1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

2011 መልዕክት፦ እቅድና አለም

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 25 2003

የኑክሌር የታጠቀችዉ ፓኪስታን እንደተዝረከረከች፥ አፍቃኒስታን እንደተሸበረች አለም አቀፉ ሕብረ ብሔር ጦር ዘንድሮ ሐምሌ ከአፍቃኒስታን መዉጣት ይጀምራል-ነዉ የአዲሱ አመት እቅድ ምግባር ተቃርኖ አብነት።

https://p.dw.com/p/QmB7
ምስል DW

03 01 11


ፕሬዝዳንት ማሕሙድ አሕመዲንጃድ ለክርስትና ሐይማኖት መሪዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልክት አስተላለፉበት።ኪም ጆንግ ኢል ለሠላም ዝግጁ ነታቸዉን ገለጡበት።አክራሪ-ነዉጠኛ የሚባሉት የሁለቱ መሪዎች መልዕክት ያንጀት-ያንገትነቱ ሲያከራክር-ቤኔዲክት አስራ-ስድስተኛ የዓለም ሐይማኖቶች መሪዎች ሥለ-ዓለም ሠላም የሚመክሩበትን ጉባኤ ጠሩበት።ጥሪ-አላማዉ ሲተነተን ባግዳድ የኖረችበት፣ ጆስ የለመደችዉ መጥፎ-አሌክሳንደሪያን ነዘራት። የጎሮጎሮሳዉያኑ ሁለት-ሺሕ አስራ አንድ።ፕሬዝዳት ኦባማ ጦራቸዉን ከአፍጋኒስታን የሚያስወጡበት አመት አንድ ሲል--የመጀመሪያ ሰለቦቹን እያስቆጠረ።ዛሬ ሰወስተኛ ቀኑ።የአለም መሪዎች የአዲስ አመት መልዕክት-ምንነት፣ የአለም ጉልሕ እዉነት እንዴትነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁኝ ቆዩ።

የእርግር ኳስ -ክሂል-ችሎታዋ ምጥቀትን የአምባገን መሪዎችዋ አገዛዝ፥ የአንደንዛዥ ዕፅ ነጋዴዎችዋ-ወንጀል-ግድያ እንደቀጨጩባት፣ የሳንባ ዳንኪራዋን ፌስታዋን የወንበዴዎችዋ ሌብነት ዘረፋ- እንዳጨለመባት፣ የተፈጥሮ ሐብት-ዉበቷን የድሆችዋ ጉስቁልና እንደጀቦነባት-ዘመነ ዘመናት ያስቆጠረችዉ ብራዚል እኩይዋን ያሰናበቱላትን ሰናይ ዉድ መሪዋን ተሰናበተች።

ሊዊስኢንቺዮ ሉላ ደ ሲልቫ።እንደ ተፈቀሩ፣ እንደተወደዱ፣ እንደ ዲሞክራሲዉ ወግ ሥልጣናቸዉን ለተተኪያቸዉ አስረከቡ።ብራዚሎች ምናልባት በታሪካቸዉ የመጀመሪያዉን ተወዳጅ-መሪያቸዉን በድምፃቸዉ በመጀመሪያዋ ሴት መሪ ተኩ።ዲልማ ሮሴፍ።የጎርጎሮሳዉያኑ አዲስ አመት አንድ ሲል ቅዳሜ ከአለም የስምንተኛዉ ሐብታም ሐገር አዲስ መሪ አዲሱን ሥልጣናቸዉን በይፋተረከቡ።

ርክክቡ ግን አዲሲቱ ፕሬዝዳት እንዳሉት ሥልጣን የመያዝ ደስታን-ከሉላ ከመለየት ሐዘን የቀየጠ ነበር።«ለሐገሩና ለሕዝቡ ልዩ ፍቅር ነበረዉ።የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን አሁን ሥረከብ የሚሰማኝ ደስታ-እሱን በመሰናበቴ ከሚሰማኝ ሐዘን ጋር የተቀየጠ ነዉ።»

የአዲሱ ዘመን አዲስ ጅምር ለብራዚሎች፣ ለሉላ፣ ለሮሴፍም በርግጥ አስደሳች ነበር።የወይዘሮ ሮሴፍ እቅድ ደግሞ ሉላ የጀመሩትን ድሕነት፥ ሥራ አጥ-ወንጀለኝነትን በመቀነስ መርሕ መቀጠል። «ትምሕርትን ለማስፋፋት፥ የጤና አገልግሎትን ለማዳራስ፥ ፀጥታን ለማስከበር አስፈላጊዉን ጥረት ሁሉ አደርጋለሁ።ከሁሉም በላይ ደግሞ ድሕነትና መከራን ለማስወገድ አበክሬ እታገላለሁ።»

ብራዚል በመፈንቅለ-መንግሥት፥ በአመፅ፥ በማጅራት መቺ-በአዳዛዥ እፅ ነጋዴዎች፥ ሥትታበጥ ምዕራብ አፊሪቃዊቷ ኮትዲቯር ከአካባቢዎቿ ሐገራት ሁሉ አንፃራዊ ሥላም-ብልፅግናን ታታጥም ነበር።ሉላ ደ ሲልቫ ደሐ-ቤተሰባቸዉን ለመርዳት ከአራተኛ ክፍል ትምሕርት ሲያቋርጡ ያሁኑ የኮትዲቯር መሪ በምርጥ ትምሕርት ቤቶች-ይማሩ ነበር።

ያንድ ዘመን፥ የሩቅ ለሩቅ ሐገራት፥ የማይስተካከል ወላጆች ግኝቶች ናቸዉ።ሉላና ባግቦ።በስድስት ወር የሚያንሰዉ ሉላ በአስራ-ዘጠኝ አመቱ የሚላስ-የሚቀመስ ለማግኘት ከአደገኛ ማሺን ጋር ሲታገል አንድ ጣቱ ሲቆረጥ ወጣቱ ባግቦ ከፕሮፌሰርነት ያደረሰዉን ጥናት በምርጥ ዩኒቨርስቲዎች ይከታተል ነበር።

Flash-Galerie Happy New Year 2011
የአዲሱ አመት መልካም ምኞትምስል Fotolia/NLshop

ባግቦ በሁለት አመት ቀድመዉ የሐገራቸዉን የፕሬዝዳትነት ሥልጣን ያዙ። ሉላ ተከተሉ።የድሮዉ የታሪክ ፕሮፌሰር አስር አመት የተንደላቀቁበትን ሥልጣን ላለመልቀቅ እንቢኝ ሲሉ የድሮዉ መሐይም ሐገር ሕዝባቸዉን አበልፀገዉ፥ አስተምረዉ፥ እንደ ተወደዱ ከስልጣን ተሰናበቱ።

የባግቦ መዘዝ-የአፍሪቃዊቷን ሐገር ሕዝብ ለዳግም ዉጊያ፥ ለባሰ ዉድቀት-ድቀት እንዳሰጋ አዲሱ አመት የሰወስት ቀን ጉዞዉን አጠናቀቀ።የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ ኢኮዋስ ባለሥልጣናት እንደዛቱት ባግቦን በሐይል ከሥልጣን ለማስወገድ ከወሰኑ ከፍተኛ ጦር የምታዘምተዉ ናጄሪያ ጆስ ላይ ሙስሊምና ክርሲቲያን እንደተላለቀባት አዲሱን አመት ለመቀበል አንድ ሁለት ትል ያዘች።

ግን የሰማንያ ሰዎች ሕይወት የጠፋበት ብዙዎች የቆሰሉበት ግጭት-በቅጡ ሳይረግብ በአዲሱ አመት ዋዜማ ርዕሠ-ከተማ አቡጃ ተሸበረች።ከአንድ የጦር ሰፈር አጠገብ የፈነዳዉ ቦምብ በትንሹ ሰላሳ ሰዉ ገደለ።የፕሬዝዳት ጉድላክ ጆናታን ቃል አቀባይ ኦሉሴን ፔቲንሪን እንዳሉት ቦምቡን ያፈነዱት የአዲሱን አመት በአል ደስታ ለማወክ የሚሹ ሐይላት ናቸዉ።

«ሕዝቡ ባጠቃላይ አዲሱን አመት በደስታ ለመቀበል ዘና ብሎ ነበር።ይሕ በግልፅ የሚያመለክተዉ ኑሮን ለማወክ በየስፍራዉ ሰይጣናዊ ምግባር የሚፈፅሙ ሰዎች መኖራቸዉን ነዉ።»

የአደጋ ጣዮቹ ማንነት ሳይታወቅ-አቡጃ-ጆስ አዲስ አመት አሉ።የሩቅ የቅርብ ታዛቢዉ ግን ናጄሪያ የራስዋን «ሰይጣን» ሳታስር የአቢዣኑን ለማባረር መቻሏን እንደጠየቀ፥ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት የቤኔዲክት አስራ-ስድስተኛን ቡራከ ሰማ።

«የእምነት ነፃነት የአንድ መንግሥት መሠረታዊ ሕጋጋት አካል ነዉ።ይሕንን ሕግ አለማክበር ማለት የመጨረሻ መጨረሻ መሠረታዊ ሕግንና መሠረታዊ ነፃነትን መጣስ ማለት ነዉ።»

የቤኔዲክት አስራ-ስድስተኛ መልዕክት በአዲሱ አመት ዋዜማ ኢራቅ ዉስጥ ሁለት ክርስቲያኖች መገደላቸዉን እና የጆሱን ግጭት መሠረት ያደረገና በመቃወምም ነበር።የርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳቱ መልዕክት ከቫቲካን ሲንቆረቆር-የግብፅዋ ጥንታዊት ከተማ አሌክሳንደሪያን ያሸበረዉ ቦምብ ሃያ-አንድ የጥንት ክርስቲያን የኮፕቲክ አማኞችዋን ሕይወት ቀጨ።ፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባረክ ሽብር ሐይማኖት አያዉቅም አይነት አሉ።

«አደጋዉ መላዉ ሐገሪቱን ነዉ-ያሸበረዉ።ኮብቶችንም ሙስሊሞችን እኩል (ያሸብራል)።ይሕ አለም የዘመን መለወጫ በአልን በሚያከብርበት በዚሕ ወቅት የተፈፀመ ወንጀል ነዉ።»

የግብፁ አደጋ ርዕሠ-ሊቃነ-ጳጳሳት ቤኔዲክት አስራ-ስድስተኛ ሥለ አለም ሠላም የሚመክር የተለያዩ ሐይማኖት መሪዎች ጉባኤ የመጥራታቸዉን ዜና እንደ ጆቦነዉ፥ የኢራኑ ፕሬዝዳት ማሕሙድ አሕመዲ ኒጃድ ለክርስቲያን ሐይማኖት አባቶች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸዉ ተሰማ።

ምዕራባዉያን ሐገራትና እስራኤል የኑክሌር ቦምብ ለማሰራት ያሴራሉ፥ አሸባሪ የሚባሉትን ሐማስና ሒዝቡላሕን ይረዳሉ በማለት የሚያወግዟቸዉ የኢራን ሙስሊማይዊት ሪፐብሊክ ፕሬዝዳት መልዕክት ይዘት እንዴትነት በርግጥ አልተተነተነም።ማስተንተን ቢያስፈልግም ተንታኞች እስካሁን ጊዜ አላገኙም ወይም አልፈለጉም።

Papst / Benedikt / Vatikan / Audienz
ምስል AP

ብቻ መልዕክቱ ቫቲካን፥ ለንደን፥ ዋሽንግተን ወይም ሌላ ስፍራ መድረስ አለመድረሱ ሳይረጋገጥ «አብዮታዊ ዘብ» የተሰኘዉ የኢራን ጦር ሁለት ሰዉ አልባ የምዕራብ ሐገራት ሰላይ አዉሮፕላኖችን መትቶ መጣሉን አስታወቀ።ዘገባዉ እዉነትም ሆነ ሐሰት አመት ያለዉ ዓለም፥ ፋርስ ላይ የሚያተከትከዉ የኢራንና የምዕራቦች አሮጌ ዉዝግብ እንደቀጠለ መሆኑን መሠከረ።

ከፋርስ ወደ ምሥራቅ እልፍ ላለ ደግሞ የሰሜን ኮሮያን መሪ የኪም ጆንግ ኢልን መልዕክት አድምጧል።ደቡብ ኮሪያና ምዕራባዉያን ሐገራት ኑክሌር ታጥቀዋል፥ የኮሪያ ልሳነ-ምድርን ሠላም አብጠዋል እያሉ የሚያወግዙ-የሚወነጅሏቸዉ ኪም ጆንግ ኢል በአዲሱ አመት አጠቃላይ ሠላም ለማዉረድ ለሚደረግ ድርድር ዝግጁ ነኝ አሉ።የሰማቸዉ እንጂ የተቀበለ ያደመጣቸዉም የለም።

የፋርስ ባሕረ-ሠላጤ ወይም የኮሪያ ልሳነ ምድር የአዲስ አመት ጉዞ የሰላም-ድርድር ይሁን የጦርነት ዉዝግብ በዋናነት የምትወስነዉ ሐገር የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት የባራክ ኦባማ የአዲስ አመት መልዕክት በሐገር ዉስጥ መርሕ ላይ ያተኮረ የተቃዋሚዎቻቸዉን ትብብር የጠየቀ ነበር።ሁለት ሺ አስራ-አንድ አፍጋኒስታን የሠፈረ ጦራቸዉን ማስወጣት የሚጀምሩበት መሆኑን በርግጥ የዘነጋዉ የለም።

አሜሪካ መራሹ ጦር የሚወጣበት ጊዜ በወራት መሰላት ሲጀመር ሁለት ባልደረቦቹ ተገደሉ።ቅዳሜ። ቅዳሜዉኑ የአሜሪካ ጦር ሰሜናዊ ፓኪስታን ዉስጥ የመሸጉ የታሊባን ደፈጣ ተዋጊዎች ያላቸዉን አስራ-ዘጠኝ ሰዎች ከሰዉ አልባ አዉሮፕላን በተኮሰዉ ሚሳዬል ገደለ።

በማግስቱ እሁድ የሽብር-ፀረ ሽብር ዉጊያ፥ የዉሐ ሙላት አደጋ ግራ ቀኝ የሚያላጋት ፓኪስታን ተጣማሪ መንግሥቷ ፈረሰ።ራሱን ከጠቅላይ ሚንስትር የሱፍ ራዛ ጂላኒ ካቢኔ ያገለለዉ የሙታሒድ ቁዋሚ ንቅናቄ (MQM) መሪ እንደሚሉት ፓርቲያቸዉ የኑሮ ዉድነት እና ሙስናን መግታት ካልቸለ መንግሥት ጋር መስራት አይፈልግም።

«ተጣማሪዉን ለመተዉ ወስነናል።ምክንያቱም መንግሥት የተዛባና ምግባረ ብልሹ አስተዳደርን እንዲለዉጥ፥ ሙስና እና የሕዝብ ችግር እንዲያቃልል (ያቀረብነዉን ሐሳብ) አልተቀበለዉም።»

የኑክሌር የታጠቀችዉ ፓኪስታን እንደተዝረከረከች፥ አፍቃኒስታን እንደተሸበረች አለም አቀፉ ሕብረ ብሔር ጦር ዘንድሮ ሐምሌ ከአፍቃኒስታን መዉጣት ይጀምራል-ነዉ የአዲሱ አመት እቅድ ምግባር ተቃርኖ አብነት።

Flash-Galerie Brasilien Rousseff Lula Präsidentenwahl
የአዲሲቱና ነባሩ የብራዚል ፕሬዝዳንቶችምስል AP

በሁለት ሺሕ አስር ከሔይቲ እስከ ፓኪስታን በደረሰዉ የተፈጥሮ አደጋ ወደ ሰወስት መቶ ሺሕ ሕዝብ አልቋል።አዉስትራሊያ አዲሱን አመት የተቀበለችዉ ገሚስ ግዛቷ በዉሐ- እንደተቀበረ ነዉ።ዉሐ የሞላዉ የአዉስትራሊያ ግዛት ስፋት ጀርመንና ፈረንሳይ አንድ ላይ ቢደመሩ ይበልጣቸዋል።ይልቅዬ ለጀርመን በጣሙን ለመራሔ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል መንግሥት የጥሩ ምልኪ ጅምር የታየበት ነዉ።ሜርክል በአዲሱ አመት መልዕክታቸዉ እንዳሉትም ሥራ አጥነት በጅጉ ቀንሷል፥ የምጣኔ ሐብት ድቀቱ ተወግዷል፥ ዩሮን ለማጠናከር የሚደረገዉ ጥረት ደግሞ ይቀጥላል።

«በነዚሕ ወራት የአዉሮጳ ትልቅ የመገበያያ ሸርፍ ፈተና ገጥሞታል።ዩሮን ማጠናከር አለብን።ይሕ ማለት ገንዘባችን ብቻ ማለት አይደለም።ዩሮ የመገበያያ ሸርፍ ብቻ አይደለም።እኛ በአዉሮጳዊነታችን የተባበርንበትም ጭምር እንጂ።የተባበረችዉ አዉሮጳ የሰላማችን እና የነፃነታችን ዋስትና ናት።ዩሮ ደግሞ የብልፅግናችን መሠረት ነዉ።»

የብልፅግናዉን መሠረት ኤስቶያ በቀደም ተቀላቀለችዉ።አስራ-ሰባተኛዋ የዩሮ ሸርፍ ተጠቃሚ ሐገር ሆነች።በቅርቡ የፕሬስ ነፃነትን የሚገድብ ሕግ በማዉጣቷ ተቃዉሞና ወቀሳ ያየለባት ሐንጋሪ ደግሞ የአዉሮጶች የሰላምና የነፃነት ተምሳሌት የሆነዉን የአዉሮጳ ሕብረትን የስድስት ወር የፕሬዝዳትነት ሥልጣን ተረከበች።

Symbolbild UN Sicherheitsrat Indien und Deutschland
የፀጥታዉ ም/ቤትምስል AP/Montage: DW

የበርሊኖች ትኩረት ግን ኒዮርክ ላይ ነበር።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላይ ጉባኤ ባለፈዉ ጥቅም በወሰነዉ መሠረት ጀርመን፥ ሕንድና ደቡብ አፍሪቃ ሁለት አመት የሚዘልቀዉን የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት መቀመጫቸዉን ተረከቡ።

ጀርመን ተዘዋዋሪዉን መቀመጫ ያገኘችዉ ካናዳን ከመሰለች ሐገር ጋር ተወዳድራ ነበር።በአለም አቀፉ ድርጅት የጀርመን አምባሳደር ፔተር ቪቲግ ነገ ከዚያ ወንበር ይቀመጣሉ።

«የጀርመን ሚና እዚሕ የታወቀ ነዉ።ከትላልቆቹ የአዉሮጳ ሐገራት አንዷ ናት።ከፍተኛ ምግባር የምታከናዉን ሐገር ናት።እዚሕ የምንታየዉ እንደዚያ ነዉ።ይሕ ደግሞ እርግጥ ነዉ።ጀርመን አልፎ-አልፎ ቋሚ ያልሆነዉ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አባል በሆነችበት ጊዜ ሐላፊነቷን በተገቢዉ መንገድ መወጧትዋ የታወቀ ነዉ።»
አዲስ አመት-ያሮጌ አዲስ እዉነት ቅይጥ አለም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ