1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

2010፤ ዓለም አቀፉ የብዝኀ-ህይወት መታሰቢያ ዘመን፣

ረቡዕ፣ ጥር 12 2002

በዓለም ዙሪያ ድን እጅግ እየተመናመነ ነው። እ ጎ አ ከ 1990 -2005 ዓ ም ብቻ 3 ከመቶ የቀነሰ ሲሆን በየዕለቱ በአማካዩ፣ 20,000 ሄክታር ደን የለበሰ መሬት ምድረበዳ ይሆናል ማለት ነው።

https://p.dw.com/p/Lbwa
2010፤ ዓለም አቀፉ የብዝኀ-ህይወት መታሰቢያ ዘመን፣
ምስል AP

በየዕለቱ በተጨማሪ 150 የተለያዩ የዱር ነፍሳትም ሆኑ እንስሳት ከገጸ ምድር በመጥፋት ላይ ናቸው። በሌላ በኩል፣ የተባበሩት መንግሥታት አጠቃላይ ጉባዔ ካባታ ዛሬ 20 ቀን የሆነው 2010 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት የብዝኀ-ህይወት ዘመን ተብሎ እንዲታሰብ መወሰኑ የታወቀ ነው። በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን፣ ብበብዝኀ-ህይወት ይዞታ ላይ እናተኩራለን፤ በቅድሚያ ግን ከሳይንስ ነክ ዜናዎች በጥቂቱ---

* የምድራችን የሙቀት መጠን አሁን ባለው ደረጃ ከቀጠለ ፣ አፍሪቃ ውስጥ በእጅግ ከፍተኛው ተራራ ኪሊማንጃሮ ጉልላት ላይ የሚገኘው የተቆለለ በረዶ ከእነአካቴው ቀልጦ ይጠፋል የሚል አስፈሪ ዜና በኮፐንሄገኑ ጉባዓ ዋዜማ አካባቢ ተሰምቶ እንደነበረ የሚታወስ ነው። የኪሊማንጃሮ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም ውስጥ የረጅሙ ተራራ ሂማላያም ሆነ ኤቨረስት በረዶም እ ጎ አ እስከ 2035 ዓ ም ፣ ሟምቶ ሊጠፋ ይችላል የሚለው ዜና፣ በህንድ መንግሥትና በተባበሩት መንግሥታት የበይነ-መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ተመልካች የምርምር ቡድን (IPCC )መካከል ቅራኔ ፈጥሯል። እ ጎ አ በ 2035 ዓ ም በረዶ ከሂማልያ ተራሮች ይጠፋል አሉ የተባሉት ህንዳዊው የበረዶ ጥናት ሊቅ ሰይድ ሐስኔንግን ሐሰት ሲሉ ቃላቸውን ሰጥተዋል። እኔ ያልኩት አሉ ሐስኔን፣ «እኔ ያልኩት በሚመጡት 40 እና 50 ዓመታት ውስጥ የበረዶው ክምር ይመናመናል ነው። ይጠፋል፣ ወይም የሚቀረው በ 2 ወይም ግማሽ ኪሎሜትር ቦታ ላይ የተከመረ በረዶ ይሆንል የሚል ቃልም አልወጣኝም» ሲሉ በዛሬው ዕለት በህንድ ቴሌቭዥን ገልጸዋል። ሳይንሳዊ ግኝትን በተመለከተ፣ ተዓማኒነት ያላቸው ዜናዎች በሚገለጡበት Peer Review Journal በተሰኘው መጸሔት፣ 2035 ም ሆነ ይህን የሚመለከት የሐስኔን መግለጫ እንዳልወጣ ቢነገርም፣ እ ጎ አ በ 1999 ዓ ም New Scientist የተሰኘው መጽሑት ባደረገላቸው ቃለ-ምልልስ፣ «የሂማልያ፣ በረዶ እየተኮማተረ ነው ጥናቴም ፣ እስከ 2035 ሊጠፋ እንደሚችል ያመላክታል» ማለታቸው ተገልጿል ቃለ-ምልሱም በኢንተርኔት ይገኛል ነው የተባለው። ይህን ያስተባበሉት ሐስኔን፣ « እኔ ኮከብ ቆጣሪ ወይም ጠንቋይ አይደለሁም፣ በ 2035 ወይም 2040 የሂማላያ የበረዶ ክምር ሟምቶ ይጠፋል» የምል አይደለሁም ሲሉ ተከራክረዋል። ሳይንቲስቱ የሚሠሩት፣ ኒው ደልሂ ውስጥ፣ የ IPCC ሊቀመንበር ራጀንድራ ፓቾሪ በሚመሩት ፣ የኃይል ምንጭና የተፈጥሮ ሀብት ተቋም በተሰኘው ድርጅት ውስጥ ነው።

* በሽታ አስተላላፊ ተኀዋስያንን በፍጥነት የሚገድል መድኀኒት በጀርመናውያን ሳይንቲስቶች መፈልሰፉ ተነገረ። መድኃኒቱ፣ እጅግ አደገኛ ተኀዋስያን በሆስፒታሎች እን ያስፋፉ የሚገታ መሆኑን ጠበብቱ አያይዘው ገልጸዋል። በበርሊን የሚገኘው የ ሮበርት ኮኽ ተቋም እንዳስታወቀው፣ ተኀዋስያንን በፍጥነት የሚያጠፋው መርዝም ሆነ መድኃኒት ከቀዶ ጥገና መሣሪያዎች የሚያስወግድ ሲሆን ፣ መሣሪያዎቹ አሲድነት ባለው መድኃኒት ከጥቅም ውጭ አይሆኑም።

* Royal Society የተሰኘው የብሪታንያ የሳይንስ አካዳሚ ማኅበር ፣ ከትናንት በስቲያ ለመጀመሪያ ጊዜ 250 ዓመት የሞላውን እውቁ ሳይንቲስት አይዛክ ኒውተን የስበትን ኃይል ነባቤ-ቃል እንዲቀምር ያበቃውን ከዛፍ ላይ የአንድ ቱፋ ፍሬ ሲወድቅ የታዘበበትን ጽሑፍ ህዝብ ይመለከተው ዘንድ በኢንተርኔት ይፋ ማድረጉ ተገለጠ። ከዛፍ የሚወድቅ ፍሬ ለምን ወደላይ ወይም ወደ ጎን አይወድቅም፣ ለምን በቀጥታ ከላይ ወደታች ወደምድር ይወርዳል? ምክንያቱ፣ ኒውተን ተመራምሮ እንደደረሰበትና በሳይንሱ ዓለም ከዚያ ወዲህ በይፋ እንደሚታወቀው፣ ፍሬውን መሬት ስለምትስበው ነው፣ በቀጥታ ከዛፍ ላይ ወደ መሬት የሚወድቀው። ከተቋቋመ 350 ዓመት የሆነው የብሪታንያው የሳይንስ አካደሚም ሆነ ተቋም የኒውተንን የምድር ስበት ነክ ጽሑፍ፣ እ ጎ አ 1752 የሳይንቲስቱን የህይወት ታሪክ የጻፈውን የ William Stukeley ሥራ እማኝ በማድረግ ፣ በኢንተርኔት፣ www.royalsociety.org/turning-the-pages

በተሰኘ ድረ-ገጽ አቅርቧል።

2010 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት ፣ ዓለም አቀፍ የብዝኀ-ህይወት መታሰቢያ ዘመን ለመባል የበቃው፣ እ ጎ አ በ 1992 ዓ ም፣ በሪዮ ዴ ጃኔሮ በተካሄደው በተባበሩት መንግሥታት የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃና ልማት ጉባዔ በተለመው መሠረት ነው። ያኔ፣ በምድራችን የሚገኙ የእንስሳትና ዕጽዋት ዓይነቶች እንዲጠበቁ ስምምነት መደረጉም የሚታወስ ነው። ዘንድሮ፣ ከዚሁ ዓለም አቀፍ የብዝኀ-ህይወት መታሰቢያ ዘመን ጋር ተያይዞ አዝርእት፣ እጽዋትና እንስሳት የሚጠበቁበት እርምጃ በተግባር ይገለጥ ዘንድ ላቅ ያለ ትኩረት የሚያገኝበት ጊዜ ይሆናል ተብሎ ነው የሚጠበቀው። ታዲያ የብዝኀ ህይወት ጉባዔዎች ፐሬዚዳንት የሆነችው ጀርመን ፣ የተግባር ዓመት በተሰኘው መፈክር ሥር ፣ በመጀመሪያ ዐቢዩ ዓለም አቀፍ የብዝኀ-ህይወት ጉባዔ፣ ከጥር 17-21 2002 ፓሪስ ፣ፈረንሳይ ውስጥ የሚካሄድ ሲሆን፣ በዚያ ጉባዔ፣ ፖለቲከኞች፣ የሳይንስ ጠበብት፣ የባህል ተጠሪዎች ጭምር ይመክራሉ። ጉባዔው፤ በምድራችን የሚገኙ እጽዋትንና እንስሳትን ዘንድሮ ብቻ ሳይሆን ምንጊዜም ከርሞና ከዚያም በኋላ መጠበቅ እንደሚገባ በአጽንዖት ሳያሳስብ እንደማይቀር ነው የሚነገረው። ጉባዔው፣ ከየአየር ንብረት ለውጥ ጋር፣ ብዝኀ-ህይወትን ለመጠበቅ ስለሚያስፈልግ ገንዘብ በሰፊው ሳይመክር አይቀርም። ከዚያም፣ ከመጋቢት 12 ቀን 2002 ዓ ም፣ አንስቶ ለ 3 ቀናት፣ በዶሃ ፣ ቓታር ፣ በዋሽንግተኑ የአዝርእትና እጽዋት ጥበቃ የስምምነት ሰነድ የፈረሙት 175 አገሮች ለ 15ኛ ጊዜ ይሰበሰባሉ።

ግንቦት 13 ፣ 2002 በኒው ዮርክ፣ የሚዘጋጀው ዐቢይ ጉባዔ፣ ከድግሱ ሌላ፣ የብዝኀ-ህይወት ጥበቃ ተግባር፣ በአቅድ በሚመራበት ሁኔታ ላይ ይሆናል የሚያተኩረው። መስከረም 10,2003 ፣ እጽዋትንና እንስሳትን በመጠበቅ ረገድ ፣የተባበሩት መንግሥታት አጠቃላይ ጉባዔ 3ኛ ዘገባ ይቀርባል። በዚህ ረገድ፣ በምዕተ-ዓመቱ ስለሚፈጸሙት ተግባራትም ውሳኔ በድምጽ ብልጫ እንደሚተላለፍ ይጠበቃል። ኅዳር 30 ቀን 2003 ፣ ካናዛዋ ጃፓን ውስጥ የብዝኀ-ህይወቱ ጥበቃ መታሰቢያ ዘመን፣ በልዩ ሥነ ሥርዓት ይደመደምና ፣ ቀጣዩን ዘመን በደን ላይ ለማትኮር ዝግጅት ይደረጋል::

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የብዝኀ-ህይወት መፈክር ፣ ብዝኀ-ህይወት፣ ህይወት ነው። ብዝኀ-ህይወት ህይወታችን ነው የሚል ነው። አንተ እርሶ ብዝኀ ህይወት ነህ፣ ነሽ። አብዛኛው የምትተነፍሱት ንጹህ አየር (ኦክስጅን)፣ በዓለም ዙሪያ ፣ በወቅያኖሶች ካሉ ጥቃቅን የአትክልት ዓይነቶች የሚገኝ ሲሆን፣ የአልኮል መጠጡን የምታገኙት ከደን ነው። የምትበሉት ፍራፍሬና ቅጠላ-ቅጠል ፣ ንቦች የላሱት ነው። የምትጠጡት ውሃ፣ ግዙፍ ሉላዊ ዑደት ያለው ነው። ደመና፣ ዝናም ፣ በረዶ ፣ ወንዞችና ወቅያኖሶች---

ጽልመታዊ አመለካከት አላቸው የሚባሉ የሥነ-ፍጥረት ጠበብት፣ የሰው ልጅ በምድራችን የተለያዩ እጽዋትና እንስሳት ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጦርነት የከፈተው ካለፉት 12,000 ዓመታት ወዲህ ነው ይላሉ። በአሁኑ ጊዜ፣ በያመቱ 140,000 የአጽዋትና እንስሳት ዘር ነው የምናወድመው። እ ጎ አ በ 2050፣ በምድራችን ከሚገኘው የአጸድና እንስሳት ዓይነትና መጠን 30 ከመቶ የሚሆነው ይወድማል። ከዓለም ህዝብ መካከል ገሚሱ፣ ከተፈጥሮ አካባቢ ርቆ በከተሞች የሚኖር እንደመሆኑ መጠን፣ የሚገለገልባቸው ቁሳቁሶች፣ በንጽህና የታሸጉ እንደመሆናቸው መጠን ከየት እንደተገኙ እንኳ ልብ ብሎ አያጤነውም። ከዕበይት የችግር ዓይነቶች ከተሞች በግንባር-ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው። የብዝኀ ሥነ ህይወት ስምምነት ዋና ጸሐፊ አህመድ ጆጋልፍ እንዲህ ያላሉ።

«አሁን ፣ ይበልጥ ተፈጥሮን እየጎዳ በሚስፋፋ የከተማ ህይወት ነው ኑሮአችንን የምንገፋ። ስለዚህ፣ ለኑሮ፣ በሚመጡት ዓመታት የሚደረገው ትግል፣ በከተሞች ውስጥ ድል ይቀዳጃል ወይም ይከስማል። »

የብዝኀ-ህይወትን ማስታወቂያ በተመለከተ የሚደረገው ዘመቻ፣ ከዓመቱ ተግባራት ጋር ሲነጻጸር ኢምንት ነው። ትክክለኛው ትግባር የሚከናወነው፣ በርሊንን፣ ፓሪስን ፣ ባሊን፣ ናይሮቢንና ኒው ዮርክን በመሳሰሉ ከተሞች በሚካሄዱ ሳይንሳዊ ጉባዔዎችና የፖለቲካ ውይይቶች ነው። ግን ጀርመናዊው፣ የብዝኀ-ህይወት ጠቢብ ፣ ማግኑስ ቬዘልእንዳሉት ለተንሰራፉና ለተንዛዙ ለመገንዘብም ለሚያዳግቱ ችግሮች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ መፈክር በመሰለ ሁኔታ መላ መፈለጊያ ዓመቶች እያስመሰለ የሚያቀርባቸው ስያሜዎች በአርግጥ ምን ፋይዳ አላቸው በማለት የአንክሮ ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ ፣ እኒሁ፣ Naturschutz Bund Deutschland(NABU)የተሰኘው ድርጅት የምርምር ባለሙያ ራሳቸው ምላሹን ሰጥተዋል።

«ነጥቡ ያለው፣ መገናኛ ብዙኀን በሰፊው ያነሱ-ይጥሉት የነበረው የኮፐንሄገኑ ጉባዔ ከከሸፈ ወዲህ፣ በእርግጥ ትንሽም ቢሆን ሰው በመጠራጠር፣ ዐቢይ ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች ምን ውጤት ያስገኛሉ ሲል መጠየቁ አይቀርም። ያም አለ፣ ያም አለ !፣ በመጨረሻ ፣ ፖለቲከኞች ፣ ህዝቡ የሚጠይቀውንም ሆነ ተጨባጭ ሁኔታዎች አጉልተው የሚያሳዩትን ጉዳይ አይፈጽሙም። ስለሆነም፣ ሰዎች፣ ዓለም አቀፉን የብዝኀ-ህይወት መታሰቢያ ዘመን አስመልክተው፣ በእርግጥ ይህ በትክክል ምን በጎ ነገር ያስገኛል ብለው ቢጠይቁ አያስደንቀኝም። »

ተክሌ የኋላ፣ ሂሩት መለሰ