1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ

እሑድ፣ ጥር 20 2010

30ኛው የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ የህብረቱ መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ተጀምሯል። የዘንድሮው ጉባኤ ሙስናን በመዋጋት ላይ አተኩሯል።

https://p.dw.com/p/2rfpK
Versammlung der Afrikanischen Union in Addis Ababa
ምስል picture alliance/AA/M. Wondimu Hailu

የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤው እንደተለመደው ጠዋት ሳይሆን በሰዓታት ዘግይቶ ከሰዓት ላይ ነው የጀመረው። የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ላለፈው አንድ ዓመት የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሆነው ካገለገሉት የጊኒ ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ ኃላፊነቱን በይፋ ተረክበዋል። ዛሬ እና ነገ በሚካሄደው ጉባኤ ዋና የመወያያ አጀንዳ ከሆነው ሙስናን መዋጋት በተጨማሪ በፕሬዝዳንት ካጋሜ የተዘጋጀው የአፍሪካ ህብረት ማሻሻያም እቅድም መነጋገሪያ ይሆናል ተብሏል። 

በአዲስ አበባው ጉባኤ ከዚህ ቀደም እንደተለመደው በአህጉሪቱ ያሉ የጸጥታ እና የሰላም ችግሮች ትኩረት እንደሚሰጣቸው በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ያሉ የዶይቼ ቬለ ምንጮች ጠቁመዋል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪም በመክፈቻ ጉባኤ ላይ ባሰሙት ንግግር በአህጉሪቱ ካሉ ግጭቶች የደቡብ ሱዳንን አንስተዋል፡፡ ፋኪ በደቡብ ሱዳን “ለሰላም እንቅፋት የሚሆኑት ላይ ማዕቀብ መጣያ ጊዜው እየመጣ ነው” ብለዋል፡፡ ሊቀመንበሩ በንግግራቸው በደቡብ ሱዳን ያሉ ተቀናቃኝ ኃይሎች የሚያደርጉትን “የማይታመን ጭካኔ” እና “ትርጉም የለሽ ብጥብጥ” ብለውታል፡፡ ድርጊቱንም አውግዘዋል፡፡

የመሪዎቹ ጉባኤ የተለያዩ የጎንዩሽ ስብሰባዎችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያው  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ ከሱዳን፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ ፕሬዝዳንቶች ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ፣ የግብጽ እና የሱዳን መሪዎች በነገው ዕለት ተገናኝተው በአባይ ግድብ ዙሪያ እንደሚመክሩም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቋል፡፡ ስለ ዛሬው ጉባኤ በስፍራው የተገኘውን ዘጋቢያችን ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስን አነጋግረነዋል። ሙሉ ቃለ ምልልሱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ

ልደት አበበ