1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፖለቲከኞች ይፈታሉ ማዕከላዊም ይዘጋል መባሉ 

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 25 2010

ዛሬ በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ የሚጠራው የምርመራ ማዕከል እንዲዘጋ መወሰኑን የጠቅላይ ሚንሥስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ድረ-ገፆች በኩል ይፋ አድርጓል። የተለያዩ ፖለቲከኞች እንደሚፈቱም ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/2qIB5
Äthiopien Online-Kampagne für Häftlinge
ምስል Tigist M./Befekadu Hailu

የፖለቲካ እስረኞች እና ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመ ኹኔታ እንዲፈቱ መወትወት ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥሯል። ጥሪው ሳይቋረጥ ለተደጋጋሚ ጊዜያት ተስተጋብቷል። «የኅሊና እስረኞች ይፈቱ» የሚለው ዘመም ከተደረገ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ነው ያለፈው። ዛሬ በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ የሚጠራው የምርመራ ማዕከል እንዲዘጋ መወሰኑን የጠቅላይ ሚንሥስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ድረ-ገፆች በኩል ይፋ አድርጓል። የተለያዩ ፖለቲከኞች እንደሚፈቱም ተገልጿል። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ይኽን ውሳኔ በተመለከተ ምን አይነት አስተያየቶች ተሰጡ? አስተያየቶቹን አሰባስበናል። 

ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንሥትር ጽ/ቤት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ገጾች ላይ ሠበር ዜና በሚል የወጣው መረጃ ብዙዎችን አስደምሟል። «በአቃቤ ሕግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙ የተለያዩ ፖለቲከኞች የተሻለ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዲሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ እንዲለቀቁ ተወስነኗል:: ጠቅላይ ሚኒስተር ሃይለማርያም ደሳለኝ» ይላል መልእክቱ። በአንድ ሰአት ልዩነት እዛው ትዊተር ገጽ ላይ ተመሳሳይ ግን ደግሞ መጠነኛ ለውጥ የተደረገበባቸው መልእክቶችም ተላልፈዋል። 

በኹለተኛው መልእክት ላይ «በእስር ላይ የሚገኙ» ከሚለው ሐረግ በተጨማሪ «የተፈረደባቸው የተለያዩ ፖለቲከኞችም» የሚልም ተካቷል። ቀደም ሲል «በይቅርታ እንዲፈቱ» የሚለው ደግሞ «በምህረት እንዲፈቱ» በሚል ተተክቷል። ቆየት ብሎ ደግሞ «የምህረት ህግና ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ እንዲፈቱ ይደረጋል::» የሚል ሌላ ተጨማሪ መልእክት ተላልፏል። 

 «በተለምዶ ማእከላዊ በመባል የሚታወቀው የምርመራ ማእከል እንዲዘጋ ተደርጎ ሙዝየም እንዲሆን» መወሰኑም በዛው በጠቅላይ ሚንሥትር ጽ/ቤት በትዊተርና ፌስቡክ ገጽ ላይ ተገልጧል። «በዓለማቀፍ ስታንዳርድና የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባፀደቀው የሰብአዊ መብት ድርጊት መርሃ ግብር መሰረት አዲስ የምርመራ ተቋም ተቋቁሞ በሌላ ህንፃ» ሥራ መጀመሩም በጽ/ቤቱ ተጠቅሷል። 

ሰሞኑን «የኅሊና እስረኞች» ይፈቱ በሚል መፈክር በተደረገው በይነ-መረብ (Internet)  ዘመቻ ከአስተባባሪዎቹ አንዱ የኾነው ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ ትዊተር ላይ በፍጥነት ሐሳቡን አንጸባርቋል። «ከበርካታ መስዋዕትነት ከተከፈለ በኋላ የቁም ስቅል መፈጸሚያው እንደሚዘጋ ቃል ተገብቷል። ያን መስማት ደስ ይላል። የሕዝብ ጥያቄ ኾነው የቀሩ በርካቶች ናቸው» ሲል በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትዊተር ላይ ጽፏል። 

ውሳኔው እጅግ ያስደመመው አኅመድ አብዱረኅማን ትዊተር ላይ «በህልሜ ነው በእውኔ ወይንስ በቴሌቪዥን?» ሲል ጠይቋል።  «በሀገሬ ተስፋ ልቆርጥ ትንሸ ሲቀረኝ ተስፋዬን የሚያለመልም ነገር ሰማሁ፡፡ እስኪ እውነት ያድርገው፡፡» ያለው ደግሞ ሠላዲን ነው እዛው ትዊተር ላይ። 

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ጉዳዮች ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋን «አለን፤ አለን» የሚል አጭር የትዊተር መልእክት ያያዘው ደግሞ ብሥራት ተሾመ ነው። «አለን» የሚለው ቃል የጠቅላይ ሚንሥትር ጽ/ቤት እስረኞችን ለመልቀቅ የመዘጋጀቱን ዜና ይፋ ካደረገ በኋላ መምጣቱ አስደንቆታል። የነገሮች በፍጥነት መቀያየር ጉዳይን በተመለከተም በመደነቅ «የማይተመን ነው!» ብሏል። 

እንዳልክ 2006 በበኩሉ ትናንት ባወጣው የትዊተር መልእክቱ፦ አቶ አዲሱ አረጋ በኦሮሚኛ «ጂራ» ማለትም «አለን» ብቻ የምትል መልእክት ማስተላለፋቸውን ትንታኔ ሰጥቶበታል። እንዳልክ በብዙዎች ዘንድ ሕወሓት አሸናፊ ኾኖ የወጣ ካስመሰለው የኢሕአዴግ መግለጫ በኋላ የተሰጠው የአቶ አዲሱ የትዊተር መልእክት «በኦህዴድ እና ህወሓት መካከል ያለው የኃይል ፍትጊያ ላለመቋጨቱ ማመላከቻ መኾኑን ገልጧል። 

የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ የሚለው ዜና ተግባራዊ የመኾኑ እውነትነት ያጠራጠራቸውም አሉ። ሙኒራ ትዊተር ላይ፦ «ነገሩ መግለጫውም በለጋ እድሜው ኤዲቲንግ በዝቶበታል..... እውነት እንዲሆን ዱዓ እናደርጋለን! ለሃገራችን መጪ ግዜ ጥሩ መረማመጃ የሚሆን ሃሳብ ነውና ሳይውል ሳያድር እውነት እንዲያደርጉት እመኛለው!» ብላለች። 

ከፖለቲካ እስረኞች ባሻገርም ጋዜጠኞች እና ጸሓፍት በአጠቃላይ የኅሊና እስረኞች እንዲፈቱ የሚተላለፈው ጥሪ ተበራክቷል።  ደብርሃን በትዊተር መልእክቱ፦ «ጦማሪያችን ዘላለም ወርቅአገኘኹ፤ እንደ እነ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ በቀለ ገርባ፣ ኦኬሊሎ አክዋይ፤ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲሁም ስምና መልካቸው የማይታወቅ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው እስረኞች ይፈታሉ ብለን እንጠብቃለን» ሲል ጽፏል። 

ማእከላዊ ሊዘጋ እና ሌላ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እስር ቤት ይገነባል መባሉን በተመለከተም የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። ጥቂቱን ለመመልከት ያኽል፦ «እምባዬን እየታገልኩ ነው የምጽፍላችሁ። "የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ይፈታሉ፤ ማዕከላዊ ፈርሶ ሙዚየም ይሠራል።" ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው ያሉት። አሁን ባስቸኳይ ይፈፀም። ድጋሚ በአመለካከት ልዩነት ሰዎች የማይታሰሩባት አገር ትፈጠር ዘንድ ዋስትና ይሰጠን። ያኔ አደባባይ ላይ አምቄ የቆየሁትን ለቅሶ ቆሜ አለቅሳለሁ።» የበፍቃዱ ኃይሉ የፌስቡክ መልእክት ነው።

«ደርግ 17 አመት ቢጠቀምበት ወያኔ ለስንት ዓመታት አሰቃየበት?» ያለው ሰለሞን ለገሰ ነው። ሰላም ፍቅር በበኩሏ «ትክክለኛ ውሳኔ ነው የታሰሩ ይለቀቁ» ብላለች። «ሥንት የማሰቃያ ቦታዎች አሉኮ ሥቃይ እየፈጸሙ በደርግ ማሳበብ ጥሩ አይደለም እናንተ ከደርግ ትብሳላችሁ እንጂ አትሻሉም !!!» የባይሳ ቶላ የፌስቡክ አስተያየት ነው። አስተያየቶቹ በርካታ ናቸው የተወሰኑትን ነበር ያቀረብንላችሁ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ