1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

HIV- ቋንቋ -ባህል

ማክሰኞ፣ ጥር 23 1998

በሞዛምቢክ በርካታ ቋንቋዎች በስፋት ለመግባቢያነት መዋላቸዉ በHIV ላይ ለሚደረገዉ ዘመቻ ብዙም እንዳልረቡ ተጠቆመ።

https://p.dw.com/p/E0j5
የቅኝ-ገዢዋ የፖርቱጋል ፓርላማ
የቅኝ-ገዢዋ የፖርቱጋል ፓርላማምስል dpa - Bildarchiv

ብዙ ተጉዞ ሞዛምቢክ ሲደረስ በርካታ ቋንቋዎች በስፋት ሲነገሩ የመስማት አጋጣሚ ይገኛል። እንዲህ ያለዉን የሞዛምቢክን ገፅታ ለማሳየት በመደበኛ ቋንቋነት ደረጃ በይፋ ፓርቱጋል፤ ሻንጋና፤ ኢሎምዌና ሲሳና የተሰኙትን ለዓይነት ከጠቀሱ ይበቃል። ይህ ፀጋ ባለበት ግን የብዙዎችን እድሜ እያሳጠረ
ስለሚገኘዉ HIV/AIDS ለማስተማርና ለማሳወቅ ቀላል አልሆነም። በዘመናዊዉ ዘዴ መረጃ ለማዳረስ በሚደረገዉ ጥረት ባህልና ወግ ከሚሰጠዉ ትርጓሜ አንፃር ፈተና ደቅነዋል።
ምንም እንኳን የቋንቋ ስብጥሩና ብዛቱ ከባህል ዉበቱ አንፃር ቀልብ ቢስብም ለጤና ባለሙያዎች በአገሪቱ መልዕክትና መረጃ በማዳረሱ ረገድ ኤድስን ለመቆጣጠር እንቅፋት ሆኗቸዋል።
ኢስሜራልዳ ዛቪየር የቋንቋ ባለሙያ ሲሆኑ ኤድስን በተመለከተ የሚተላለፉ መልዕክቶች በተለያየ ቋንቋ የሚሰጡትን ትርጓሜና የፈጥሩትን ግንዛቤ ለማጥናት ሞክረዋል።
በዚህም በትርጉም ስራዉ ሂደት ከአንድ ቋንቋ ወደሌላዉ መልዕክት ሲወራረስ ምን ያህል ለባህላዊ አቀራረቡ ጥንቃቄ የተሞላ መሆን እንደሚኖርበት ቃኝተዋል።
ያዩትንም ሲያስረዱ ለምሳሌ በደቡብ ሞዛምቢክ ኗሪዎች በሚነገረዉ ሻንጋና ቋንቋ ስለወሲባዊ ግንኙነት በቀጥታ መናገር አልተለመደም ይልቁንም በስላች ምንጣፍ ላይ ስለመጋደም ነዉ የሚነገረዉ ይላሉ።
ዛቪየር ማህበራዊ ልማት የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ያዘጋጀዉን የማስተማሪያ ፓስተር እንደተመለከቱት ከህብረተሰቡ አፍራሽ ምላሽ እንደሚያጭር ወዲያዉ ነበር የተረዱት።
ፖስተሩ ከፖርቱጋል ቋንቋ ወደአገራዊዉ ቋንቋ የተተረጎመ ሲሆን ጥቅል ይዘቱም የማዕድን ቆፋሪዎችና የከባድ መኪና ሹፌሮች የስራ ባህሪያቸዉ በHIV ቫይረስ እንደሚያጋልጣቸዉ ያሳያል።
ፖስተሩን የተመለከቱ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በሽታዉን ለማስፋፋት ዋነኛ ምክንያት የሆነዉ ፅንስ ማስወረድ ነዉ የሚል ግንዛቤ ያዙ።
በማዕድን ቁፋሮ ተግባር የተሰማሩት ሰራተኞች በበኩላቸዉ ለቫይረሱ ስርጭት ቀንደኛ ተጠያቂ ተደርገዉ መቅረባቸዉን በመቃወም እኛን እየከሰሱ ሚስቶቻችን እኛ በሌለንበት ተደፋፍረዉ ለበሽታዉ እንዲጋለጡ ያደርጋል በማለት አወገዙት።
ዛቪየር እንደሚሉት ይህን መሰሉን ስራ ከመስራት በፊት የHIV ን ስጭት ለመቆጣጠር እየጣረ የሚገኘዉ ድርጅት የህብረተሰቡን ምክር ለማግኘት መሞከር ነበረበት።
በአንፃሩ ደግሞ በአገሩቱ በተለያዩ የአገር ዉስጥ ቋንቋዎች በሚወጡት በርካታ የህትመት ዉጤቶችና የራዲዮ ፕሮግራሞች አጥኚዋ ተመስጠዋል።
በእሳቸዉ እምነትም ምንም እንኳን የትርጉምና ያቀራረብ ችግር ቢታይም የቋንቋዉን መብዛትና በስፋት የመነገር አጋጣሚ ለዉጤታማ የማስተማሪያ ዘዴ መጠቀም ይቻላል።
ይህንንም ሲያስረዱ በሞዛምቢክ HIV/AIDSን በመቆጣጠር ዙሪያ በርካታ ፖስተሮችና መፅሄቶች በተለያዩ ቋንቋዎች መተርጎማቸዉን ይገልፃሉ።
ብሄራዊ የHIV/AIDS ማጥፊያ ኮሚሽን የግንኙነትና ቅስቀሳ አስተባባሪ ኤልያስ ኮሳ በበኩላቸዉ የአገሪቱ መንግስትና አጋሮቹ የተቸገሩበት ነገር ቢኖር የህብረተሰቡን ፍላጎት የሚያሟላ ስለኤድስ የሚያወራ ነገር ማዘጋጀት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በHIV ዙሪያ የተደረጉ እንቅስቃሴዎችም ያረጋገጡት የሚሰሩት ስራዎች ሁሉ ለየማህበረሰቡ ባህልና ወጎች የቀረቡ መሆን እንደሚኖርባቸዉ ነዉ።
ከዚህ በመነሳትም ባለስጣናቱ በአገራቸዉ የሚዘጋጁት የማስተማሪያ፤ የመረጃና የመገናኛ ዉጤቶች ሁሉ ከማህበረሰቡ የተቀዱና እነሱን ያሳተፉ መሆን አለባቸዉ የሚል መመሪያ አዉጥተዋል።
በሞዛምቢክ ባህላዊ አይነኬ ጉዳዮች አሉ፤ ለምሳሌ ወጣቶች በምንም መልኩ ለአዛዉንት ስለፃታ ግንኙነት ማዉራት አይችሉም።
እንዲሁም በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ሴቶች ከሴቶች ጋር እንጂ ከወንዶች ጋር ማዉራትም አይፈቀድላቸዉም።
ዉጤት ለማምጣት ከታሰበም ስለ በሽታዉ ግንዛቤ በመፍጠሩ ሂደትም ይህ የህብረተሰቡ ፍላጎትና ወግ መከበር ይኖርበታል።
ይህ ሁሉ ተሟልቶም HIVን የሚመለከቱ መልዕክቶች በተስማሚዉ ቋንቋና በተገቢዉ አገላለፅ ቢቀርቡም ሰዎች ሊጠቀሙባቸዉ እስካልቻሉ ድረስ ጥቅም የለዉም።
ይህም ማለት 54 በመቶዉ ህዝብ ማንበብና መፃፍ ባልተማረባት እንደሞዛምቢክ ባለችዉ አገር በፅሁፍ የቀረቡ የማስተማሪያ መልዕክቶች ትርጉም አልባ ናቸዉ።
ከዚህ በመነሳትም በአሁኑ ጊዜ በሞዛምቢክ ስለበሽታዉ ለማስተማር ራዲዮ ከፍተኛዉ የመገናኛ ዘዴ ሆኗል።
በራዲዮ ሞዛምቢክ ሩትና ጓደኞቿ የተሰኘ በHIV ላይ ያተኮረ የራዲዮ ተከታታይ ድራማ በ11 ቋንቋዎች ተተርጉሞ በመተላለፍ ላይ ይገኛል።
የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት UNICEF የሚደግፈዉ ከልጆች ለልጆች የራዲዮ ፕሮግራምም በወጣቶች መካከል የበሽታዉን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚደረገዉ ጥረት አንዱ አካል ነዉ።
ባለሙያዎችም በሚሰራዉ ስራ ዉጤታማ ለመሆን ህብረተሰቡን ማንቃቱ ብቻ ሳይሆን የሚሰጠዉ አገልግሎት ስፋትና የግንዛቤ መፍጠሪያዉ መንገድ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ይላሉ።