1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

BRICS እና አከራካሪው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሥልጣን፣

ዓርብ፣ ግንቦት 19 2003

በኢንዱስትሪ ወደበለጸጉት አገሮች ደረጃ በመጠጋት ላይ ያሉት በአንግሊዝኛው ምህጻር BRICS የሚሰኙት 5 አገሮች፤ ብራዚል ፣ ሩሲያ፤ ህንድ፤ ቻይናና ደቡብ አፍሪቃ፤ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አመራር ሁሌ፣

https://p.dw.com/p/RQD4

በአውሮፓውያን እጅ መሆኑ አግባብ አይደለም በማለት የራሳቸውን እጩ የማቅረብ አዝማሚያ የያዙ ይመስላሉ። አውሮፓውያን፤ ለምን ይህን ቦታ ለራሳቸው ብቻ እንደያዙ መቀጠል ፈለጉ? ታዛቢ ምን ይላል? በብራሰልስ፤ የአፍሪቃ ካራይብና ሰላማዊው ውቅያኖስ አዋሳኝ አገሮች(ACP) ጽ/ቤት የካቢኔ ሥራ አስኪያጅ የሆኑትን የኤኮኖሚ ባለሙያ ዶ/ር ኦባዲያ ሜይላፊያን ፣

ተክሌ የኋላ አነጋግሮ የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሯል።

በ 21ኛው ክ/ዘመን፣ እንዲህ ዓይነቱን ዐቢይ ዓለም አቀፍ ተቋም፣ለመምራት፤ የአንድ አካባቢ ወይም ክፍለ ዓለም ተወላጅ ብቻ ነው የሚያስፈልገው የሚለው አቋም እስከመቼ የሚያስኬድ ይሆናል? ዶ/ር ኦባዲያ ሜይላፊያ--

«አውሮፓውያኑ፤ ለመገንዘብ የሚያዳግት አይደለም፤ ይህ የሥልጣን ቦታ ምንጊዜም በአውሮፓዊ እንዲያዝ ነው የሚፈልጉት። እ ጎ አ በ 1944 በብሪተን ውድስ በተደረገው ስምምነት መሠረት፤ አሜሪካውያን፤ ምንጊዜም የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንትነቱን ሥልጣን፣ እንዲይዙ፤ አውሮፓውያኑ ደግሞ ሁልጊዜየዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅትሥልጣን በአጃቸው አድርገው ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል። ግን፤ እ ጎ አ፣ በ 1944 የነበረችው ዓለምና የ 2011 ዷ ዓለም አንድ አይደሉም። »

ያኔ፤ 2ኛው የዓለም ጦርነት ሊያከትም አንድ ዓመት ብቻ ነበረ የቀረው። የዓለም ፖለቲካ ከዚያ ዐቢይ ጦርነት ሌላ የተለየ መልክም እንደነበረው የሚዘነጋ አይደለም።

«በ 1944 ከኢትዮጵያና ላይቤሪያ በስተቀር አንድም ነጻ አፍሪቃዊ ሀገር አልነበረም። አፍሪቃውያን በአመዛኙ በቅኝ ግዛት ሥር ነበርን። ህንድ ነጻ አገር አልነበረችም። ቻይናም፤ በውስጣዊ አብዮት ተቅጥራ ነበር። አሜሪካ፣ 50 ከመቶውን የዓለም ያልተጣራ ገቢ ታመርት ነበር። አውሮፓም በሰፊ የመልሶ ግንባታ ሂደት ላይ ነበረች። ይሁንና፣ የአውሮፓ አገሮች፣ ቅኝ ገዥዎችም ነበሩ። እንደሚመስለኝ፤ በአሁኑ ጊዜ፣ ይህ የሁለቱ ወገኖች ሥልጣን በአጅ አድርጎ የመቀበሉ ጉዳይ አጠያያቂ ነው። በኤኮኖሚ ደርጅተው፣ ብቅ ያሉ የአፍሪቃ የአስያና የላቲን አሜሪካ አገሮች አሉ። ቻይና ብቻ፤ ከ 2 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ተቀማጭ የውጭ ምንዛሪ አላት። ህንድና ብራዚልምአሉ። ስለዚህ ገሐዳዊ እይታና አሠራርም ሊኖረን ይገባል።»

ዋናው ተፈላጊ ጉዳይ ችሎታ መሆኑ ቢታወቅም፤ የሌላ ክፍለ-ዓለም ተወላጅ ቢሾሙበት አይከፋም ። ማን ይመስሎታል ከ BRICS አገሮች ወይም ከማንኛውም አዳጊ አገር ያን ቦታ ለመያዝ ብቁ የሚባለው?

«በዚህ መድረክ፤ እነ--እገሌ ብዬ ስም ለመዘርዘር ተገቢ ሆኖ አይታየኝም። የብዙ ሰዎች ስም በመገናኛ ብዙኀን ተደርድረዋል። ክሪስቲን ላጋርድ እጩ ሆነው ቀርበዋል። የፈረንሳይ የኤኮኖሚና የገንዘብ ሚንስትር ናቸው። ፈረንሳውያንም ያላንዳች ጥርጥር ሌላ ፈረንሳዊ ቦታውን እንዲይዝላቸው በጉጉት ነው የሚጠብቁት።»

ፈረንሳውያኑ፤ ዶሚኒክ እሽትራውስ ካን ቦታውን ከለቀቁ ወዲህ በሌላ የራሳቸው ዜጋ ይያዝ ዘንድ አጥብቀው መሻታቸው እሙን ነው። እጩ ደግሞ አልታጣም የኤኮኖሚና የገንዘብ ሚንስትር ወ/ሮ ክሪስቲን ላጋርድ--

«የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ለመሆን፤ እጩ ተወዳዳሪ ሆኜ ቀርቤአለሁ ጉዳዩን በሰፊው አብላልቼውአለሁ። እናም ለሥራ የምንቀሳቀሰው፣ ፕሬዚዳንቱና ጠ/ሚንስትሩ፤ ሁለቱም በሰጡኝ የተሟላ ድጋፍ ነው።»

ሌሎችም አሉ። እንዳነበብነው ቱርካዊው ከማል ደርቪሽ የተከበሩ የኤኮኖሚ ምሁር ናቸው ግን፤ ቦታውን አልፈልግም ብለዋል። የሲንጋፑሩ ራጉራትናም ስማቸው ተጠቅሷል።

የደቡብ አፍሪቃው ትሬቨር ማኑኤልም አሉበት።

አዎ ፤ የደቡብ አፍሪቃው ትሬቨር ማኑኤል ሌላው ናቸው። እጅግ የተሳካላቸው የፋይናንስ ሚንስትር ናቸው፤ በትግሉ ዘመቻ የተሳተፉ ታሥረው የነበሩና ከዚያም ወጥተው ችሎታቸውን ፣ የኤኮኖሚ ባለሙያነታቸውን፤ በእሥር ቤትም ይሁን በፖለቲካው የትግል ሜዳ ያስመሠከሩ ተደናቂ ሰው ናቸው ፤ እጅግ የተሳካ ተግባር አከናውነዋል። ቅንና ታማኞች ናቸው። ከፍተኛ ብቃት አላቸው። ውጤት የሚያስገኙ መሪም ናቸው። እኒህ በአሁኑ ጊዜ የአቅድ ሚንስትር በመሆን ደቡብ አፍሪቃን የሚያለግሉት እኒሁ ሰው፣ እጅግ ተስማሚ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(IMF) መሪ መሆን ይችላሉ። እዚህ ላይ አደላ እባል ይሆናል!እኔም የአፍሪቃ ሰው ነኝና! አዎ ፤ እርሳቸው ያለጥርጥር እጅግ ምሥጉን የሥራ መሪ መሆን ይችላሉ።»

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ