1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

2012ዓ,ም ሞቃት ዓመት

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 23 2005

ትናንት የተሰናበተዉ የጎርጎሮሳዊ 2012ዓ,ም የሰሜን ንፍቀ ክበብ ክረምት ወቅት ባለፉት ዓመታት ከታዩት ሞቃት የተባሉ ክረምቶች ከአንድ እስከ አስረኛ ባሉት ረድፍ አንዱ መሆኑ ተገለጸ። በአንፃሩ ብርዱና በረዶዉ በዚሁ ዓመት የሰዉ ህይወት እስከመቅጠፍ የደረሰባቸዉ አካባቢዎችም አሉ።

https://p.dw.com/p/17C2J
ምስል dapd
Wetter in Europa Weihnachten 2012 Deutschland
ምስል picture-alliance/dpa

የፈረንጆቹ የገና በዓል ለወትሮዉ በአብዛኛዉ የሰሜን ንፍቀ ክበብ አካባቢ ሀገሮች ክረምቱ ሲሆን ዙሪያ ገባዉን በሚያለብሰዉ ብትን በረዶ ታጅቦ ደም በሚያረጋ ዓይነት ቅዝቃዜ የሚከበር ነዉ። በተለይ እዚህ ጀርመን በታህሳሱ የጠቆረ ሰማይ እና የጨለመ ዙሪያ ገባ በዓሉን ቤት ዉስጥ ክትት ብሎ ከቤተሰብ ጋ ለበዓል ቤት ካፈራዉ ድግስ እየተቋደሱ መዋሉ ልዩ እና ተናፋቂ ያደርገዋል። እዚህ የጀርመን መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡትና እንደታየዉ ግን በተለይ የዘንድሮዉን የገና በዓል ቢያንስ ሙኒክ ከተማ ባለዉ መረጃ መሰረት ካለፉት አንድ መቶ ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በሞቃት የአየር ሁኔታ ነዉ የተከበረዉ። የፀሓይዋ ፍንትዉ ብሎ መዉጣት ራሱ ወቅቱ በትክክል ይህ ታህሳስ ወር ነዉን? እንዲሉ ግድ ይላል። በደቡብ ፈረንሳይዋ ቢያሪዝ ሙቀቱ 22 ዲግሪ በመድረሱም ሰዎች ከቤታቸዉ ዉጭ መዋል ብቻ ሳይሆን በባህር ላይ ቀዘፋ እንዲዝናንቱ ጋብዟል። ኗሪዎቹ እንዲህ ነበር ያሉት፤

«ይህ ፍፁም የተለየ ነዉ፤ ለዚህ ወቅት ይህ እጅግ ግሩም የአየር ጠባይ ነዉ፤ በመሠረቱ በዚህ ወቅት ሁሌም ቀዝቃዛ ነዉ።»

ጀርመንም ቢሆን ደመቅ ያለች ፀሐይ የመፀዉ ዓይነት የአየር ሁኔታ በማስከተሏ በተለይ በብርዱ ወቅት እጅግ በሚቀዘቅዘዉና ሲሞቅም ከፍተኛ የሙቀት መጠን በሚያስተናግደዉ በሙኒክና አካባቢዉ ኗሪዎች ወደመናፈሻ ቦታዎች፤ የቢራ መጠጫ አፀዶችና በረንዳ ላይ ተቀምጦ ሻይ ቡና ወደሚባልባቸዉ ስፍራዎች ጎራ ማለታቸዉ ታይቷል። ለመዝናናት ከወጡት የከተማዉ ኗሪዎች አንዱ በዚህ ወቅት ከቅዝቃዜዉ ለመሸሽ ቤታቸዉ ዉስጥ ተከተዉ በዓሉን ለማድመቅ የገና ዛፍ በማስጌጥ ያሳልፉ የነበረዉን ጊዜ በማስታወስ ዘንድሮ ያን ከማድረግ ወደዉጭ ወጣ ብለዉ በክረምት የተገኘችዉን ፀሐይ እየሞቁ መዝናናትን እንደመረጡ ገልፀዋል፤

«ለዚህ እኮነዉ በዚህ ዓመት የገና ዛፍ የማይኖረኝ። ምክንያቱም ሙቀቱ 14 ዲግሪ ደርሶ የሚሠራዉ የገና ዛፍ አያስደስትም፤ አለበለዚያ እኮ እቤት ተከተን  ዛፉን ማስጌጥ ሊኖርብን ነዉ። ሆኖም እንደሚታየዉ ያንን ትተን እዚህ መናፈሻ ዉስጥ ተቀምጠን ሙቀቱን እያጣጣምን ነዉ።»

Russland Winter
ምስል Reuters

ሙቀት አለ ቢባልም ግን በእርግጥ ብርድ የለም ማለት አይደለም። በአብዛኞቹ ምዕራባዊ የአዉሮጳ ግዛቶች ግን የሙቀት መጠን መለኪያዉ ከዜሮ በላይ ያሳያል። መንገዶች እንደመስታወት በሚያብረቀርቀዉ አንሸራታች በረዶ አልተሸፈኑም። ከበረዶ ይልቅ ዝናብ ደጋግሞ ይዘንባል። የተመድ የአየር ንብረት ትንበያ ዘርፍ ባለፈዉ ሳምንት የገና በዓል ወቅትን ብቻ ሳይሆን በጥቅሉ የጎርጎሮሳዊዉ 2012ዓ,ም እጅግ ሞቃት የሚባል ክረምትን እንዳስተናገደ ነዉ ያመለከተዉ። ሁኔታዉም ዓለማችን ወደሞቃትነት በፍጥነት እየተለወጠች መሆኗን እንደሚያሳይ ጠቁሟል። ባለፈዉ ሳምንት ረቡዕ ጄኔቫ ላይ ባቀረቡት ዘገባም ፖሊሲ አዉጭዎችና የአየር ንብረት ለዉጥን ለመግታት የሚደራደሩ ወገኖች ከዶሃዉ የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለዉጥ ተመልካች ጉባኤ ማግስት ይህን እዉነታ ልብ ሊሉ እንደሚገባም አሳስበዋል። ምንም እንኳን የዓመቱ የክረምት ሁኔታ እንዲህ ነዉ ብሎ የሚሰጠዉ ብያኔ የሚገለፀዉ በመጋቢት መጨረሻ ቢሆንም ከወዲሁ ይዞታዉ ሲታይ ቀደም ሲል እንደተባለዉ ከሌላዉ ጊዜ ይልቅ ሞቃት ከሚባሉት መካከል እንደሚመደብ አያጠያይቅም ነዉ ያሉት።

Wetter in Europa Weihnachten 2012 Deutschland
ምስል picture-alliance/dpa

የገና በዓል እያየነዉ ያለበረዶ አልፏል ያሉት ጃሩድ የአየር ሁኔታዉ በዚሁ መልኩ እንደሚቀጥል አያጠራጥርም ብለዋል። በጀርመን ሃምቡርግ የማክስፕላንት የአየር ንብረት ትንበያ ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ሞይብ ላቲፍ ጀርመን ዉስጥ በገና ሰሞን የታየዉን የሙቀት መጨመር ሁኔታ ተንተርሶ በርግጥ የአየር ንብረት ለዉጥ ገሀድ ሆኗል ብሎ ለማለት ጊዜ የሚያስፈልገዉ ጉዳይ ነዉ ይላሉ፤

«ሁኔታዉን በትክክል ለመገንዘብ ከተፈለገ የግድ የረዥም ጊዜዉን ሂደት መከታተል ያስፈልጋል። እኔ ብዙ ጊዜ ይህንን ማነፃፀር የምፈልገዉ በይዘቱ አንድ ሆኖ የተለያየ መልክና ቅርፅ ሊያሳይ እንደሚችል ጉዳይ ነዉ። ብዙ ጊዜ የዛ ነገር የጎላ ገፅታ የሚወጣበት አጋጣሚ ቢኖርም ከጎላዉ ገጽታ ጋ ሌሎችም የሚታዩበት አጋጣሚ መኖሩን ነዉ። ይህ ማለት ምንድነዉ ላለፉት አስርት ዓመታት የቅዝቃዜዉ መጠን አንፃራዊ መካከለኛ የሆነ የክረምት ወቅት በተከታታይ አይተናል። እስካሁንም የሚታየዉ ከዚሁ ጋ ተመሳሳይ ነዉ። እናም በዚህም መሠረት እኔ መናገር የምችለዉ የዓለም የሙቀት መጠን በእርግጥም እየጨመረ መሄዱን የሚያመላክቱ ክስተቶች መኖራቸዉን ጠቋሚ መሆኑን።»

USA Busunglück in Oregon
ምስል Reuters

በጀርመንና ሌሎች አካባቢዎች ስለክረምቱ መሞቅ ቢነገርም በተቃራኒዉ በምስራቅ አዉሮጳ ቅዝቃዜዉም ሆነ በረዶዉ ተጠናክሮ የሰዉ ህይወት እስከማጥፋት መድረሱ ይሰማል። ሩሲያ ዉስጥ ለምሳሌየሙቀቱ መጠን ከዜሮ በታች 30 ዲግሪ ደርሷል። ቅዳሜ ዕለት የወጡ ዘገባዎች እንዳለመከቱት ታዲያ ጠንካራዉ የክረምት ቅዝቃዜ በታህሳስ ወር ብቻ ወደአንድ መቶ አርባ ሁለት ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። ወደአንድ ሺህ ሶስት መቶ ሃምሳ ያህሉ ደግሞ ቅዝቃዜዉ ባስከተለባቸዉ የጤና እክል ምክንያት በህክምና እየተረዱይገኛሉ። ፖላንድም እንዲሁ ቅዝቃዜዉ ለስልሳ አንድ ሰዎች ህልፈተ ህይወት ምክንያት ሆኗል። ከእነዚህ መካከል አርባ አንዱ ህይወታቸዉን ያጡት ከብርዱ ለመዳን ከተጠቀሙባቸዉ ቤት የማሞቂያ ስልቶች የወጣ ካርቦን ሞኖክሳይድ ተመርዘዉ መሆኑን አሶሲየትድ ፕረስ ዘግቧል። እንደባለስልጣናቱ ገለፃም ከሆነ በብዛት ህይወታቸዉ ለአደጋ የተጋለጠዉ ድሆችና የጎዳና ላይ ኗሪዎች ናቸዉ።

በተለያዩ የአሜሪካንግዛቶችምእንዲሁበኃይለኛ ንፋስ የሚገፋበረዶከቅዝቃዜዉ በተጨማሪ በሰዉም ሆነ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነዉ። ጀርመን በተቃራኒ ሰዎች በዉሃ ዳርቻዎች ሳይቀር ከቤት ዉጭ ተቀምጠዉ የሚዝናኑበት ሁኔታ ይታያል። ይህን ያስተዋሉ ደግሞ በአንድ ወቅት የነበረ የአየር ሁኔታ በሌላ ጊዜ የሚለወጥ ከሆነ በትክክል የአየር ንብረት ለዉጥ ማለት ይህ ነዉ እያሉ ነዉ። የዘርፉ ተመራማሪ ሞይብ ላቲፍ ግን የአየር ፀባይና አጠቃላይ የሆነዉ የአየር ንብረት ለዉጥን ማምታት አይገባም ባይናቸዉ፤

«በመሠረቱ የአየር ጠባይን ከአየር ንብረት ጋ ማሳከር አይገባም። የአየር ጠባይ ሁሌም በተቃራኒዎች የሚንፀባረቅ ነዉ። እዚህ ምዕራብ አዉሮፓ በአሁኑ ወቅት እንዳለዉ በጣም ሞቃት ንፋስ ሲኖር በሌላ ስፍራ ግን ከፍተኛ ቅዝቃዜ አለ ማለት ነዉ። በሩሲያ አሁን ይህ በግልፅ እየታየ ነዉ። አንድ አካባቢ ከፍተኛ የአየር ግፊት ሲኖር ሌላ ጋ ደግሞ ዝቅተኛ ይሆናል። በአሁኑ ሰዓት ሩሲያ ዉስጥ በጣም ጠንካራ የሆነ ከፍተኛ ግፊት አለ። በዚህም መሠረት የሳይቤሪያ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ይታያል።»

Russland Winter
ምስል Reuters

እንደ ባለሙያዉ ገለፃ ከሆነም በምስራቅ አዉሮጳ ያለዉ የአየር ግፊት ቅዝቃዜዉን በየትኛዉም ጊዜ ወደምዕራብ ሊያመጣዉ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል። የብሪታንያ የአየር ሁኔታ ትንበያ ተቋምም እንዲሁ በግል የደረሰበትን ተመሳሳይ መረጃ አዉጥቷል። ይህኛዉ ደግሞ ከኋላ ጀምሮ በመጥቀስ ከዚህ ዓመት ቀደም ብሎ በቅርቡ የጎርጎሮሳዊዉ 2010ዓ,ም እጅግ ሞቃት ከተባሉት ዓመታት ተብሎ እንደነበር አስታዉሷል። እንደብሪታንያዉ የአየር ንብረት ትንበያ ከጎርጎሮሳዊዉ 1850ዓ,ም አንስቶ የተመዘገበ መረጃን በማጣቀስም ዛሬ አንድ የተባለዉ 2013ዓ,ም እንዲሁ ከ2012 የበለጠ ሞቃት እንደሚሆን ጠቁሟል።

ይህ ማለት ግን እያንዳንዱ የዓለም ክፍል ሞቃታማ ይሆናል ማለት ሳይሆን የየአካባቢዉ የአየር ጠባይ ተለዋዋጭነትን መሠረት በማደርግ የሚቀያየር እንደሚሆንም ተገልጿል። አብዛኞቹ የዘርፉ ተመራማሪዎች የሙቀት መጠን በዓለማችን እንዲጨምር የሚያደርጉ ዓበይት ያሏቸዉ ምክንያቶች ሰዉ ሰራሽ መሆናቸዉን ነዉ አስረግጠዉ የሚገልፁት። ዋነኛዉ ደግሞ የበካይ ጋዞች ልቀት መጠን መባባስ ነዉ። ባለፉት በርካታ ዓመታት ወደከባቢ አየር የሚገባዉ የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን ከፍተኛ መሆኑ ቢገለፅም በተለይ መዘዙ ተብራርቶ ስለቅነሳዉ ብዙ በሚነገርበት በዚህ ወቅት ብሶ መገኘቱም እያነጋገረ ነዉ። ለአብነትም በጎርጎሮሳዊዉ 2011ዓ,ም በቻይና መሪነት የተመዘገበዉ የበካይ ጋዝ ልቀት መጠን እጅግ ከፍ ማለቱም ተጠቅሷል። ይህ ሊያስከትል ይችላል የሚባለዉ የአየር ንብረት መለዋወጥም በተለይ ባለፈዉ ዓመት ጎልቶ መታየቱን ለመጠቆም ሳንዲ የተሰኘ ስያሜ የተሰጠዉ ወጀብና ማዕበል በአሜሪካን ትልቅ ግዛት ኒዉርክና አካባቢዉ ያደረሰዉን ጉዳት፤ እንዲሁም እዚያዉ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ የተከሰዉን ድርቅ ማስታወስ በቂ እንደሆነ ባለሙያዎቹ አንስተዋል።  

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ