1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

123ኛው የአድዋ ድል

ቅዳሜ፣ የካቲት 23 2011

123ኛው የአድዋ ድል በአል በአዲስ አበባ ምኒልክ አደባባይ ከፍ ባለ የአከባበር ድምቀት ተከበረ፡፡ በአከባበሩ ላይ የጠገኙት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ የምናከብረው ነጻነት ሳይሆን ድላችንን ነው ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/3EMH5
Äthiopien Adwa Feier in Addis Abeba
ምስል DW/S. Muchie

የአድዋ ድል በዓል

123ኛው የአድዋ ድል በአል በአዲስ አበባ ምኒልክ አደባባይ ከፍ ባለ የአከባበር ድምቀት ተከበረ፡፡ በበአሉ ላይ ቁጥሩ የበዛ ለድሉ ዋጋ የሰጠ ህዝብ ኢትዮጵዊ ቀለም ያላቸው ህብረ ዝማሬዎችን፡ ሽለላ እና ፉከራዎችን፡ አርበኞቹን የሚያስታውሱ አልባሳትን በማድረግ በደመቀ ሁኔታ ሲዘክራቸው ውሏል፡፡

በአከባበሩ ላይ ብዙዎች ደስተኛ ሆነው አርበኞችንና ተጋድሎአቸውን በስፋት አወድሰዋል፡፡ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ስለ ሃገር ፡ ስለ ህዝብ ፡ ስለ ታሪክ ባንድ አቋም ልቡ የተሰለፈው የኢትዮጵያ ጀግና ህዝብ እንድነቱንና ህብረቱን አጠናክሮ በመጋደሉ ለዚህ ድል በቅተናል ሲል መልእክቱን በተወካዩ በኩል አስተላልፏል፡፡

Äthiopien Adwa Feier in Addis Abeba
ምስል DW/S. Muchie

በአከባበሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ የምናከብረው ነጻነት ሳይሆን ድላችንን ነው ብለዋል፡፡ ምክትል ከንቲባው ኢትዮጵያዊያን ለየትኛውም ፈታኝ ሁኔታ የማንገዛ፡ ድንቅ ፡ኩሩ ፡ ታላቅ ህዝቦች ነን ብለዋል፡፡ ለእናትና አባት አርበኞች ሁልጊዜ የተጋድሎ ወለታቸው ሊዘከር ይገባል ፡ ባገኘነው አጋጣሚ በማንኛውም መድረክ ላይ ድሉ የመላው አፍሪካ ብቻ ሳይሆን የጥቁሮች ሁሉ መሆኑን አብዝተን እናስተጋባለንም ብለዋል፡፡


ከዋና ከተማ አዲስ አበባ በ1 ሺህ አስር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አድዋ ከተማ ደግሞ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ወደስፍራው የሄዱ ወገኖች እና ባለስልጣናት እንዲሁም የውጭ ሀገር እንግዶች የበዓሉ ተሳታፊዎች እንደሆኑ የመቀለው ዘጋቢያችን ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ የላከልን ዘገባ ያመለክታል። ዛሬ ጠዋትም በስሎዳ ተራራ ሥር በተካሄደው ክብረ በዓል ላይ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ባደረጉት ንግግር የአድዋ ድል በመላው ዓለም ያስከተለውን ተፅዕኖ ጠቅሰዋል።
«ከአፍሪቃ እስከ አሜሪካ እና ካሬቢያን ምድር የነጻነት ፍላጎት ላይበገር ተቀጣጠለ። በባርነት ቀንበር ስር የነበሩት መላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦች እጅግ አሰቃቂ በሆነ በደል እና ረገጣ ሊቀጥሉ እንደማይችሉ በማመን ለአንዴ እና ለመጨረሻ በቅኝ ገዚዎች ላይ እንዲነሱ አድርጓቸዋል። »
ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ በበኩላቸው የዛሬውን የአድዋ የድል በዓል አስመልክተው በጽሑፍ ባስተላለፉት መልእክት የአድዋ ድል ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን በአድዋ ላይ በደም እና በአጥንት የከፈሉት መስዋዕትነት የዛሬው እና የነገው ትውልድ በቅኝ ግዛት ቀንበር ትከሻው ጎብጦ አንገቱን ሰብሮ እንዳይኖር እንዳስቻለው ዘርዝረዋል። 
 

Äthiopien Feierlichkeiten in Adwa
ምስል DW/M. Haileselassie

ሰለሞን ሙጬ/ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ

ልደት አበበ