብር አጠገብ አርፏል ።  ለባለቤታቸው ለልጆቻቸዉ ለልጅ ልጆቻቸዉና ለወዳጆቻቸዉ  መጽናናትን፣ ለእርሳቸውም እረፍተ-ነፍስን እንመኛለን። ቃለ ምልልስ የሰጡንን በሙሉ በዶይቼ ቬለ ስም እያመሰገንን ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ