1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

13ኛዉ የጀርመን አፍሪቃ የኤሌክትሪክ ኃይል ትብብር  መድረክ

ረቡዕ፣ መጋቢት 18 2011

13ኛዉ የጀርመን አፍሪቃ የኤሌክትሪክ ኃይል ትብብር  መድረክ ዉይይት ዛሬ  በሀምቡርግ ከተማ ተጀምሯል። ዉይይቱ እያደገ የመጣዉን የአፍሪቃ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በገንዘብ መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሚያተኩር መሆኑ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/3FlOB
German-African Energy Forum 2012
ምስል DW/C. Vieira

የተሻለ የአሰራር ዘዴ ፣ ዕዉቀትና ቴክኖሎጅ ያላቸዉ የጀርመን ድርጅቶች ወደ ስራ ይሰማራሉ።

ለሁለት ቀናት በሚዘልቀዉ በዚህ የዉይይት መድረክ የጀርመን ባለሀብቶች በአፍሪቃ የኃይል አቅርቦት ላይ የሚሳተፉበት ሥልትም ዉይይት ያደረግበታል። 
የጀርመን አፍሪቃ የትብብር መድረክ «ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ » የተሰኘዉ ማዕቀፍ አካል ሲሆን ጀርመን ለአፍሪቃ ከምታደርገዉ የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ የአህጉሪቱን የሀይል አቅርቦት ፕሮጀክቶችን በገንዘብ ለማገዝ የሚያስችሉ አዳዲስ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚዘጋጅ መሆኑን የአፍሪካና የጀርመን የንግድ ማህበር ገልጿል።
የኤለክትሪክ ሀይል አቅርቦት በአፍሪቃ በፍጥነት እያደገ ነዉ።በመሆኑም አፍሪቃ በተለይም ኢትዮጵያ ጀርመንን ከመሳሰሉ የካበተ ልምድ ካላቸዉ ሀገራት ድጋፍ ማግኘቷ ለኃይል ማመንጨትና ማሰራጨት ስራ ጠቀሜታዉ የጎላ መሆኑን በዉይይት መድረኩ ተሳታፊ የሆኑትና በርሊን በሚገኜዉ የኢትዮጵያ ኢምባሲ የኢኮኖሚና የቢዝነስ ዲፕሎማሲ ዘርፍ ሀላፊ አቶ እስክንድር ይርጋ ለ DW ገልፀዋል።ከዉይይቱ የሚጠበቁ ነገሮች መኖራቸዉንም አስረድተዋል።
«ከፎረሙ የሚጠበቁ ዋና ዋና ነጥቦች አሉ። ከነዚህም ዉስጥ ደረጃዉን የጠበቀ ልምድ እንዴት አድርገን ወደ አፍሪቃ የኃይል ማመንጨትና ስርጭት ዉስጥ እናስገባ የሚለዉ ነዉ።ሁለተኛዉ ይህንን እዉን ለማድረግ የሚያስችል የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እንዴት አድርገን ከጀርመን ወደ አፍሪቃ እናምጣ የሚለዉ ነዉ። ሦስተኛዉ ይንን የሚሰሩት የጀርመን «ካምፓኒዎች»በትብብር ወይም «በስፖንሰርሽፕ»ረገድ እንዴት አድርገዉ ወደ አፍሪቃ ይግቡ የሚለዉ ነዉ።»
ከዚህ አኳያ በጀርመን በኃይሉ ዘርፍ የተሻለ የአሰራር ዘዴ ፣ ዕዉቀትና ቴክኖሎጅ ያላቸዉ ድርጅቶች በኢትዮጵያ የኃይል ማመንጨት ስራ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ የማድረግ ግብ መኖሩንም አብራርተዋል።
በኃይል ማመንጨትና ማሰራጨት ስራ የተሰማሩ የጀርመን ኩባንዮች በአፍሪቃ በኃይል አቅርቦት ዘርፍ እንዴት ይሰማሩ በሚል ዉይይት መካሄዱንም አቶ እስክንድር አመልክተዋል።ይህም ኢትዮጵያ የኤለክትሪክ ሽፋንን ለማሳደግና በበቂ ሁኔታ ለዜጎቿ ለማዳረስ የያዘችዉን ዕቅድ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ማንኛዉም ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ ለሚደረግ ሽግግር የሀይል አቅርቦት ዋነኛ ግብዓት በመሆኑም በዚህ ዘርፍ የሚገኜዉ ድጋፍ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።          
እንደ አቶ እስክንድር ይህ የጀርመን ድጋፍ ሁለቱ ሀገሮች በአጋርነት ተያይዘዉ የሚያድጉበትን ሁኔታም ይፈጥራል። «የጀርመን መንግስት ለኢትዮጵያ የሚያደርገዉ የአንድ ወገን ሳይሆን ተያይዘን የምናድግበት «በፓርትነር ሽፕ»የእነሱም ድርጅቶች  ወደ ኢትዮጵያ መጥተዉ ትርፋማ የሚሆኑበት አዋጭ መስክ መሆኑ ስለተለየ ነዉ።»

German-African Energy Forum 2012
ምስል DW/C. Vieira

ዛሬ ሐምቡርግ ዉስጥ የተጀመረዉ 13ኛዉ የኃይል አቅርቦት መድረክ የጀርመን የመንግስትና ባለስልጣናትና የግል ባለሀብቶች እንዲሁም ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ35 የአፍሪቃ ሀገሮች የተወከሉ 55 ተሳታፊዎች የተገኙበት ነዉ። ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

 

ፀሀይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ