1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

500ዓመት የሆነዉ የጀርመን የቢራ አጠማመቅ ዘዴ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 27 2008

ጀርመን በዓለም ሃገራት ዘንድ ከምትታወቅበት የሕክምና መድኃኒትና ቁሳቁስ እንዲሁም ተሽከርካሪ ባሻገር በምትጠምቀዉ ቢራም ዝናዋ መግነኑ ይታወቃል። እንደዉም አንዳንዶች የጀርመን ቢራ ርጎነዉ ነዉ ብለዉ ሲያሞካሹም ይሰማል። ጀርመኖች ራሳቸዉ ደግሞ ቢራን ፈሳሹ ዳቡ እያሉ ነዉ የሚጠሩት።

https://p.dw.com/p/1Iike
Deutschland Merkel 500 Jahre Reinheitsgebot
ምስል Reuters/M. Rehle

500ዓመት የሆነዉ የጀርመን የቢራ አጠማመቅ ዘዴ

ይኸዉ ርጎ ብሎም ፈሳሹ ዳቡ ተብሎ የሚሞካሸዉ የጀርመኑ ቢራ የአጠማመቅ ስርዓት ወጥቶለት ለመጠጥነት መቅረብ ከጀመረ፤ ዘንድሮ 500 መቶኛ ዓመቱን ይዞአል። እንደ ሕጉ ደግሞ በየትኛዉም ቦታ የሚጠመቅ የጀርመን ቢራ ሆፕፍን የተባለ እንደ ጌሾ ያለ ቅጠል፤ ብቅል እርሾና ዉኃን ብቻ ነዉ ያካተተዉ። በጎርጎረሳዉያኑ የቀን ቀመር 1516 ዓ,ም በደቡባዊ ጀርመን በባየር ግዛት ዉስጥ የአጠማመቁ ዘዴ በሕግ ቀርቦ መጠመቅ የጀመረበት 500ኛ ዓመት የዛሬ ወር ግድም በተለያዩ ዝግጅቶች ከቢራዉ ጋር ተከብሮአል። በእለቱ ዝግጅታችን የጀርመኑን ቢራ ታሪክዊና ባህላዊ ሂረቱን እየዳሰስን በኢትዮጵያ የጀርመን የቢራ መጥመቅያ ቤቶችን እንቃኛለን።

Deutschland G7 Gipfel Barack Obama Frühschoppen in Krün
ምስል Reuters/M. Rehle

ጀርመን ባየር ግዛት የዛሬ 500 ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ የጀርመን ቢራ የአጠማመቅ ዘዴ በሕግ ፀደቀ። ከዝያን ጊዜ ጀምሮ የጀርመኑ ቢራ ከጌሾ፤ ገብስ፤ እርሾና ዉኃ በቀር ምንም ነገር አይገባበትም። የጀርመን ቢራ ይህንኑ የአጠማመቅ ዘዴዉን ይዞ በጀርመን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የጀርመን የቢራ አጠማመቅ ጥራት ማስጠበቅያ ሆኖ እዉቅናንም ማግኘቱ ይታወቃል። የጀርመን የቢራ አጠማመቅ ሕግ ለመጀመርያ ጊዜ ጊዜ የዛሬ 500 ዓመት ማለት በ 1516 ዓ,ም ሚያዝያ 23 በባየር ኢንጎልፍ ከተማ በባየሩ ልዑል ዊሊያም 4ኛና ሉድቪግ 10ኛ መጽደቁን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

እንድያም ሆኖ በአጠቃላይ የጀርመን ቢራ ጠመቃ ረጅም እድሜ እንዳለዉ ዘገባዎች ያመለክታሉ። በ 736 ምዕተ ዓመት በባየር ጋይዝን ፊልድ አካባቢ ከገብስ የተሰራ መጠጥ መጠመቅ እንደጀመረ ታሪክ ያሳያል።በጥንት ጊዜ በጀርመን የሚገኙ ገዳሞች በብዛት ቢራን ይጠምቁ ስለነበር፤ በአሁኑ ጊዜ ገበያ ላይ በስፍት ለሚታየዉ ቢራ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸዉም ተዘግቦአል። በዝያን ጊዜ ቢራ ጠመቃ ከወንዶች ይልቅ የሴቶች ስራም እንደነበር ነዉ የተመለከተዉ።

Deutschland Merkel 500 Jahre Reinheitsgebot
ምስል Privat

በጥንት ዘመን ቢራ ለጀርመናዉያን እንደምግብ ሁሉ ሠዎች በቀን የሚወስዱት ዋና ነገርም ነበር ። በዝያን ጊዜ እጅግም ንጹሕ የመጠጥ ዉኃ አለመኖሩና የመጠጥ ዉኃ ለብዙ በሽታዎች መንስዔ ስለነበር፤ ቢራ ጥሩ የዉኃ ጥምን ማርክያና ጥሩ መተክያም ሆኖ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ተጠቅሶአል። በርግጥ በጥንት ጊዜ ይጠመቅ የነበረዉ ቢራ የአልኮል መጠኑ ዛሬ ገበያ ላይ እንዳለዉ የቢራ ዓይነት ከፍተኛ ባለመሆኑና እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ ልጆችም ሆኑ ሴቶች ሙሉ ቀን እንደ ዉኃ ይጠቱት እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ።

የዛሬ 500 ዓመት በባየር ግዛት የቢራ አጠማመቅ ሕግ የወጣዉ የነዋሪዎቻቸዉን ጤንነት ለመጠበቅ እንደሆነ ዘገባዎች ያሳያሉ። ሕጉ ከመዉጣቱ በፊት ግን ቢራ ዉስጥ ፖም መሳይ አይነት ፍራፍሪ፤ ስራስር፤ ቀለም የሚሰጥ ሞን የተባለ ተክል፤ ሰጋቱራ መሰል ነገር ሁሉ ይገባበት እንደነበር ነዉ የተመለከተዉ። በሌላ በኩል የአጠማመቅ ሕጉ ከወጣ በኋላ በኤኮኖሚ አኳያ ያስገኘዉ ትልቅ ሚናም አለ። ይኸዉም ቢራ ለመጥመቅ ሕጉ ገብስ ብቻ ጥቅም ላይ እንዲዉል በማድረጉና የቢራ ግብር መጠን ጥቅም ላይ በሚዉለዉ ገብስ መለካቱ ነዉ። ሌላዉ ይህን ተከትሎ፤ የምግብ እጥረትና የረኃብ አደጋን ለመከላከል እንደ ስንዴ አጃ የመሳሰሉ ዋንኛ የምግብ ጥራጥሪዎች ቢራን ለመጥመቅ ጥቅም ላይ እንዳይዉሉ መደረጉ ነዉ። ይህ ሕግ ከወጣ በኃላ የጀርመን ቢራና የአጠማመቅ ዘዴዉ እስከዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለምንም ተፎካካሪና የገበያ ፉክቻ ተወዳጅነቱን ጠብቆ ይገኛል።

Äthiopien Biergarten in Addis Abeba
የአዲስ አበባዉ «ቢር ጋርትን ኢን»ምስል Privat

ለጀርመናዉያን የቢራ መድረክ ልክ እንደኛ የቡና ባህል እንደማለት ነዉ፤ ለማኅበረሰቡ የሚያከብረዉ ባህሉ ነዉ፤ የሚገናኝበት መድረኩ ነዉ ሲሉ በፍራንክፈርት ነዋሪ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ከበደ ነግረዉናል።

«በጀርመን ሃገር የቢራ አጠጣጥ ሥነ-ስርዓት ፤ እንደ ትልቅ ባህል ተወስዶ በየዓመቱ ማኅበረሰቡን የሚያገናኝ የሥነ-ስርዓት መድረክ ሆንዋል። የቢራ አጠጣጥ ባህል በጀርመን አገር የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለዉ ነዉ። ልክ እንደኛ በቡና አጠጣ ባህል ፤ ሠዎች በቡና መጠጫ መድረክ ላይ ተገናኝተዉ ቡና ፤ ቶና በረካ እየጠጡ ችግራቸዉን እንደሚወያዩ በቤተሰብም የተለያዩ ነገሮችን እንደሚወያዩበት መድረክ ፤ የጀርመኑ የቢራ አጠጣጥ ሥነ-ስርዓትም፤ ነገሮችን የሚወያዩበት፤ የሚዝናኑበት፤ የሚገናኙበት መድረክ ነዉ። እንደሚታወቀዉ በዓለማችን ብዙ ቢራ የሚጠጣበት አገር ጀርመን ነዉ። በተለይ በባየር ሙኒክ በየዓመቱ ህዝብ ተገናኝቶ የቢራ መጠጫ ሥነ-ስርዓትን በደማቅ ያከብራል። ስለዚህም ሕዝብን በማገናኘቱ ረገድ ከፍተኛ ማኅበራዊ ጠቀሚታ አለዉ»

የዛሬ ወር ግድም የጀርመኑ ቢራ በሕጉ መሠረት መጠመቅ የጀመረበትን 500ኛ ዓመቱን ሲያከብር የጀርመን ቢራ ጠማቂዎችና አፍቃሪዎች በድምቀት ነዉ ያከበሩት። ግዙፉ የጀርመኑ ፖስታ ቤት የጀርመኑ የቢራ ጠመቃ ጅማሮ 500ኛ ዓመትን አስመልክቶ ፤ ልዩ የፖስታቤት ቴንብር አዉጥቶ ነበር።

Äthiopien Biergarten in Addis Abeba
የአዲስ አበባዉ «ቢር ጋርትን ኢን» ቢራ መጥመቅያምስል Privat

« በዉጭ ሃገራት የሚገኙ የጀርመን ቢራ ጠማቂዎች በጀርመን ቢራ ስም ሲጠምቁ የተለየ ምንም ዓይነት ነገርን እንደማይጨምሩ የጀርመን ቢራ ጠማቂዎች ማኅበር ሃንስ ጊዮርግ አይሊስ አረጋግጠዋል።

መዲና አዲስ አበባ ላይ «ቢር ጋርተን» በሚል መጠርያዉ የሚታወቀዉ ታዋቂዉ የጀርመን ቢራ መጥመቅያ ቤት አስተዳዳሪ ወ/ሮ አዲሲቱ ተጅቤ ድርጅታቸዉ የሚጠምቀዉ ቢራ የጀርመን የቢራ አጠማመቅ ሥርዓትን ሙሉ በሙሉ እንደሆነ አረጋግጠዋል።

« እኛ የምንጠምቀዉ ቢራ በጀርመን የቢራ አጠማመቅ ስርዓትና ሕግ መሠረት ነዉ።

በአዲስ አበባ ከተማ በጀርመን የቢራ አጠማመቅ ዘዴን ይዘዉ የጀርመንን ቢራ እየጠመቀ የሚያቀርበዉ ሌላዉ እንቢልታ የተሰኘዉ ሆቴል ነዉ። አስተዳዳሪዉ አቶ ዳንኤል ነጋ ናቸዉ። ቢራ ለመጥመቅ በአጠቃላይ የሚያስፈልጉንን ነገሮች የምናመጣዉም ከጀርመን አገር ነዉ። ለምሳሌ ብቅል የምናመጣዉ ከታዋቂዉ የጀርመን ብቅል አምራች ድርጅት ቫየር ማን ነዉ የምናመጣዉ። ሌላዉ በጀርመን ሃገር ጥራት ደረጃ ሕግ መሠረት ብቅል ፤ ሆፕስ «ማለት ጌሾ» እሱንም ቢሆን እኛ ከዉጭ ነዉ የምናመጣዉ፤ ሌላዉ ዉኃ ነዉ ዉኃን ከዚህ እንጠቀማለን ሌላዉ እርሾ ነዉ፤ እርሶዉንም የምንወስደዉ ከዚሁ ከኢትዮጵያ ነዉ። »

Äthiopien Biergarten in Addis Abeba
የአዲስ አበባዉ «ቢር ጋርትን ኢን» ቢራምስል Reuters/H. Hanschke

አንድ ቢራ ተጠምቆ ለመጠጣት ማለት ለብርጭቆ እስኪበቃ ስንት ጊዜ ነዉ የሚፈጀዉ? « ቢራ ተጠምቆ እስኪጠጣ ድረስ ወደ አራት ሳምንት ያህል ይፈጃል»

ቢር ጋርድን የተሰኘዉና አዲስ አበባ ላይ የሚገኘዉ የጀርመን የቢራ መጥመቅያችሁ ምን ያህል ይወደዳል፤ የጀርመንን ቢራ ብሎ የሚመጣዉ ተጠቃሚስ ብዙ ነዉ?

« የኛ ቢራ በጣም ተወዳጅ ነዉ፤ ጀርመንና ኢትዮጵያዉያኖችን ጨምሮ የተለያዩ ዜጎች እኛ ጋር ይመጣሉ። ቤታችን ከሰኞች እስከእሁድ ሙሉ ነዉ፤ በጣም ይወዱታል።»

በርግጥ የጀርመናዉያን ቢራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ ነዉ። እንዴት ነዉ የጀርመንን ቢራ ለመጥመቅ ያሰባችሁት? መጥመቅያዉን ሁሉ ከጀርመን እንዳስገባችሁ ይታወቃል።

Äthiopien Biergarten in Addis Abeba
የአዲስ አበባዉ «ቢር ጋርትን ኢን»ምስል Privat

« የዛሬ አርባ ዓመት ነዉ አባቴ የጀርመንን ቢራ መጥመቅያ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባትና ለመጥመቅ ሃሳብን ያመጣዉ። ድርጅቱ በእግሩ እስኪቆም ብዙ ጊዜ ፈጀ። በተለያዩ አይነት ችግሮች ማለት የገንዘብ ችግር፤ አመቺ ቦታ ያለማግኘት ችግር ፤ የአጋር እጦት ችግር የመሳሰሉትን አስወግዶ ከሠላሳ ዓመት በኋላ የዛሬ አስር ዓመት ተቋቋመ። የመጥመቅያ ሆቴሉን የምንጠራዉ «ቢር ጋርድን ኢን» ብለን ነዉ። መጠርያዉ የቤት ዉስጥ አይነት እደምታን እንዳለዉ ለማመላክት በሚል ነዉ የተሰጠዉ።

እንደሚታወቀዉ ጀርመናዉያን በቁጥር ለመግለፅ እስከሚያዳግት ድረስ የተለያዩ ጣዕም ያላቸዉንና የተለያዩ የአልኮል መጠን ያላቸዉን ቢራ ዓይነቶችን ይጠምቃሉ። የአዲስ አበባዉ ቢር ጋርትን ኢን ስንት ዓይነት ቢራን ይጠምቃል?

« እኛ የምንጠምቀዉ ሁለት የቢራ ዓይነቶችን ነዉ፤ «ብሉንዲ» ና «ኢቦኒ » ይባላሉ። ይህ ቢራ ከጀርመኑ የቢራ ጋር ስናነጻፅረዉ የፒልስነር አይነት ቢራ አይነት ነዉ። የአልኮል መጠኑም እንደ ሌላዉ ቢራ ዓይነት የተለመደዉ ዓይነት ነዉ።»

ጀርመናዉያን አዲስ አበባ ላይ የጀርመን መጥመቅያ ቤት መኖሩን ሰምተዉ ሲመጡ በደስታና እጅግ በመደነቅ ነዉ። መጥመቅያ ቤቱን እንጎብኝ ብለዉ ይጠይቃሉ ፤ ጥራቱና ንጽሕናዉን አይተዉ እጅግ አድንቀዉ ነዉ የሚሄዱት። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ የጀርመን መጥመቅያ ቤትን በማግኘታቸዉ ተደስተዉ ነዉ የሚሄዱት። እዚህ ላይ ጀርመናዉያn ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዉያን ሌሎችም ዜጎች ጭምር የጀርመንን ቢራ መጥመቅያ አይተዉ ቢራዉን በመጎንጨታቸዉ ደስ እንዳላቸዉ ይገልፃሉ። የቢር ጋርትን ኢን አስተዳዳሪ ድርጅታቸዉ የጀርመንን ቢራ ብቻ ሳይሆን ፤ ከጀርመኑ ቢራ ጋር የሚቀርበዉን የጀርመን ባህላዊ ምግብንም እንደሚያቀርብ ገልፀዋል።

Deutschland Dillon, Early, Vergin, Borrud und Lomas trinken Bier
ምስል DW/C. Lomas

አዲስ አባበባ ላይ የሚገኙት ሁለቱ የጀርመን ቢራ መጥመቅያ ቤቶች ማለት «ቢር ጋርትን ኢን» ና «እንቢልታ ሆቴል » ከመቶ ዓመታት በላይ በወዳጅነት የዘለቁትን ሁለቱን ሃገሮች ግንኙነት ይበልጥ እያጠናከሩናየጀርመናዉያኑን ባህል ቀረብ አድርገዉ እያሳዩ ይመስለናል። ቃለ ምልልስ የሰጡን እያመሰገንን ሙሉዉን ቅንብር የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ