1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፓኪስታን የሽብር መሐል ምርጫ

ሰኞ፣ ግንቦት 5 2005

የኢዝላማባድ ፖለቲከኞች «መሪዎቻችን በአሸባሪዎች ሥለተገደሉ፥ ባልደረቦቻችን ሥለታገቱ» ወይም ከአወደ አፍሪቃ በተደጋጋሚ እንደምንሰማዉ «መስዋዕትነት» ሥለከፈልን የያዝነዉን ሥልጣን አንለቅም አላሉም።እንደ ባግዳድ፥ እንደ ካቡል፥ እንደ ሞቅዲሾ ፖለቲከኞች ቤተ-መንግሥት ተቀምጠዉ በወኪል፥ በራዲዮ፥ ቴሌቪዥን ንግግር፥ ተመረጥን አላሉም።

https://p.dw.com/p/18X5H
Supporters of the Pakistan Muslim League - Nawaz (PML-N) celebrate in front of a party office as results of the general election come in, in Lahore May 11, 2013. Former Prime Minister Nawaz Sharif said on Saturday his PML-N party was the clear winner in Pakistan's general election and that he hoped for a majority to avoid a coalition. REUTERS/Damir Sagolj (PAKISTAN - Tags: TPX IMAGES OF THE DAY ELECTIONS POLITICS)
የምርጫ ዘመቻ- ፌስታምስል Reuters

13 05 13



በምጣኔ ሐብት ድቀት፥ በሙስና፥ በድንበር ዉዝግብም ግራ ቀኝ ትላጋለች።እንደ ሶማሊያ፥ እንደ ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ፥ እንደ ማሊ፥ እንደ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ፥ እንደ ሶሪያ፥ እንደ ኢራቅ፥ እንደ አፍቃኒስታን በርስ በርስ ጦርነት፥በሐይማኖት ሐራጥቃ አክራሪዎች ግጭት ትነፍራለች። እንደ ሁሉም የፅንፈኞች ሽብር፥ ግድያ፥ የሐያላን ግፊት ተፅዕኖ ያተረማምሳታል።ከሁሉም ተለይታ ግን ኑክሌር ታጥቃለች።በሁሉም ችግሮቿ መሐል፥ ከሁሉም ተቃርና እንደ ዲሞክራሲዉ ወግ መሪዋቿን መረጠች።ቅዳሜ።ፓኪስታን።የምርጫዉ ሒደት እና ዉጤት መነሻ፥የሐገሪቱ ጥቅል እዉነት ማጣቃሻ፥የሐያሉ ዓለም አቋም መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

ከሁለት ሺሕ አስራ-አንድ ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) እንደነበረበችበት ያለፈዉ ሳምንትንም በቦምብ ፍንዳታ፥ በሽብር ግድያ፥ ጀምራ በሽብር እልቂት አገባደደችዉ።የነበሩ ይናገራሉ፥ የቀበሩ ያረዳሉ።

«ANP እጩ አማን ማስዑድ እኔና ወንድሜ ከነበርንበት ሥፍራ እንደተቃረቡ፥ አካባቢዉ በድንገተኛ ፍንዳታ ተናወጠ።ወደ ሥፍራዉ ሩጬ ስደርስ፥አካባቢዉ በወደቁ ሰዎች ተሞልቷል።አንዳዶቹ እጅ-እግራቸዉ ተቆርጧል።ሌሎቹ ችንቅላታቸዉ ተበጥሷል።የቆሰሉትን ተሸክሜ ወደ ሆስታል ወሰድኩ፥ ምን እንደሆነ አላዉቅም።ወድሜም ሆስፒታል ነዉ።»

እንደ ሁለት ሺሕ ሰባቱ-ሁሉ ዘንድሮ በዚሕ ሳምንትም በሽብር፥ ግድያዉ መሐል የምርጫ ዘመቻ ነበር።


ዩናይትድ ስቴትስ የጀመረች፥ የመራችና ያስተባበረችዉ ዓለም አቀፍ ፀረ-ሽብር ዘመቻ ከኢራቅ እስከ ማሊ፥ ከኪጋሊ እስከ አዲስ አበባ፥ ከሞቃዲሾ እስከ ደማስቆ የተሰጠዉ ትርጉም፥ የአፈፃፀሙ እምዴትነት፥ ያጠፋና የሚያጠፋዉ ሕይወት ስንትነት በርግጥ ብዙ ያነግግር፥ ያጠያይቅ፥ ያወዛግባልም። በዘመቻዉ ያላበረ ወይም ለማበር ያልፈቀደ መንግሥት ግን በርግጥ የለም።

ተጠርጣሪ አሸባሪዎችን በተለይም የአልቃኢዳ እና የታሊባን አባላትና መሪዎችን በመያዝና በመግደል ደግሞ ፓኪስታንን የሚወዳደር ሐገር የለም።ፀረ-ሽብር ዘመቻዉን የጀመረችዉ፥ የመራችና ያስተባበረችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ከአፍቃኒስታን እስከ ኢራቅ ያዘመተቻቸዉ በርካታ ወታደሯቿ በአሸባሪዎች ጥቃት ተገድለዉባታል።አሸባሪዎች የገደሉባት ትልቅ ባለሥልጣን ግን አምባሳደር ናቸዉ።የቤንጋዚ-ሊቢያ አምባሳደሯ።

በአሸባሪዎች ጥቃት እዉቅ ትልቅ ፖለቲከኛዋን ያጣችዉ ብቸኛይቱ ሐገርም ያቺ ብዙ አሸባሪዎችን በመያዝ፥ በመግደል፥ ዓለምን የምትበልጠዉ ደቡብ ምሥራቃዊቱ ሐገር ናት።ፓኪስታን።ደግሞ በተቃራኒዉ አሸባሪዎችን ባለመያዝ፥ ወይም ሆን ብላ በመደበቅ በዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች በተደጋጋሚ የምትወቀስ፥ የምትተቸዉ እንደ ሐገር ከተፈጠረችበት ከ1947 ጀምሮ ከዋሽግተኖች ጉያ ያልተለየችዉ ሐገር ናት።ፓኪስታን።

«ፓኪስታንን እንዉጋ ብሎ ማንም አልተናገረም።እኔም ያልኩት እንዲሕ ነዉ፥ ዩናይትድ ስቴትስ አልቃኢዳ፥ ቢን ላደን፥ ከፍተኛ ባለሥልጣኖቹ ያሉበትን የምናዉቅ ከሆነ፥ እና ፓኪስታን እርምጃ ለመዉሰድ ካልቻለች፥ ወይም ካልፈደቀደች እኛ መዉሰድ አለብን።»

የያኔዉ እጩ፥ የዛሬዉ የሁለተኛ ዘመን ፕሬዝዳት ባራክ ኦቦማ በ2008ቱ የምርጫ ዘመቻቸዉ።አቦማ የምርጫ ዘመቻ ከመጀመራዉ አንድ ዓመት በፊት ፓኪስታን የምርጫ ዘመቻና ምርጫ ላይ ነበረች። ሽብርም በርግጥ አልተለያትም።ባለተለያት ሽብር በትደማበት፥ ባልተለያት ወቀሳ-ትችት በምትሸማቀቅበት፥ መሐል በተደረገባት የምርጫ ዘመቻ የቀድሞ እዉቅ መሪዋን ሕይወት ገበረች። ወይዘሮ ቤናዚር ቡቶን።ሕዳር ሁለት ሺሕ ሰባት።

ያም ሆኖ እጩ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ የትልቂቱን ሐገር ትልቅ ሥልጣን ለማይዝ እንደ ዉጪ መርሕ ካነጣጠሩበት ዋናዉ ፀረ-ሽብር ዘመቻዉን ከኢራቅ ነቅሎ ፓኪስታን ላይ መትከል ነበር።

«ፓኪስታን የማትተባበር ከሆነ እኛ መወሰን አለብን።አሁን ያለዉ ሥልት ትልቁ ችግር፥ ለአስር ዓመት ሙሸረፍን መንከባከባችን ነዉ።በዚሕ ሰበብ በፓኪስታን ሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነትን አጥተናል። ምክንያቱም ፀረ-ዲሞክራሲ በመሆናችን።(መርሐችን)፥እሱ አምባገነን ነዉ ግን የኛ አምባገነን ነዉ በሚለዉ የሐኛዉ ክፍለ-ዘመን አስተሳሰብ ላይ (የተመሠረተ) ነዉ።በዚሕም ምክንያት ፓኪስታን ዉስጥ ተዓማኒነት አጥተናል።አስር ቢሊዮን ዶላር አዉጥተናል።እነሱ ግን አል-ቃኢዳን አልተከታተሉም።ሥለዚሕም የአፍቃኒስታኑን ጦርነት ከጀመርን ወዲሕ እነሱ (አል-ቃኢዳዎች ከምንጊዜዉም በላይ ተጠናክረዋል።ይሕ እኔ የአሜሪካ ፕሬዝዳት ስሆን ይቀየራል።»

በርግጥም ኦባማ ፕሬዝዳት ሆኑ።ፓኪስታን ዉስጥም ብዙ ነገር ለበጎ-ይሁን ለመጥፎ ተየቀየረ።ኦባማ በተመረጡበት ዓመት-ሁለት ሺሕ ስምንት፥ የፓኪስታኑ ፕሬዝዳት ፔርቬዝ ሙሸረፍ የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን ለቀቁ።የሟቿ ጠቅላይ ሚንስትር የቤናዚር ቡቶ ባለቤት አሲፊ ዓሊ ዛርዳሪ ፕሬዝዳንት ሆኑ።

ኦባማ ምርጫ ዘመቻቸዉ እንደዛቱት የአሜሪካ ጦር ፓኪስታን ግዛት ዘልቆ እየገባ የታሊባንና የአል-ቃኢዳ ይዞታ የተባሉ አካባቢዎችን በሰዉ አልባ አዉሮፕላን በተደጋጋሚ ይደበድብ ያዘ።ኦባማ ሥልጣን የያዙበት ሁለተኛ ዓመት ሲቃረብ የዩናይትድ ስቴትስ ሰዉ አልባ የጦር ጄቶች የገደሉት የፓኪስታን ሕዝብ ሁለት ሺሕ መድረሱ ተዘገበ።አጥኚዎች እንደሚገምቱት እስካለፈዉ ሕዳር ድረስ የአሜሪካ ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች በተኮሱት ሚሳዬል የተገደሉት ፓኪስታናዉያን ቁጥር ከሰወስት ሺሕ አምስት መቶ ይበልጣል።

ግንቦት ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ። ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ በምርጫ ዘመቻቸዉ እንደዛቱት ለአሜሪካ ሕዝብ ትልቁን የአሜሪካ ጠላት ኦስማ ቢላደንን አቦታባድ-ፓኪስታን ዉስጥ ግዳይ ጣሉ።የሙሸረፍ መወገድ፥ የሰዉ አልባዉ አዉሮፕላን ጥቃት መጠናከር፥ የቢን ላደን መገደልም ኦባማ እንዳሉት የአሸባሪዎችን ጥቃት አለማዳከሙ ነዉ ዚቁ።

ከጥቅምት ሁለት ሺሕ አንድ እስካሁን በተቆጠረዉ አስራ-አንድ ዓመት ከመንፈቅ አሸባሪዎች ባደረሱት ጥቃት ሐምሳ ሺሕ ያሕል ፓኪስታናዊ ገድለዋል።ከመቶ ሺሕ በላይ አቁስለዋል።

ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ሐገራቸዉ ፓኪስታን ዉስጥ ለጀመረችዉ ፀረ-ሽብር ዘመቻ በአስር-አመት ዉስጥ አስር ቢሊዮን ዶላር ማዉጣትዋ ቆጭቷቸዋል። የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ እንደገመቱት ትንሺቱ፥ ደሐይቱ፥ ሐገር ፖኪስታን ግን ከሁለት ሺሕ አንድ እስከ ሁለት ሺሕ አስር በተቆጠረዉ ዘጠኝ ዓመት ዉስጥ ብቻ፥ የአሜሪካንን ጦርነት በመዋጋቷ ከስልሳ ሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ ሐብት ንብረት በአሸባሪዎች ጥቃት ወድሞባታል።

ሽብር፥ ጥፋት፥ ዉድመቱ በርግጥ ባለፈዉ ሳምንቱ ምርጫ መሐልም አላባራም።የፖለቲከኞች እገታም ታከለበት።

«አጥቂዎቹ ከዉስጥ ሆነዉ ተኩስ የከፈቱበት መኪና ጥቁር ነበር።ስድስት ሰዎች ተሳፍረዉበት ነበር።የሰሌዳ ቁጥሩን ግን አላዉቀዉም።»

ሐሙስ።ማዕከላዊ ፓኪስታን ሙልታን በተባለችዉ ከተማ ለእንደራሴነት ይወዳደሩ የነበሩት የቀድሞዉ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚንስትር የዩሱፍ ራዛ ጂላኒ ወንድ ልጅ ታገቱ።እስካለፈዉ ሰኔ ድረስ ፓኪስታኒን ለአራት ዓመት በጠቅላይ ሚንስትርነት የመሩት ጂላኒ እና ባለፈዉ ሐሙስ የታገቱት ወንድ ልጃቸዉ የፓኪስታን ሕዝብ ፓርቲ PPP አባል ናቸዉ።

ፒፒፒ-በሁለት ሺሕ ሰባት የተገደሉት የቤናዚር ቡቶ ፓርቲ ነዉ።የሙልታን አዉራጃ ፖሊስ ባለሥልጣን እንደሚሉት አጋቾቹ የታላቢን ደፈጣ ተዋጊዎች ወይም አሸባሪዎች መሆናቸዉ አያጠራጥርም።

«የአሸባሪዎች ጥቃት መሆኑ ምንም አያጠራጥርም።»

ፓኪስታን እንደ ሶማሊያ እንደ ኮንጎ፥ እንደ ኢራቅ፥ እንደ አፍቃኒስታን እንደ ሌሎቹም በአሸባሪዎች ጥቃት ትወድማለች።እንደ ኢትዮ-ኤርትራ በድንበር ግዛት ይገባኛል ከሕንድ ጋር እንድሜ ልኳን እንደተፋጠጠች ነዉ። ሠላም-አንድነቷን የሚጠብቅ የዉጪ ጦር ሐገሯ እንዲሰፍር ግን አልለመነችም።አልፈለገችምም።

በአሸባሪዎች ጥቃት፥ በአሜሪካኖች ድብደባ፥ ጥፋት ዉድመቱ መሐል ፓኪስታን በነፃነት ታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የሲቢል መንግሥት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ሳይወገድ ሙሉ ዘመነ-ሥልጣኑን አጠናቀቀባት።ጦሩ በዘንድሮዉ ምርጫ ፀጥታን ከማስከበር ሐላፊነቱ ንቅንቅ አላለም።

የኢዝላማባድ ፖለቲከኞች «መሪዎቻችን በአሸባሪዎች ሥለተገደሉ፥ ባልደረቦቻችን ሥለታገቱ» ወይም ከአወደ አፍሪቃ በተደጋጋሚ እንደምንሰማዉ «መስዋዕትነት» ሥለከፈልን የያዝነዉን ሥልጣን አንለቅም አላሉም።እንደ ባግዳድ፥ እንደ ካቡል፥ እንደ ሞቅዲሾ ፖለቲከኞች ቤተ-መንግሥት ተቀምጠዉ በወኪል፥ በራዲዮ፥ ቴሌቪዥን ንግግር፥ ወይም በጎሳ ተጠሪዎች ተመረጥን አላሉም።

እየሞቱ፥ እየታገቱ፥ እየደሙ እንደ ዲሞክራሲዉ ወግ በአደባባይ ተወዳደሩ።የምክር ቤት እንደራሴዎች የምርጫዉ ዘመቻ ከተሟሟቀበት እስከ ቅዳሜዉ ምርጫ በተቆጠሩት ስምንት ቀናት ዉስጥ አሸባሪዎች ባፈነዱት ቦምብ አንድ መቶ ሐምሳ ሰዎች ተገድለዋል።

የፓኪስታን ሕዝብ ግን አልተበገረም። የሽብር ሠላባ የሆኑ ወገኖቹን እየቀበረ፥ ቁስለኞቹን እያሳከመ መሪዎቹን መረጠ።ሕዝቡ፥ ፖለቲከኞቹም ቦምብ-ጥይት እየዘነበባቸዉ ለምርጫ መታደማቸዉ፥ የገለልተኛዉ አስመራጭ ኮሚሽን መሪ ፋክሩዲን ኢብራሒም እንዳሉት ለፓኪስታኖች ከዚያ በላይ አስደሳች ነገር የለም።

«በጣም በመደሰቴ ከየት እንደምጀምር አላዉቅም።ይሕን ቀን ሁላችንም ሥንናፍቀዉ ነበር።ሕዝቡ ለሥልጣን የሚበቃበትን ቀን።»

በምርጫዉ በርካታ አካባቢያዊና ብሄራዊ ፓርቲዎች ተወዳድረዋል።ዋንኞቹ ግን ሰወስት ናቸዉ።የቡቶዉ የፓኪስታን ሕዝብ ፓርቲ፥ (ፒፒፒ) ፥ የነዋዝ ሸሪፉ የፓኪስታን ሙስሊም ሊግ፥ ፒ (ፒ ኤም ኤል-ኤን፥) እና የቀድሞዉ እዉቅ የኪሪኬት ተጫዋች የኢምራን ካሕን ፓኪስታን ተሕሪክ-ኢ-ኢንሳፍ (ፒ ቲ አይ)።

ድምፁን መስጠት ከሚችለዉ ሰማንያ-ሥድስት ሚሊዮን ሕዝብ ሥልሳ ከመቶ ያሕሉ ድምፁን ሰጥቷል።እንደገና ያስመራጭ ኮሚሽኑ መሪ ፋክሩዲን ኢብራሒም።

«ለሕዝቡ ድምፅሕን ሥጥ፥ ድምፅሕን ሥጥ ማለታችሁን ቀጥላችኋል።ለሕዝቡ የመምረጥን አስፈላጊነት አሳያችሁት። እና ዉጤቱ ከሥልሳ ከመቶ የሚበልጥ ወይም ሥልሳ ከመቶ ያሕሉ ሕዝብ ድምፅ በመስጠቱ ሒደት ተካፍሏል።ከዚሕ በላይ ደስተኛ መሆኔን ከመግለፅ ዉጪ የምጨምረዉ የለኝም። ሁላችንም ደስተኞች ነን።ከባድ ሥራ ነበር።»

ጄኔራል ፔርቬዝ ሙሸረፍ በ1999 ከሥልጣን አስወግደዉ ያሠሯቸዉ፥ ከእስራት ፈተዉ ያሰደዷቸዉ የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትር ነዋዝ ሸሪፍ ደግሞ ከደስተኞቹ ሁሉ ደስተኛ ናቸዉ።አሸንፈዋልና። የፓኪስታን ምክር ቤት ሰወስት መቶ አርባ-ሁለት መቀመጫዎች አሉት።ከዚሕ ዉስጥ በሕዝብ ቀጥታ ድምፅ የሚመረጡ እንደራሴዎች የሚይዙት ሁለት መቶ ሰባ-ሁለቱን መቀመጫ ነዉ።

እስከ ዛሬ ይፋ በሆነዉ ዉጤት መሠረት የሸሪፍ የሙስሊሞች ሊግ ፓርቲ አንድ መቶ አስራ-አምስት መቀመጫዎችን አግኝቷል።ሸሪፍ ብቻቸዉን መንግሥት መመሥረት ባችሉም አሸንፈዋል።የድላቸዉ ሰበብ ምክንያት ከቱጃር የሚወለዱት ግን ሲታሰሩ፥ ሲፈቱ፥ ሲሰደዱ ዓመታት ያስቆጠሩት ቱጃሩ ፖለቲከኛ የወደመዉን የሐገሪቱን ምጣኔ ሐብት ለማሻሻሻል ቃል መግባታችዉ አንዱ ነዉ።ከታሊባኖች ጋር ለመደራደር ቃል መግባታቸዉ ሁለተኛዉ ምናልባትም ትልቁ።

«ባለፉት ጊዚያት ለዚች ሐገር ለዉጥ ያመጣዉ የሙስሊም ሊግ ነዉ።ለዉጥ ምን ማለት እንደሆነ ለሚያዉቀዉ ሁሉ፥ ለዉጥ ሊያመጣ የሚችለዉ አንድ ፓርቲ ነዉ።ያም ፒ ኤም ኤል-ኤን ነዉ።የዛሬዉ የመራጮች ትጋት የምንናገረዉ ለዉጥ ምን እንደሆነ ያሳየናል።»

አሉ የቀድሞዉ እና የወደፊቱ ጠቅላይ ሚንስትር ነዋዝ ሸሪፍ።ከታሊባኖች ጋር ለመደራደር ቃል በመግባታቸዉ ለተመረጡት ነዋዝ ሸሪፍ እና ለመራጩ የፓኪስታን ሕዝብ የደስታ መግለጫ በመላክ የዩናይትድ ስቴቱን ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማን የቀደመ የለም።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን ቀጠሉ።የአፍቃኒስታኑ ፕሬዝዳት ሐሚድ ካርዛይ አሰለሱ።ከዚያ ሁሉም።ሸሪፍ የገቡት ቃል፥ ሁሉም የተመኘት ገቢር ይሆን-ይሆን? ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ









A Pakistani resident casts her vote at a polling station in Islamabad on May 11, 2013. Pakistanis queued up to vote in landmark elections, defying Taliban attacks to cast their ballots in polls marking a historic democratic transition for the nuclear-armed state. AFP PHOTO / AAMIR QURESHI (Photo credit should read AAMIR QURESHI/AFP/Getty Images)
ምስል AMIR QURESHI/AFP/Getty Images
1----Different roads remained closed during election in provincial capital Peshawar as Militants threatened to sabotage the election process. Autor: Faridullah Khan
ፀጥታ ቁጥጥርምስል Faridullah Khan
A Pakistani election official empties a ballot box at the end of polling in Islamabad on May 11, 2013. Polling stations closed at 6:00 pm (1300 GMT) in Pakistan's historic general elections, which saw a "huge" turnout in the largest province of Punjab, an election commission official announced. AFP PHOTO / AAMIR QURESHI (Photo credit should read AAMIR QURESHI/AFP/Getty Images)
ምስል AAMIR QURESHI/AFP/Getty Images
Nawaz Sharif (C), leader of the Pakistan Muslim League - Nawaz (PML-N) political party, casts his vote for the general election at a polling station in Lahore May 11, 2013. A string of militant attacks cast a long shadow over Pakistan's general election on Saturday, but millions still turned out to vote in a landmark test of the troubled country's democracy. REUTERS/Mohsin Raza (PAKISTAN - Tags: POLITICS ELECTIONS TPX IMAGES OF THE DAY)
ምርጫ ነዋዝ ሸሪፍምስል Reuters
Security officials and residents are seen through the shattered windscreen of a damaged vehicle at the site of a bomb attack in Karachi May 11, 2013. A bomb attack on the office of the Awami National Party (ANP) in the commercial capital, Karachi, killed 11 people and wounded 35. At least two were wounded in a pair of blasts that followed and media reported gunfire in the city. REUTERS/Athar Hussain (PAKISTAN - Tags: POLITICS ELECTIONS CIVIL UNREST CRIME LAW)
የምርጫ ዘመቻ-የሽብር ጥቃትምስል Reuters
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ