1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ኢትዮጵያ እና ግብፅን እንዲያሸማግሉ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ ጠየቁ

እሑድ፣ ጥር 3 2012

በየካቲት የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ-መንበርነትን የሚረከቡት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያና ግብፅን እንዲያሸማግሉ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጠየቁ። ፕሬዝዳንት ራማፎሳ " ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጋር አጭር ውይይት አድርጊያለሁ። ከኢትዮጵያ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን አረጋግጠውልኛል" ብለዋል

https://p.dw.com/p/3W58T
Grand Ethiopian Renaissance Dam
ምስል picture-alliance/dpa/G. Forster

በመጪው የካቲት የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ-መንበርነትን የሚረከቡት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያ እና ግብፅን እንዲያሸማግሉ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጠየቁ። የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሶስቱ አገሮች ልዩነቶቻቸውን በውይይት ሊፈቱ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል እና አስተዳደር ጉዳይ ላይ ባደረጉት ድርድር ከሥምምነት ሳይደርሱ ተለያይተዋል። በባለሙያዎች ደረጃ ከተደረገው ድርድር በኋላ አንዳቸው ሌላውን የሚወቅስ መግለጫ አውጥተዋል።

የኢትዮጵያ፤ የግብጽ እና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ምኒስትሮች የአሜሪካ እና የዓለም ባንክ ታዛቢዎች በሚገኙበት የሚያደርጉት የመጨረሻ ውይይት ነገ በዋሽንግተን ዲሲ ይካሔዳል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በዛሬው ዕለት ወደ ዋሽንግተን ማቅናታቸውን መሥሪያ ቤታቸው ገልጿል።

ለጉብኝት ወደ ደቡብ አፍሪካ ያመሩት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግን ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ላይ በሚደረገው ድርድር አሸማጋይ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

"አሁን ያቀረብንው ጥያቄ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የኢትዮጵያ እና የግብጽ ጥሩ ወዳጅ ፤ ቀጣዩ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ-መንበር እንደመሆናቸው ከሁለቱም ወገኖች ጉዳዩን በሰላም እንዲፈቱ ውይይት ማድረግ ይችላሉ። ምክንያቱም ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው። ያለ ሰላም በአፍሪካ የልማት እና የዕድገት ርዕያችንን ማሳካት አንችልም። በዚህ ረገድ በመላው ዓለም ግንባር ቀደም ናቸው። ለዚያም ነው እንደ ወንድም እና እንደ ወዳጅ አገር ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳንን እንዲያሸማግሉ ጥሪ ያቀረብንው" ብለዋል ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በበኩላቸው ሶስቱ አገሮች ከአንዳች ስምምነት እንዲደርሱ የማመጣቸት ሚና ለመወጣት ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። የአባይ ወንዝ ለኢትዮጵያም ይሁን ለግብፅ ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ራማፎሳ መፍትሔ የሚበጅበት መንገድ ሊኖር ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።  ከግብፁ አቻቸው በጉዳዩ ላይ መመካከራቸው የተናገሩት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ ለውይይት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ "የኅዳሴ ግድብ ጉዳይ በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ውይይት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ጥሩው ነገር ሁለቱም አገሮች ለመወያየት እና መፍትሔ ለማበጀት ፈቃደኞች ናቸው። ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጋር አጭር ውይይት አድርጊያለሁ። ከኢትዮጵያ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን አረጋግጠውልኛል። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ በተመሳሳይ ለውይይት ዝግጁ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል። ስለዚህ መፍትሔ ሊገኝ ይችላል ብዬ አስባለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ኅብረትን እስከ መጪው የካቲት ድረስ በሊቀ-መንበርነት የሚመሩት የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታሕ አል-ሲሲ የሥልጣን ጊዜ ሲያበቃ ራማፎሳ አኅጉራዊውን ኅብረት የመምራት ኃላፊነት ይቀበላሉ። ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ኅብረቱን ከመጪው የካቲት ጀምሮ ለአንድ አመት በሊቀ-መንበርነት እንዲመሩ የተመረጡት በ32ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነበር።

እሸቴ በቀለ