1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

2ኛ ዓመቱን የያዘው የቡሩንዲ ቀውስ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 21 2009

የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን ለመወዳደር ከወሰኑ አሁን ሁለት ዓመት ሆናቸው። ፕሬዚደንቱ ይህን ውሳኔ ከደረሱ እጎአ ሚያዝያ 2015 ዓም ወዲህ ሀገሪቱ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች፤ በሁለት ዓመቱ ሁከትና ግጭት የሞተው ሰው ቁጥር 3000፣ በኃይል የታፈኑት 1000፣ የታሰሩት ደግሞ 8000 ደርሷል።

https://p.dw.com/p/2c69F
Burundi Proteste gegen Präsident Nkurunziza Demonstration
ምስል Getty Images/AFP/J. Huxta

Fokus Afrika A 29.04.2017 - MP3-Stereo

በቡሩንዲ ተቃዋሚ ቡድን ዘገባ መሰረት፣ የወጣት ሚሊሺያ ቡድኖች፣ በተለይ ኢምቦኔራኩሬ የተባለው የገዢው ፓርቲ  « ሲኤንዲዲ/ኤፍዲዲ » ፓርቲ  የወጣት ክንፍ አባላት እጅግ  አሁንም የሀገሪቱን ህዝብ የማስፈራራት ተግባራቸውን ቀጥለዋል። ሕዝቡ የፕሬዚደንቱን ለተጨማሪ ዘመነ ስልጣን የመወዳደርን ውሳኔ ያኔ አደባባይ በመውጣት አጥብቆ ነበር የተቃወመው። አሁን ግን ሁኔታው ተቀይሮ ማንም ተቃውሞውን በግልጽ የማያሳይበት ጊዜ እንደመጣ በመዲናይቱ ቡጁምቡራ በሚገኘው የኒካቢጋ የተባለው የተቃዋሚው ቡድን ጠንካራ ሰፈር ነዋሪ የሆነው ጄምስ ካናኒ አስታውቋል። በከተማይቱ የፖሊስ ቁጥጥር መጠናከሩን የገለጸው ጄምስ፣ ሰዎች በኃይል ታፍነው እንደሚወሰዱ እንደሚሞቱ በየቀኑ ከሚቀርቡ ዜናዎች እንደሚሰማ አመልክቷል።
 የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት፣ በምህፃሩ «ዩኤንኤችሲአር» እንዳስታወቀው፣ ከ400,000 የሚበልጡ የቡሩንዲ ዜጎች ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል።  በተለይ፣ የቡሩንዲ ወጣቶች ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ  መሆኑን ነው የውጭ ታዛቢዎች እና የሀገሪቱ ዜጎች የሚናገሩት።  በመሆኑም፣  አንዳንዶች  ተሳክቶላቸው  ሀገር ለቀው መውጣት ችለዋል፣ አንዳንዶች ግን የት እንደደረሱ አይታወቅም።  ምናልባት የዓማፅያን ቡድኖችን ተቀላቅለው ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፣ ይህም ታድያ፣ በ ኒካቢጋ በእጅ ሙያ የተሰማራው ዦን ክሎድ ካሬጌያ እንደሚለው፣ በቡሩንዲ ዜጎች ዘንድ  በሀገሪቱ በማንኛውም ጊዜ ጦርነት ሊጀመር ይችል ይሆናል የሚለውን ስጋት ፈጥሯል።
ፎቶ አንሺው እና የመብት ተሟጋቹ ቴዲ ማዛኒም ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ያቋቋሙዋቸው ሚሊሺያዎች በርዋንዳ የጎሳ ጭፍጨፋ በተካሄደበት እጎአ በ1994ዓም  ይሰማ የነበረውን ጥላቻ የሚፈጥረውን ዓይነት አነጋገር ዛሬም በመላይቱ ሀገር በማስፋፋት ላይ እንደሚገኙ ለዶይቸ ቬለ ገልጾ፣ ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን  አስታውቋል። 
« ቡሩንዲ በመንግሥት፣ በፖሊስ እና በጦር ኃይሉ ጥብቅ ቁጥጥር ስር የምትገኝ ሀገር ናት።  መንግሥት በብሄራዊ ደረጃ ያስፋፋው ሽብር  እጅግ ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ የቡሩንዲ ዜጎች መናገር እንኳን አይችሉም፣ በቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ኔልሰን ማንዴላ ርዳታ በአሩሻ ታንዛንያ የሰላም ስምምነት ገንብተነው የነበረው ዴሞክራሲያዊ  ስርዓት ጨርሶ ጠፍቷል። የፕሬስ፣ ሀሳብን በነፃ የመግለጽ ነፃነት የለም። ማንም ከአንድ ግዛት ወደ ሌላ ግዛት በነፃ መዘዋወርም አይችልም። »
የቡሩንዲ ሕዝብ በስቃይ ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ጊዜ ጀርመን ወደ ቡሩንዲ አንዳችም የገንዘብ ርዳታ እንዳትልክ ማዛኒ ተማፅኗል፣ ምክንያቱም፣ ይህ ዓይነቱ ርዳታ ለሀገሪቱ ሕዝብ ስቃይ መባባስ ተጠያቂ የሆኑትን የጦር ጀነራሎችን ኪስ ከመሙላት ባለፈ፣ በርግጥ ርዳታው ለሚያስፈልገው ሲቭል ሕዝብ ጥቅም አይውልም።  
የምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ አባል ሀገራት ፣  በጎርጎርዮሳዊው ግንቦት 10፣ 2017 ዓም በታንዛንያ የዳሬሰላም ከተማ  ጉባዔ ያካሂዳሉ፣ በፈረንሳይ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተመልካች ተቋም ተንታኝ ቲየሪ ቨርኩሎን  ፣ ይህን ስብሰባ በቡሩንዲ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የቀጠለውን ውዝግብ ለማብቃት የሚቻልበትን መፍትሔ ለማፈላለግ ጥሩ አጋጣሚ አድርገው ተመልክተውታል።  የሀገራቱ መሪዎች በዳሬሰላም ዓቢይ ጉባዔአቸው ላይ የጎረቤት ቡሩንዲን ውዝግብ   ዋነኛ  የመወያያ አጀንዳ ማድረግ ይገባቸዋል።   
« የምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ አባል ሀገራት ይህን ካላደረጉ ግን፣  እየተካረረ የሄደውን የቡሩንዲን ቀውስ ለማርገብ  አንድ ሁነኛ ርምጃ መውሰድ የሚችሉበት አጋጣሚ መና  ይቀራል ማለት ነው። »
እንደ የምሥራቅ አፍሪቃ አጥኚ ቲየሪ በርኩሎን አስተያየት የቡሩንዲን ቀውስ ለማብቃት የተደረጉት ዲፕሎማሲያ የሽምግልና ጥረቶች ሁሉ አንዳችም ፋይዳ አላስገኙም፤ ሁከቱም ቀጥሏል።   ምክንያቱም፣ ይላሉ ቨርኩሎን፣
«« መከፋፈል የሚታይበት የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤትን የመሰለ አንድ ዓለም አቀፍ አካል ለቡሩንዲ ውዝግብ መፍትሔ በማፈላለጉ ጥረት ላይ በሌላው የተከፋፈለ ዓለም አቀፍ አካል፣ ማለትም፣ በምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ  ላይ  ጥገኛ ሆኗል።  በዚህም  የተነሳ  ጥረቱ ውጤታማ ሊሆን  አይችልም። »
ቨርኩሎን እንደሚሉት፣ ምሥራቅ አፍሪቃውያኑ የተካረረውን የቡሩንዲ ቀውስ ማርገብ ካልቻሉ  ሀገሪቱን የማረጋጋቱ ሂደት ሊጀመር አይችልም፣ አሁን እንደሚታየው፣ የዚችው ምሥራቅ አፍሪቃ ሀገር ቀውስ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ከሞላ ጎደል ተረስቷል። በዚህም የተነሳ እስከ ጎርጎርጎሪዮሳዊው 2017 ዓም መጨረሻ ድረስ ከቡሩንዲ የሚሰደደው ሰው ቁጥር በጉልህ እንደሚጨምር እና የሀገሪቱ ሕዝብ ኤኮኖሚያዊ ሁኔታም ይበልጡን እንደሚበላሽ ቨርኩሎን ጠቁመዋል። የቡሩንዲ ሕዝብ በወቅቱ በወባ በሽታ እና ባልተመጣጠነ አመጋገብ  የተጎዳ ሲሆን፣ የምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ አባል ሀገራት የቡሩንዲን ቀውስ ለማብቃት ጥረታቸውን ካላጠናከሩ ሁኔታዎች እየከፉ መሄዳቸው አይቀርም። በቲየሪ ቨርኩሎን ግምት መሰረት፣ ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛም እስከ 2020 ዓም ድረስ በስልጣን ላይ መቆየት እንዲችሉ በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ላይ ያቀዱትን ለውጥ ተግባራዊ ማድረጋቸው አይቀርም።

Pierre Nkurunziza
ምስል I.Sanogo/AFP/GettyImages
Logo Ostafrikanische Gemeinschaft EAC
UNHCR Südsudan Flüchtlinge
ምስል Getty Images/AFP/I. Kasamani
Burundi Imbonerakure Miliz
ምስል Getty Images/AFP/C. de Souza

አርያም ተክሌ/ማርቲና ሽቪኮብስኪ

ማንተጋፍቶት ስለሺ