1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋህነን አባላት እጃቸውን ሰጡ

ሰኞ፣ ጥር 14 2010

የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ በምህጻሩ ጋህነን አመራር እና አባላት መሆናቸዉ የተገለፀ 148 ሰዎች እጃቸዉን ለመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መስጠታቸዉ ተገለጸ። የጋምቤላ ፕሬዚዳንት ጋትሉዋክ ቱት ዛሬ ለዶይቸ ቬለ እንደተናገሩት ለሦስት ወራት ከተካሄደ ድርድር በኋላ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነዉ።

https://p.dw.com/p/2rJ7Z
Karte von Äthiopien
ምስል DW/E.B. Tekle

የጋህነን አባላት እጃቸውን ሰጡ

የጋምቤላ ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ጋህነን)ቁጥር ሁለት በመባል የሚጠራው ቡድን አባላት ሰሞኑን ለኢትዮጵያ መንግሥት እጃቸውን ሰጥተው ወደ ሀገራቸዉ መመለሳቸው ተሰምቷል። ይህ የሆነውም ከቡድኑ ጋር በተደረሰ ስምምነት ነው። እጃቸውን ከሰጡት 148 የጋህነን ቁጥር ሁለት አመራር እና አባላት መካከል ከ 18 በላዩ ሴቶች እንደሆኑ የጋምቤላ ፕሬዚዳንት ጋትሉዋክ ቱት ዛሬ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። እንቅስቃሴውን በተመለከተ ሲያስረዱም  « እነዚህ ሰዎች ኤርትራ ውስጥ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው።  ወደ ደቡብ ሱዳንም የገቡበት ሁኔታ ነበር። » ብለዋል።ሺንዋ ዜና ምንጭ አማፂያን እንደሆኑ የጠቆማቸው እነዚህ ወገኖች በትክክል እነማን ናቸው? አላማቸውስ ምን ነበር? እንደ አቶ ጋትሉዋክ ገለፃ « ጋህነን ቁጥር ሁለት በተለይ ኤርትራ ውስጥ የተለያዩ ፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው። ጋህነን ቁጥር ሁለት የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ነው።»

Karte Äthiopien Südsudan Gambella Englisch
የጋምቤላ ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ አባላት በደቡብ ሱዳን እና በኤርትሪያ እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር

በተለያየ አካባቢ የነበሩትን የዚሁ የጋህነን ቁጥር ሁለት እንቅስቃሴ አባላትን ለማግባባት ጊዜ እንደወሰደ እና ከሦስት ወራት በኋላ ሰላም ፈጣሪ ስምምነት ላይ መደረሱን አቶ ጋትሉዋክ ተናግረዋል። « መንግሥታችን በሰላማዊ መንገድ ከእነሱ ጋር ከስምምነት እንዲደርሱ አድርጓል። አላማው  የሀገራችንን እና የክልላችንን ሰላም ለመጠበቅ ነው። እጃቸውን የሰጡት አባላትም ከጥር 11 ጀምሮ የተሀድሶ ስልጠና እየወሰዱ እንደሆነ እና ከስልጠናው በኋላ ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው እንደሚቀላቀሉ ፕሬዚዳንት ጋትሉዋክ አክለው ገልጸዋል።  

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ