1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

50ኛው የበርሊን ዓለም አቀፍ የቴክኒዎሎጂ ትርዒት፣

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 3 2002

የሥልጣኔ አንዱ ዋና ዓላማ፤ ሰዎች በኑሮአቸው ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች መፍትኄ መሻት፣ ከባዱን ነገር ማቅለል ነው። ለዚህ ትልቁን አስተዋጽዖ አድራጊ ደግሞ፣ ሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ነው።

https://p.dw.com/p/P7Fi
ምስል DW-TV

ሰው ብልጠት እንዲያሳዩ አድሮጎ የሠራቸው የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎች፣ በጥንቃቄና በቁጠባ ተግባራቸውን ማካናወን ይችላሉ፣ ለምሳሌ ያህል የልብስ ማጠቢያ መሣሪያዎች ፣ የልብሱን የመቆሸሽ ደረጃ አስልተው የሚያስፈልገውን የፈሳሽ ሳሙናና ውሃ መጠን ለክተው፣ ኤልክትሪክ የሚረክስበትንም ሰዓት መርጠው ነው ሥራቸውን የሚጀምሩት። በዓመት 60 ጋን ገደማ የሚሆን ውሃም እንዳይባክን ይቆጥባሉ።

ማለፊያ ስም ያላቸው፤ ዚመንስ፤ ቦሽና ሚሌ የመሳሰሉት በዚህ ረገድ እመርታ ማሳየት ብቻ ሳይሆን ለተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ፤ ለውሃና ኤልክትሪክ ቁጠባ አስተዋጽዖ አድርገዋል ነው የተባለው።

የመስኮት መጋረጃዎችና የቤት ማሞቂያ መሳሪያዎች ፤ ከእጅ ስልክ መሣሪያ (ሞባይል)በጣት ጠቅ ተደርጎ ይከፈታሉ ወይም ይዘጋሉ። የኤሌክትሪክ ምድጃ እንደጋለ ድንገት ቢረሳ ፣ ራሱ ተቆጣጥሮ ማጥፋት ይችላል።

ይህ ሁሉ ፤ ባለፈው ሳምንት ዓርብ በይፋ ተከፍቶ ዛሬ በሚደመደመው የበርሊኑ ዓለም አቀፍ የመገናኛና የመዝናኛ የቤት ዕቃዎች ትርዒት ሲታይ ነው የሰነበተው። አዲስ ነገር አጥብቀው ማየት የሚሹ በሂደቱ ይረካሉ። ቅጥ አጣ የሚሉ ደግሞ ደንታ የላቸውም። ዘመናዊ በሚሰኘው አዳዲስ የሥነ ቴክኒክ ውጤት መገልገል የሚፈልጉ ሁሉ፣ ምኞታቸውን በቀላሉ ማሳካት አይችሉም ዋጋ ይገታቸዋልና። ለምሳሌ ያህል አሁን ብዙ የሚነገርለት፣ በልዩ መነጽር እርዳታ የሚታየው ዘመናዊ የተሰኘው 3 ማዕዘናዊው ቴሌቭዥን ዋጋው 2,000 ዩውሮ ገደማ የሚያወጣ ሲሆን፤ ጠፍጣፋውን መደበኛው ዘመናዊ ቴሌቭዥን በአማካዩ 680 ዩውሮ ነው፣ ዋጋው!። በዛ ያሉ የውጭ አገርና የሀገር ውስጥ የመገናኛና መዝናኛ መሣሪያ ሠሪ የኢንዱስትሪ ኩባንያዎች ለትርዒት ያቀረቡ ሲሆን ፤ ከጀርመን ታዋቂ ኩባንያዎች መካከል፤ «ሎቨ» =አንበሳ የተሰኘው ቴሌቭዥን ሠሪ ብቻ ሆኖአል በዚህ ረገድ ያልተሣተፈው። ሎቨ፣ ልዩ መነጽር ከማቅረብ ያለመነጽር እርዳታ የሚታይ 3 ማዕዘናዊ ቴሌቭዥን ለመሥራት ከ «ፍራውንሆፈር» የምርምር ተቋም ጋር እየመከረ ሳይሆን እንዳልቀረም ተወስቷል። ተቋሙ፤ በርሊን ውስጥ ያለ ልዩ መነጽር እርዳታ ፣ የ3 ማዕዘናዊ ቴሌቭዥን ተንቀሳቃሽ ምስል ሊታይ እንደሚችል ሳያሳይ አልቀረም። በዘንድሮው የበርሊኑ ዓለም አቀፍ የመገናኛና የመዝናኛ የቤት ዕቃዎች ትርዒት፣ ከ 3 ማዕዘናዊው ቴሌቭዥን ሌላ፤ አማላይ ሆኖ የታየው፤ የቴሌቭዥንና ኢንተርኔት ቅንጅት ሲሆን ይህም ከርቀት የቴሌቭዥን ፕሮግራም መቀያየሪያ በሆነው ንዑስ መሣሪያ አማካይነት ፣በቴሌቭዥኑ መስኮት ውስጥ፣ ሰዎች እንደምርጫቸው የኢንተርኔት ዝግጅቶችን፣ ድረ ገጾችን አለበዚያም የቴሌቭዥን ዝግጅቶችን መከታተል ይችላሉ ማለት ነው። ይህ በእንግሊዝኛው Hybrid Broadcast Broadband TV ወይም በአህጽሮት Hbb TV የሚሰኘው መሆኑ ነው። በአንድ ዕለት ስለተሠራጨ ዝግጅት፣ ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት የሚቻልበት ዕድልም አለ። ከጀርመኑ የዚመንስ ኩባንያ ውጤቶች ሌላ ለምሳሌ የጃፓኑ ቶሺባና የደቡብ ኮሮያው ሳምሱንግም በዚህ ዘርፍ ሰፊ እመርታ ማሳየታቸውን ሳያስመሠክሩ አልቀሩም።

ለህዝብ እይታ የቀረቡት አብዛኞቹ የቤት እቃዎች ፣ ለሴቶች ታስበው እንደሁ የተጠየቁት

የበርሊኑ ዓለም አቀፍ ትርዒት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የንስ ሃይቴከር፤ እንዲህ ነበረ ያብራሩት።

«እርግጥ ነው በሰፊው ታስቦበት ለቤተሰብ ነው የቀረቡት። አዲሱ የቴሌቭዥን መሣሪያም ሆነ የማዕድ ቤት መሣሪያዎች፤ የቡና ማፍያ ጀበናም ቢሆን ወደዚህ ወደ በርሊኑ ዓለም አቀፍ ትርዒት ለሚመጡ ሁሉ አማላይ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ታዲያ፣ ውድ የቤት ዕቃዎችን የሚገዙ ወንዶች ናቸው።»

50ኛው ዓለም አቀፍ የበርሊን የመገናኛና የመዝናኛ መሣሪያዎች እንዲሁም ልዩ- ልዩ የቤት ዕቃዎች ትርዒት፣ ከተከፈተበት ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ዛሬ እስከሚደመደምበት ዕለት ድረስ ፤ የጎብኝዎቹ ቁጥር ከ 230,000 ላያንስ እንደሚችል ነው የተገለጠው። የኤሌክትሮ ቴክኒክ እና ኤሌክትሮኒክ ኢንዱስትሪ ማዕከላዊ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚዳንት ሃንስ ዮዓኺም ካምፕ እንዳሉት ፤ የኢንዱስትሪውና የንግዱ ዘርፍ የጠበቀው በከፊል ከታሰበው በላይ ተሳካቷል ብለዋል። በጀርመን ሀገር የተጠቀሰው ዘርፍ በዓመት ከ 25 ቢሊዮን ዩውሮ በላይ ትርፍ እንደሚያገኝ ያቀረበው ግምት ሐቅ ሳይሆን እንደማይቀርም ነው የተመለከተው።

በበርሊኑ ትርዒት ፤ በመገኘት ፣ ዕውቁ የኢንተርኔት መረጃ አቅራቢ ድርጅት «ጉግል» የበላይ ኀላፊ ኤሪክ ሽሚት እናዳስረዱት ከሆነ፤ ድርጅታቸው፤ ከቴሌቭዥን ሠሪዎች ጋር በመተባበር ድረ-ገጻቸው ከጥቂት ወራት በኋላ በዩናይትድ እስቴትስ የቴሌቭዥን አገልግሎትም እንዲኖረው ያደርጋል። በአውሮፓም አገልግሎቱ፤ በመጪው 2011 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት እንደሚዳረስ ሽሚት አስታወቀዋል። ጉግል የተለያዩ ቋንቋዎችን በድምፅ መተርጎም የሚቻልበትን አዲስ ሥነ-ቴክኒክም በበርሊኑ ትርዒት ላይ አሳይቷል።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ