1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

UTC 16:00 የዓለም ዜና 200612

ረቡዕ፣ ሰኔ 13 2004

የዓለም ዜና

https://p.dw.com/p/15Iho

ካይሮ ሙባረክ ሞት ያሰጋቸዋል

የቀድሞው የግብፅ ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ ለሞት የሚያሰጋቸው ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተዘገበ ። የግብፅ የፀጥታ ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ከሆስፒታል እስር ቤት ፣ ወደ ወታደራዊ ሆስፒታል ትንናት የተወሰዱት ሙባረክ ራሳቸውን ስተዋል ። መንግሥታዊው የመካከለኛው ምሥራቅ ዜና አግልግሎት ሙባረክ ሳይሞቱ አንዳልቀረ ትናንት ቢዘግብም ፣ የሙባረክ ጠበቃ አል አህራም ለተባለው ጋዜጣ እንደተናገሩት ህይወታቸው አላለፈም ። አሶስየትድ ፕሬስ እንደዘገበው ሙባረክ ትንንት የተገጠመላቸው ሰው ሰራሽ የእስትንፋስ መሣሪያ ዛሪ የተነቀለላቸው ሲሆን ልባቸውና ዋና ዋና የሰውነት ክፍሎቻቸውም ተግባራቸውን አላቆሙም ። ጠበቃቸው እንዳሉት ሙባረክ የሙት በቃ እስራት ከተፈረደባቸው በኋላ በተያዙበት የእስር ቤት ሆስፒታል በህክምና እጦት ምክንያት የጤናቸው ሁኔታ እየተባባሰ ሄዶ ነበር ። የግብፅ መገናኛ ብዙሃን ትናንት ለሊት እንደዘገቡት የ84 ዓመቱ ሙባረክ አንጎላቸው ውስጥ የደም መፍሰስ ሳያጋጥማቸው አልቀረም ። የመተንፈስ ችግር ያለባቸውን የሙባረክን ሁኔታ 15 ሃኪሞች የሚገኙበት አንድ የጤና ባለሞያዎች ቡድን ይከታተላቸው እንደ ነበር የግብፅ የደህንነት ባለሥልጣናት አስታውቀዋል ።

ሎስ ካቦስ የቡድን 20 ጉባኤ ፍፃሜ

ሎስ ካቦስ ሜክሲኮ የተካሄደው የቡድን 20 ሃገራት ጉባኤ የዓለም የፋይናንስ ገበያ ተጠናክሮ እንዲያገግም በጋራ ለመሥራት ቃል ገባ ። ትናንት ጉባኤው ሲጠናቀቅ በወጣው መግለጫ እንደተጠቆመው መሪዎቹ ችግሩን ለመፍታት የተቀናጀ የፊናንስ አሰራርን መከተል የሚያስችሉ እርምጃዎች ሥራ ላይ መዋላቸውን እንደሚደግፉ አስታውቀዋል ። በዩሮ ቀውስና መፍትሄው በላይ ቀረቡ ሃሳቦች ላይ የተነጋገረው ይኽው ጉባኤ የዩሮ ተጠቃሚ ሃገራት ዩሮን ለማረጋጋት አስፈላጊ የሆኑትን እርምጃዎች በሙሉ እንደሚወስዱም በመግለጫው ጠቅሷል ። በጉባኤው ላይ የተገኙት የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በሰጡት አስተያየት አውሮፓ ችግሩን ለመፍታት ከአሁኑ ይበልጥ መተባበር ይገባዋል ብለዋል ።

«በበኩሌ የተጠናከረ አውሮፓ እንደሚያስፈልገን ፣ትብብራችን ይበልጥ ጥብቅ መሆን እንደሚገባው በድጋሚ ግልፅ አድርጌያለሁ ። ምክንያቱም ገበያው የሚፈልገው በአንድ ላይ ወደ ቀድሞው ቦታችን እንድንመለስ ነው ። በተጨማሪም በአውሮፓ ቁጥጥሩና አመኔታው አብሮ የሚሄድና ሚዛኑን ጠብቆ መከናወን የሚገባው መሆኑንም ግልፅ አድርጌያለሁ ። »

የቡድን ሃያ ጉባኤ ተሳታፊታፊዎች ተጨማሪ የንግድ ማነቆዎች ቢያንስ ለአንድ ዓመት ያህል ለማዘግየትም ተስማምተዋል ። ለ 2 ቀናት በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ የወጣው መግለጫ ይህንኑ በመጨረሻ ደቂቃ ላይ የተደረሰበትን ስምምነት አካቷል ። በዚሁ መሠረት ሃገራቱ እጎአ እስከ 2014 ሃገራቱ ተጨማሪ የንግድ ማነቆ እርምጃዎችን ከመውሰድ ይቆጠባሉ ። ብራዚል አርጀንቲናና ደቡብ አፍሪቃ የንግድ ማነቆው ገደብ የሚያበቃበት ጊዜ ቀድሞም እንደተቀመጠው በ 2013 ያብቃ ባይ ነበሩ ። የተቀሩት ሃገራት ደግሞ እስከ 2015 እንዲራዘም ጠይቀው ነበር ። ይሁንና ለሁለት የተከፈለው ጉባኤ በ ሩስያው ፕሬዝዳንት ቫላድሚር ፑቲን ገላጋይ ሃሳብ መስማማቱን ሮይተርስ ዘግቧል ።

ካይሮ የምርጫ ውዝግብ

ሙባረክ ሞት እንደሚያሰጋቸው በሚሰማበት በአሁኑ ወቅት የግብፅ ምርጫ ውዝግብ እንደቀጠለ ነው ። እጩየ መሀመድ ሞርሲ አሸንፏል የሚለው የሙስሊም ወንድማማቾች ማህበር ትናንት ማስረጃ ያላቸውን አቅርቧል ። ደጋፊዎቹም ለሊቱን ጭምር ታህሪር አደባባይ ነበሩ ። የሞርሲ ተቀናቃኝ የሙባረክ የመጨረሻው ጠቅላይ ሚኒስትር አህመድ ሻፊቅም ድሉ የኔ ነው ብለዋል ። የሻፊቅ የምርጫ ዘመቻ ቡድን የሙስሊም ወንድማማቾች ያቀረበውን ማስረጃም ሃሰት ሲሉ አጣጥሏል ። ሻፊቅ ሀሙስ ውጤቱ ይፋ እንዲሆንና የፕሬዝዳንትነቱንም ሥልጣን እንዲረከቡ ጠይቀዋል ። የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚቴ ሁለቱ ወገኖች ያቀረቡትን አቤቱታ ዛሬ መመልከት ጀምሯል ። ጉዳዩን የመረመረው ነፃ ዳኞች የሚገኙበት ቡድን ግን ቀደም ሲል ሞርሲ ማሸነፋቸውን አረጋግጧል ።

ደማስቆ የሶሪያው ብጥብጥ

ዛሬ ሶሪያ ውስጥ በደረሰ ግጭት የ 46 ሰዎች ህይወት እንደጠፋ አንድ የመብት ተሟጋች ድርጅት አስታወቀ ። መቀመጫውን ብሪታኒያ ያደረገው የዚህ ድርጅቱ ሃላፊ እንደተናገሩት ከተገደሉት ውስጥ 29 ኙ ወታደሮች ሲሆኑ 5 ቱ ደግሞ አምፅያን ናቸው ። ከወታደሮቹ አብዛኛዎቹ የሞቱት ከአማፅያን ጋር በተካሄደ የጨበጣ ውጊያ ነው ። የሟቾቹ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚጨምርበት በሶሪያ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ታዛቢ ቡድን የሶሪያ ቆይታው ለአደጋ የተጋለጠ ቢሆንም በሃገሪቱ ውስጥ የመቆየት የሞራል ግዴታ እንዳለበት የቡድኑ መሪ ሜጀር ጀነራል ሮበርት ሙድ አስታውቀዋል ። ሙድ እንዳሉት የመንግስታቱ ድርጅት መኪናዎች 10 ጊዜ ያህል በቀጥታ 100 ጊዜ ደግሞ በተዘዋዋሪ የተኩስ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል ። ይሁንና ታዛቢዎች ከሶሪያ አይወጡም ። ሆኖም ግን ባለፈው ቅዳሜ ቡድኑ የሶሪያ ተልዕኮውን ለጊዜው ማቆሙን አስታውቋል ። ሙድ ታዛቢው ቡድን ሥራውን እንደገና የሚጀምርባቸውን ሁኔታዎች አስረድተዋል ።

« የመጀመሪያ የሚጠበቅባቸው ምልክት ውይይት እንዲከፈት በይበልጥ መደበኛ ሥራቸውን እንዲያካሂዱ የኃይሉ እርምጃ በሰፊው መቀነስ አለበት ። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መንግሥትና የተቃውሞ ወገን ለታዛቢዎቹ ህልውናና ደህንነት እንዲሁም የመዘዋውር መብት ማረጋጋጫ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ። »

የተልዕኮው የሶሪያ ቆይታ የዛሬ ወር ያበቃል ። ብጥብጡ ከቀጠለ የቡድኑን የሶሪያ ቆይታ ለማራዘም መስማማቱ አሰቸጋሪ እንደሚሆን ምዕራባውያን መንግሥታት እያስጠነቀቁ ነው ።

ደማስቆ የፑቲን አቋም

በሶሪያ የ መንግሥት ለውጥ እንዲደረግ የቀረበውን ሃሳብ ሩስያ ተቃወመች ። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በሶሪያ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ለሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ና ለ ቻይናው ፕሬዝዳንት ሁ ጂንታኦ ፣ የሶሪያ ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ከአሁን በኋላ ሥልጣን ላይ መቆየት አይገባቸውም ማለታቸውን ፑቲን ብጥብቅ ተቃውመዋል ። ፑቲን በሶሪያ ጉዳይ ሌሎች ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸው አሳስበዋል

« ለሌሎች አገሮች ህዝቦች ማን ሥልጣን ላይ ይውጣ ና ማን ይውረድ ሌሎች የመወሰን መብት የላቸውም ። 2 ተኛ ደረጃ ትልቁ ጉዳይ እንዲሁ የሥልጣን ዝውውር እዲደረግ ማብቃት አይደለም ። ዋናው ጉዳይ ሃገር ውስጥ ደም የሚፈስበትስ ውዝግብ ቆሞ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ነው ። ይህን ሁኔታ ደግሞ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው ህገ መንግሥቱን ተከትሎ መሥራት ሲቻል ነው »

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር አንስቶ በቀጠለው የሶሪያው ግጭት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ 14,400 በላይ መሆኑን አስታውቋል ።

የዓለም ዜና