1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

77 ከመቶው፦ የፉላኒ ወጣቶች አበሳ

ዓርብ፣ መስከረም 18 2011

መነሻቸው ከኢትዮጵያ እንደሆነ የሚነገርላቸው በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ በብዛት የሚገኙት የፉላኒ ህዝቦች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዙሃን መገናኛዎች ስማቸው ተደጋግሞ ሲነሳ ይደመጣል። በአብዛኛው አርብቶ አደሮች የሆኑት ፉላኒዎች በርካታ ተግዳሮቶችን ተጋፍጠው የሚኖሩ ናቸው። ከጎሳው የሚወለዱ ወጣቶች ደግሞ ተደራቢ ችግር መጥቶባቸዋል።

https://p.dw.com/p/35dBN
DW Fulani
ምስል DW/K. Gänsler

የፉላኒ ወጣቶች አበሳ

ነዋሪነቱ በማዕከላዊ ናይጄሪያ ባለው የፕላቶ ግዛት የሆነው የ29 ዓመቱ ኢድሪስ አብዱላሂ ባይሮ ላሞቻቸውን እየነዱ የሚጨዋወቱ ሁለት አዳጊ ዕረኞችን አሻግሮ ይመለከታል። ዕድሜያቸው ከ16 ያልዘለለው እኒህ አዳጊዎች የዘወትር ሥራቸው ከ20 የሚበልጡ ላሞችን በቂ ሳር እና ውኃ እንዲያገኙ ማድረግ ነው። ኢድሪስ ከዓመታት በፊት እንደ እነርሱ የከብት ጭራ ተከትሎ ሜዳ ሸንተረሩን ሲያቋርጥ ነበር የሚውለው። 

እንደ አዳጊዎቹ ሁሉ የፉላኒ ጎሳ አባል የሆነው ኢድሪስ አብዱላሂ ከቤተሰቦቹ ጋር በጫካ ነበር የሚኖረው። ላሞች፣ ጥጃዎች እና ፍየሎችን ተከትሎ ከቦታ ቦታ ሲባዝን የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው ኢድሪስ ባደገበት ግዛት ባለው የጆስ ዩኒቨርስቲ በታሪክ እና ዓለም አቀፍ ጥናት መመረቅ የቻለ ነው። ከትውልድ ስፍራው ርቆ ቢኖርም እንዲህ እንዳሁኑ ያደገበትን ማኅበረሰብ ማግኘት እና ገጠሩን መጎብኘት ያስደስተዋል።

DW Fulani
ምስል DW/K. Gänsler

«ለእኔ እንደ ሁለትዮሽ ልምድ እመለከተዋለሁ፤ የገጠሩን፣ የጫካውን ሕይወት እና የከተሜውን ሕይወት። እኔ የለውጥ ሰው ነኝ። በለውጥ፣ በዘመናዊነት አምናለሁ። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች፤ በገጠር የሰፈሩቱ የእኔ ሕዝቦች እንዲዘምኑ እና እንዲማሩ እሻለሁ» ይላል ኢድሪስ።

በእርግጥም ዘመናዊ ትምህርት የማግኘት ዕድል ከማኅበረሰቡ ዋነኛ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ነው። በተለምዶ ፉላኒዎች አንድ ቦታ የማይቀመጡ፣ በምዕራብ እና ማዕከላዊ አፍሪካ ባሉ ቦታዎች የሚዘዋወሩ ናቸው። አሁን አሁን አብዛኞቹ የፉላኒ ማኅበረሰቦች በቋሚነት መስፈርን እያዘወተሩ ቢመጡም ያሉባቸው ቦታዎች ግን ብዙውን ጊዜ ከትምህርት ቤቶች እና የጤና ማዕከላትን ከመሳሰሉ አገልግሎት መስጫዎች የራቁ ናቸው።

ኢድሪስ ራሱን እንደ ዕድለኛ ይቆጥራል። ልጅ እያለ የማኅበረሰቡ አባላት ትምህርት ቤት እንዲገባ ድጋፍ አድርገውለታል። የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ለመቀጠል ደግሞ ላሞቹን ገበያ ማውጣት ነበረበት። ላሞች ለፉላኒዎች የኩራት እና የደስታ ምንጫቸው ብቻ አይደሉም፤ እንደ ባንክም ያገለግላሉ። 

«የሸጥኳቸው ላሞች ብዙ ናቸው። ሁሌም የትምህርት ቤት ክፍያ ሲደርስብኝ ወደ መንደራችን እሄዳለሁ። ወደጫካ እወርድናም አንዷን ላም እይዝና ወደ ገበያ እወስድና እሸጣለሁ። በቡኩሩ እና ጆስ የከብቶች ገበያ አለን። እንዲህ እንዲሆን ባልፈልግም እንደዚያ እያደረግኩ ነበር የትምህርት ቤት ወጪዬን ስከፍል የነበረው። ከሆነ ቦታ ገቢ ባገኝ እና ከብቶቼን ብተዋቸው ምኞቴ ነበር» ይላል ኢድሪስ።

የ20 ዓመቷ ማሪያም መሐመድ ግን እንደ ኢድሪስ በትምህርቷ ለመዝለቅ አልታደለችም። የሁለት ልጆች እናት ከመሆኗ በፊት ትምህርቷን መከታተል የቻለችው ለአጭር ጊዜ ነው። ማሪያም አሁን ከጆስ ከተማ አንድ ሰዓት በመኪና ተጉዞ ከሚደረስበት አነስተኛ የሰፈራ ቦታ ትኖራለች። «የእኔ ችግር ምንድነው? የተወለድኩት እዚህ ነው ነገር ግን እኩል መብት አልተሰጠንም። በዚህ መሬት ላይ እኛን ማየት አይፈልጉም። እና መንግሥትም ምንም እያደረገ አይደለም። መንግሥት ይህን ችግር ተመልክቶ ልክ እዚህ እንደተወለደ እንደማንኛውም ሰው በእኩልነት ሊመለከተን ይገባን ነበር። ነገር ግን የምንስተናገደው በእኩልነት አይደለም» ስትል ያለባቸውን ችግር ትናገራለች ማሪየም።   

DW Fulani
ምስል DW/K. Gänsler

ወጣቷን የሚያናድዷት ነገሮች ብዙ ናቸው። ለረጅም ጊዜ መነጋገሪያ የሆነው የመሰረት ልማት እጦት ያበሳጫታል። ለፉላኒዎች የተሰጠው አሉታዊ ምስልም ያስቆጣታል። አርሶ አደሮች በፉላኒዎች የኑሮ ዘይቤ እና ለላሞቻቸው ባላቸው ፍቅር ምክንያት ያፌዙባቸዋል። ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ግን በአርብቶ አደሮቹ ፉላኒዎች ላይ የሚሰነዘረው ዘለፋ ጠንከር ማለት ይዟል። «የፉላኒ አሸባሪዎች» የሚሉ ቃላት በብዙዎቹ የናይጄሪያ ጋዜጦች ላይ መነበብ ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። በቴሌቪዥን ጣቢያዎች በሚተላለፉ ውይይቶች ወይም ቶክሾው ላይም ተመሳሳዩን አገላለጽ ማድመጥ እየተለመደ መጥቷል። 

ከጎርጎሮሳዊው 2018 መባቻ ጀምሮ እየተባባሰ በመጣው ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል። እነዚህ ግጭቶች ከዓመታት በፊት የተቀሰቀሱ ቢሆንም የአሁኑን ለየት የሚያደርገው ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ይበልጥ መታጠቃቸው ነው። አብዛኞቹ የአካባቢው መገናኛ ብዙሃን የጥቃቶቹ ፈጻሚ አድርገው የሚገልጹት ፉላኒዎችን ነው። ይህ የሚወልደው ቁጣ ደግሞ ወደተጨማሪ ግድያ የሚገፋ ሆኗል። ከፉላኒ ጎሳ የሚወለደው ኢድሪስ አስቀድሞም የነበረው እኩልነት አልባነት ይበልጥ እየከፋ ይሄዳል ብሎ ይሰጋል። 

«ይሄ መጥፎ ስም የመስጠት ነገር በሁለቱ ተፈላሚ ወገኖች ወይም ቡድኖች መካከል የጠነነ ጠላትነት እንዲኖር ያደርጋል። ምክንያቱም ፉላኒዎች ሌሎች ጎሳዎችን እንደጠላቶቻቸው መመልከት ይጀምራሉ። ከቀን ወደ ቀን ይበልጡኑ አክራሪ እየሆኑ ይመጣሉ» ሲል ኢድሪስ ስጋቱን ይገልጻል። 

ለግጭቱ በሙሉ ፉላኒዎች ተጠያቂ በመደረጋቸው ተስፋ የቆረጡ የጎሳው ወጣቶች የሽፍታዎች እና የአሸባሪ ቡድኖች ወጥመድ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ ይላል ኢድሪስ። «አስተውል! ላሞቼ ሊዘረፉ ይችላሉ። ምናልባትም እኔም ልገደል እችላለሁ። ወንድሜ ተገድሎ ምንም አልተደረገም። እንደዚህ ሲሆን መንግሥትን እንደ ጠላታቸው መመልከት ይጀምራሉ። ይህንን አሸባሪዎች ለራሳቸው መጠቀሚያ ያደርጉታል፤ ያሳምኗቸዋል። ከዚያም ይጠቀሙባቸዋል» ይላል። 

ብዙዎች በፕላቶ ግዛት ያሉ ነዋሪዎች በተለይም ክርስቲያኖችን ሲያነጋግሩ የሚዘነጉት ነገር ይህንን ነው። ብዙ የክርስትና እምነት ተከታዮች ፉላኒዎቹ እስልምናን ወደ ደቡብ አቅጣጫ እያስፋፉ እና በክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ላይ የጂሃድ ጦርነት ጀምረዋል ሲሉ ይከሳሉ። በእርግጥ ጥቂትም ቢሆኑ በዚህ የማይስማሙ ክርስቲያኖች አሉ። ብሌስ አጉዋም በጉዳዩ ላይ ጥብቅ አቋም ካላቸው ጥቂቶች መካከል አንዱ ናቸው። የካቶሊክ ቄስ የሆኑት ብሌስ በጆስ  ከተማ ያለው የውይይት፣ ዕርቅ እና ሰላም ማዕከል ኃላፊ ናቸው። ቄሱ በቅርቡ በአባቢያቸው እየሆነ ያለው ነገር ክፉኛ ያሳስቧቸዋል። 

DW Fulani
ምስል DW/K. Gänsler

«በዚህ መጥፎ ስም የመስጠት አባዜ ምክንያት የፉላኒ ወጣቶች የማይገቡባቸው ቦታዎች አሉ። ምክንያቱ ደግሞ ወጣቶቹ የፉላኒ አሸባሪዎች ተብለው መጠራታቸው ነው። ነገር ግን ሁሉም አሸባሪ አይደሉም። ብዙ ጥሩ እና ሰላም አፍቃሪ፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና ከጎረቤቶቻቸው ጋር ተዋህደው የሚኖሩ ፉላኒዎች አሉ» ይላሉ የሃይማኖት አባቱ። 

ቄስ ብሌስ ከተለያዩ እምነቶች እና ብሔሮች ለሚመጡ ወጣቶች ውይይቶች እና አውደ ጥናቶች ያዘጋጃሉ። ሰላም የተሞላበት ህይወት በጋራ መኖር ይቻላል የሚል የጠነከረ አቋም አላቸው። ነገር ግን ለወጣት ፉላኒዎች ምክር ቢጤ ጣል ያደርጋሉ። «ለፉላኒ ወጣት ትውልድ አንድ ያለው መንገድ የሚመስለኝ ከብዙሃን መገናኛ ጋር ግንኙነት መፍጠር ነው። የራሳቸውን ታሪክ መናገር አለባቸው። የራስህን ታሪክ ራስህ ካልተረከኸው ማንም ሊናገርልህ አይችልም። ስለዚህ ራሳቸውን ለማዳን እና ያለውን ታሪክ ለመቀየር የብዙሃን መገናኛዎችን መጠቀም ይኖርባቸዋል» ሲሉ ይመክራሉ።  

የኢዲሪስም ዓላማ ከቄሱ ምክር ጋር የተመሳሰለ ነው። ከዩኒቨርስቲ ከተመረቀ በኋላ ሥራ ፍለጋ ላይ ያለው ኢድሪስ በጆስ ከተማ እና አካባቢው እየተዘዋወረ የጎሳዎቹን አባላት ለማሳመን እየጣረ ይገኛል። ብዙ ሰዎች ስለ ፉላኒ የሕይወት ዘይቤ ምንነት በግልጽ እንዲናገሩ ለማግባባት ይሞክራል። በወጣት ፉላኒዎች ላይ መጥፎ ስም መለጠፍ ማንንም አይጠቅምም ብሎ የሚያምነው ኢድሪስ ትምህርትን ተጠቅሞ ችግሩን ለመቅረፍ ያልማል። ትምህርት የሚያመጣውን ለውጥ ደግሞ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ በራሱ ሕይወት ላይ አይቶታል። 

«ቅድሚያ የምሰጠው በሕዝቦቼ ደጃፍ እንዴት ትምህርት ማድረስ እችላለሁ ለሚለው ነው። ምክንያቱም ብዙዎቹ ኋላ ቀር እና የተረሱ ሕዝቦች ናቸው። ከሁሉም በላቀ የተገለሉ ሕዝቦች ናቸው። መንግሥት ጉዳዬም አይላቸው። መንግሥት ለእነርሱ ግድ ስለሌለው እነርሱም አይናገሩም። እነርሱን ወክለው የሚናገሩ ሰዎችም የላቸውም። አሁን እኔ የእነርሱ ወኪል ነኝ። እነርሱን ወክዬ ድምጻቸውን አሰማላችኋለሁ» ሲል ኢድሪስ   

ካትሪን ጋንስለር / ተስፋለም ወልደየስ 

ሸዋዬ ለገሠ