1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሀገር አልባ አፍሪቃውያን በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ የካቲት 9 2011

ከ700,000 በላይ አፍሪቃውያን እትብቶቻቸው የተቀበሩባት አፍሪቃ ውስጥ ሀገር አልባዎች ኾነው ይባትታሉ። መሽቶ ሲነጋ ሥራ የላቸውም። መማር አይችሉም፤ መብትም የላቸውም። እንደው እንደባዘኑ ሕይወትን ይገፋሉ። የአፍሪቃ ኅብረት ለእነዚህ ሀገር አልባ አፍሪቃውያን አንዳች ነገር ያድርግ ሲሉ የመብት ተሟጋቾች ይሞግታሉ።

https://p.dw.com/p/3DTWA
Afrika Obdachlosigkeit - Nubians in Kenia
ምስል picture alliance/AA/R. Canik

«ሕጉ እንዳልተፈጠርክ ሲቆጥርህ እጅግ አብዝቶ ለብዝበዛ፤ ለበደል ትጋለጣለህ።»

ተወልደው ያደጉት ኬንያ ውስጥ ነው። ከግማሽ ምእተ ዓመት በላይ እዛው ኬንያ ውስጥ ኖረዋል፤ ግን ደግሞ ሀገር አልባዎች ናቸው።  ምንጫቸው ከዚምባብዌ ሲኾን፤ ኬንያ የገቡት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1960ዎቹ ውስጥ እንደኾነ ይነገራል። ዛሬም ድረስ ታዲያ ዜግነት ሳይሰጣቸው እዛው ኬንያ ተወስነው ይኖራሉ። ከዚምባብዌ የፈለሱት የሾና ማኅበረሰብ በኬንያ መዲና ናይሮቢ ቁጥራቸው ከ4000 ይበልጣል።

የሾና ማኅበረሰብ ወደ ኬኒያ ከመጡበት ጊዜ አንስቶ የኬንያ ዜጋ እንዲኾኑ የሚያስችል ሕግ በሀገሪቱ አለመኖሩ ሲበዛ ጎድቷቸዋል። አብዛኞቹ ሾናዎች እዛው ኬንያ ውስጥ ተወልደው ያደጉ ቢኾንም ቅሉ ሀገር አልባዎች ናቸው። የ34 ዓመቱ ቶማስ ኩቴንዳ ከሀገር አልባዎቹ አንዱ ነው።

«የተወለድኩት፤ እድገቴና ትምህርቴም እዚሁ ኪያምባ ማማንጂና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ለትምህርት ቤቴ የእጅ ኳስ ተጫውቻለሁ፤ እስከ ብሔራዊ ቡድንም ደርሻለሁ። ስውዲን ሄደን እንድንጋጠምም ተመረጥን። ኹሉም ተጨዋቾች ኬንያውያን ነበሩ እናም የጉዞ ሠነዳቸውን ወዲያው ነው ያገኙት። ምንም እንኳን እኔ የቡድናችን አምበል ብኾንም ስዊድን መኼድ አልቻልኩም። ኬንያን ለመወከል የጉዞ ሠነድ ያስፈልገኛል። ያ ደግሞ የለኝም። ዕውቅና ላልሰጠች ሀገር ተሰልፌ ልጫወት ነበር። የመለያ ልብሴ ከጀርባው ኬንያን እንደምወክል ነው የተጻፈው።»

Afrika Südafrika - Pass
ምስል Getty Images/AFP/G. Guercia

የቶማስ ሀገር አልባነት በሱ ብቻ አላከተመም። ዛሬ ችግሩ ልጆቹ ላይም ተከስቷል። የአብራኩ ክፋዮች በተወለዱባት ሀገር ትምህርት ቤት የሚቀበላቸው ማግኘት አልቻሉም።

«ትምህርት የሚቀስሙበት ስፍራ ለማግኘት እነዚህ ልጆች የትም ልወስዳቸው አልችልም። ቦታ ባገኝላቸው ብዬ እኔ ወደተማርኩበት ትምህርት ቤት ወሰድኳቸው። እዚያም ቢኾን ለመመዝገብ የልደት ምስክር ወረቀት ጠየቋቸው።»

እንደ ቶማስ ኹሉ በዓለም ዙሪያ 12 ሚሊዮን ሰዎች ሀገር አልባ ናቸው። 710,000 ያኽሉ ደግሞ አፍሪቃ ውስጥ ይገኛሉ። አብዛኛዎቹ አይቮሪኮስት ውስጥ ይኖራሉ። አይቮሪኮስት ምጣኔ ሐብቷ ድንገት በተመነደገበት ወቅት ከጎረቤት ሃገራት ማሊ፤ ቡርኪናፋሶ እና ጋና የፈለሱ ሰዎች ሀገር አልባ ኾነው በዛው የቀሩ ናቸው። የሀገሪቱ መንግሥት ያልተመዘገቡ የውጭ ዜጎች ዜግነት ማግኘት አይችሉም የሚል ሕግ ማውጣቱ ፈላሲያኑን ሀገር አልባ ኾነው እንዲቀሩ አስገድዷቸዋል።

በማንነታቸው አለያም በሐይማኖታቸው ይገለላሉ። ራሳቸው ፈላሲያኑ ከኅብረተሰቡ ጋር ለመቀላቀል አለመሻታቸው ሌላኛው ተግዳሮት ነው። ኬንያ ለሚኖሩ ሾናዎች ደግሞ የሃገራቱ ሕግጋት ሌላኛው መሰናክል ነው። ሀገር አልባውያን በየሚኖሩባቸው ሃገራት ሕግጋት ተዘንግተው መከራቸውን ይበላሉ። በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) የኬንያ ቅርንጫፍ ሠራተኛ ካትሪን ሐሞን ሀገር አልባውያን የሚደርስባቸውን መከራ እንዲህ ያብራራሉ።

«ሕጉ እንዳልተፈጠርክ ሲቆጥርህ እጅግ አብዝቶ ለብዝበዛ፤ ለበደል ትጋለጣለህ። ሥራ ማግኘት አትችልም፤ ስለዚህም በማንኛውም ኹኔታ ውስጥ ይኹን ያገኘኸውን ሥራ ትቀበላለህ። ያኔም ለጉልበት ብዝበዛ ትዳረጋለህ። አብዛኛውን ጊዜ ሀገር አልባ ሰዎች እጅግ ይበዘበዛሉ። እናም ለጥቃት የተጋለጡ ሰዎች በቀላሉ በደል ይደርስባቸዋል። በሕገወጥ አዟዟሪዎች እጅ ሊወድቁ፤ ሊበደሉ፤ መጠነ-ሰፊ የመብት ጥሰት ሊገጥማቸው ይችላል።»

UNHCR startet Kampagne gegen Staatenlosigkeit
ምስል picture-alliance/dpa/S. Di Nolfi

የመብት ተሟጋቾች የአፍሪቃ ኅብረት ለሀገር አልባውያን አንዳች መፍትኄ እንዲሻ እየሞገቱ ነው። ምናልባትም ታዲያ መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የአፍሪቃ ኅብረት ለቶማስ እና በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ሀገር አልባ አፍሪቃውያን መፍትኄ ያበጅ ይኾናል። ለጊዜው ግን ችግሩ እንዳለ ዐውቆ ለመፍትኄው እንቅስቃሴ ጀምሯል። የሰብአዊ መብቶች፤ የዲሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ባለሞያዋ ብራውን ማንዲም ያንኑ ነው አስረግጠው የሚናገሩት።

«የአፍሪቃ ኅብረት በእርግጥ አፍሪቃ ውስጥ ሀገር አልባነትን ለማስወገድ የአፍሪቃ ሰብአዊ መብቶች መተዳደሪያ ደንብን በግሩም ኹኔታ እያረቀቀ ነው። ያ በትንሹም ቢኾን ሀገር አልባነትን ለማስወገድ ጠቃሚ ይኾናል።»

ከዚህ ኹሉ ግን ይላሉ፦ በጆሐንስበርግ ዩኒቨርሲቲ መምሕር የኾኑት ክርስቲያኖ ዲኦርሲ፦ ከዚህ ኹሉ ለሀገር አልባ አፍሪቃውያን ወሳኙ አፍሪቃ አቀፍ ፓስፖርትን ማዘጋጀት ነው።

«የአፍሪቃ አቀፍ ፓስፖርት ሐሳብ እየተብላላ ነው። ያ ማለት በአፍሪቃ ምድር የተወለደ ኹሉ በመሠረቱ ከአፍሪቃ ፓስፖርት ተጠቃሚ ይኾናል። በእርግጥ ገና በሒደቱ ጅማሬ ላይ ነን። ኾኖም ይኽ ችግሩን ለመቅረፍ ኹነኛ ጅማሮ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።»

እናስ አፍሪቃ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሀገር አልባ ልጆቿ የሚያሰሙትን ጩኸት አድምጣ ልጆቼ ብላ ታቅፋቸው ይኾን? ሀገር አልባውያን ግን ድምጻቸው አኹንም ያስተጋባል።

ሲልጃ ፍሮይኅሊሽ/ ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ