1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለሱዳን በምስጢር የተሰጡት የእርሻ መሬቶችና ዉዝግቡ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 8 2011

በኢትዮጵያ እና ሱዳን የወሰን ድንበሮች የሚገኙ የኢትዮጵያ የእርሻ መሬቶች ፓርላማ ተወያይቶ ሳያጸድቅ ስልጣን ላይ በነበሩ የኢሃዲግ አመራር ፊርማ ለሱዳን ተላልፈው መሰጠታቸው ስህተት እንደነበር አንድ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሃላፊ አስታወቁ ።

https://p.dw.com/p/36nNo
Afrika Kongo Brandrodung Kohle
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Gouby

በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማስመለስ አንድ ኮሚቴ ተቋቁሟል

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ልዩ ረዳት እና የኮምኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አብይ ኤፍሬም ለ «DW» እንዳብራሩት ህጋዊ ተቀባይነት በሌለው ስምምነት ከአማራ ክልል ተላልፈው የተሰጡት መሬቶች በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲመለሱ የሚያደርግ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራውን ጀምሯል። የቀድሞ የመተማ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሙሉዓለም ገሌ በበኩላቸው ገዥው የኢህአዲግ መንግስት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ስልጣኑን የሚቀናቀኑ በሱዳን ድንበር አካባቢ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ትጥቅ ያነሱ ተቃዋሚ ኃይላትን ለማጥፋት ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ስር የነበረው ከ 23 ሺህ ሄክታር የሚልቅ የመተማ ደለሎ ለም የእርሻ መሬት ከ 12 ኪሎ ሜትር በላይ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመዝለቅ ለሱዳን አሳልፎ ሰቷል ሲሉ ወቅሰዋል። የቀድሞ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩት ባለስልጣን መሬቱ ለሱዳን ተላልፎ እንዲሰጥ ባቀረቡት ሰነድ ላይ አልፈርምም ካሉ በኋላ በማያውቁት ጉዳይ 38 የተለያዩ ክሶች ተመስርቶባቸው ከ 4 ዓመታት በላይ መታሰራቸውንም አቶ ሙሉዓለም ገልጸዋል ። የኢትዮጵያ መንግስት በሚስጥራዊ ስምምነት ከ 23ሺህ ሄክታር በላይ መተማ ደለሎ የሚገኘውን የአገሩን መሬት ቆርሶ ለሱዳን ሰቷል በሚል በአካባቢው የሚኖሩ አርሶአደሮች በተቃውሞ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ድርጅቶች አክቲቪስቶች እና የኢትዮጵያ የድንበር ጉዳይ ኮሚቴ በሚል የተቋቋመ ገለልተኛ ድርጅት ጭምር ሲያቀርቡ ለነበረው ተደጋጋሚ ክስ የአገሪቱን ሰላም ለማወክ የሚጥሩ ጸረ ሰላም ሃይሎች የፈጠራ ክስ ነው በማለት ሲያጣጥለው ቀይቷል።

የአዴፓ አመራሮችም ሆኑ የፌደራል መንግሥት ባለስልጣናት በ 1988 ዓ.ም በሁለቱ አገራት መካከል በተካሄደው የድንበር ግጭት ገፍተን ከያዝነው የሱዳን መሬት ለቀን ወተናል እንጂ የሰጥነው መሬት የለም በማለት ማስተባበላቸው አይዘነጋም።

ይሁን እንጂ እንደ ሱዳን ትሪቡን ያሉ የዜና አውታሮች እ.ኤ.አ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በተለይም በኢትዮ-ሱዳን ድንበር አቅራቢያ በአትባራ ወንዝ ዙሪያ የሚገኙ የምሥራቃዊ ሱዳን ገበሬዎች ከ 100 ዓመታት በላይ አወዛጋቢ ሆነው የቆዩ የእርሻ መሬቶቻቸው እንደተመለሱላቸው የሚገልጹ ዘገባዎችን በሰፊው ሲያሰራጩ ቆይተዋል። የመሬቱን ለሱዳን ተላልፎ መሰጠት የተቃወሙ ገበሬዎች በጎንደር እና ማዕከላዊ እስርቤቶች የሽብር ክስ እየተመሰረተባቸው ሰቆቃ እንደተፈጸመባቸውም ይነገራል። የአማራ ክልል የጸጥታ እና ደህንነት ሃላፊ በነበሩበት ወቅት ከሱዳን መንግስት ጋር ምስጢራዊውን ስምምነት ተፈራርመዋል እየተባለ ትችት ሲሰነዘርባቸው የቆዩት የአዴፓ የወቅቱ ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በቅርቡ ከአማራ ቴሌቪቭን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ስምምነቱ በተፈጸመበት ወቅት ለትምህርት እንግሊዝ ሃገር እንደነበሩ እና ሆን ተብሎ ስማቸውን የማጥፋት ዘመቻ ሲካሄድ መቆየቱን በመግለጽ ተላልፎ የተሰጠው መሬት ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ የግዛት ሉዓላዊነት ስር እንደነበረ ሲሰሙ በተፈጸመው ታሪካዊ ስህተት ክፉኛ መደንገጣቸውን ነበር የገለጹት ።

ቀደም ባሉት መንግስታት በአጼ ምኒልክ በቀዳማዊ ኃይለስላሴም ሆነ በደርግ ሥርዓት በታሪክ ሱዳን ጓንግን ተሻግሮ አሁን ከኢትዮጵያ ተቆርሶ እስከተሰጠው ለም እና የተንጣለለው የደለሎ የእርሻ መሬት አንዳችም የባለቤትነት ይዞታ እንዳልነበረው የቀድሞ የመተማ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሙሉዓለም ገሌ በተለይ ለ ዲ ደብሊው ገልጸዋል። በ1983 ዓ.ም የደርግ ሥርዓት ማብቂያ ላይ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር አካባቢ የነበረው ወታደራዊ ጥበቃ መሳሳቱን ተከትሎ የሱዳን ባለሃብቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ጓንግን ተሻግረው አካባቢውን በሱዳን ሜካናይድ ጦር ሃይል እገዛ ተቆጣጥረው ማረስ መጀመራቸውንም አብራርተዋል። በተለይም ከ 1986 ዓ.ም በኋላ አንግረብን ተሻግረው የአርማጮሆን መሬት , በቋራም ነፍስገበያን እንዲሁም ጓንግንም አልፎ በመተማ-ደለሎ አብደረግ ሽመልጋራ እና ሌሎችም አካባቢዎች የሱዳን ሰራዊት ከፍተኛ መስፋፋት በማድረጉ በኢትዮጵያ አርሶአደሮች እና በመከላከያ ሰራዊት መልሶ ጥቃት ሙሉ በሙሉ ከአካባቢው በማባረር ጓንግን ዳግም ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እንዳይዘልቁ ለማድረግ ተችሎ ነበር። ይሁን እንጂ በ 1988 ዓ.ም ከሱዳን ሰልጥነው የመጡ ናቸው የተባሉ አሸባሪዎች አዲስ አበባ ላይ የሚካሄደውን የአፍሪቃ ህብረት ጉባኤ ለመሳተፍ በመጡት የግብጹ ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ ላይ የግድያ ሙከራ መፈጸማቸውን ተከትሎ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው በመሻከሩ ሁለቱም አገራት የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ ተቃዋሚዎችን መርዳት እና ማደራጀት መጀመራቸው ታውቋል። ይህ ውዝግብ ባልተፈታበት ሁኔታ ነው የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጦርነት በመቀስቀሱ ስልጣኑ በውስጥም በውጭም ሃይላት አጣብቂኝ ውስጥ የገባው መንግስት በጦርነት ተገፍቶ የተያዘ ነው በሚል ሰበብ ለውለታ መክፈያነት መሬቱን በምስጢር ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት ከውሳኔ ላይ የደረሰው ይላሉ የቀድሞ የመተማ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሙሉዓለም ።

አቶ ሙሉዓለም ዓ.ም ሱዳን እና ኢትዮጵያ የሚወዛገቡባቸን መሬቶች ለመለየት ከሁለቱም አገራት የተውጣጣ የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ ባደረገው ሰፊ ጥናት ማስረጃዎችን አርሶ አደሮች ግብር የከፈሉባቸውን ደረሰኞች እና የነዋሪነት መታወቂያዎችን መርምሮ ከ 95 በመቶ በላይ የይገባኛል ጥያቄ የቀረበባቸው መሬቶች የኢትዮጵያ መሆናቸው ተረጋግጦ የሱዳን ተወካዮችም በጥናቱ ላይ መፈረማቸውን ይናገራሉ። ይሁንና በተለይም ከፍተኛ የኢትዮጵያ የእርሻ ልማት ይካሄድበት የነበረው የመተማ ደለሎ አካባቢ ሰፊ ለም መሬት እንዲሰጣቸው ሱዳኖች ተደጋጋሚ ውትወታ በማቅረባቸው ጉዳዩ የመጨረሻ እልባት ሳይሰጠው በእንጥልጥል ቆየ። አቶ ሙሉዓለም በሚያዝያ ወር 1995 ዓ.ም የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ከነበሩት አቶ አባይ ጸሃዬ ደለሎ ድረስ በአስቸኳይ እንዲመጡ ትዕዛዝ ደረሳቸው ። እዛም በጦር ሄሊኮፕተክ የመጡ የሱዳንን ባለስልጣናት ጋር ተገናኙ ። የደለሎ መሬት ከአጼ ምኒልክ ጀምሮ እስከ ደርግ ዘመን ሲያወዛግብ መቆየቱን በመግለጽ ለሰላም ሲባል መሬቱ ለሱዳኖች እንዲሰጣቸው ቢያግቧቧቸውም ሕዝባዊ ተቃውሞን የሚቀሰቅስ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ እጃቸውን በማስገባት የታሪክ ተጠያቂ መሆን እንደማይፈልጉ መግለጻቸውን ነው አቶ ሙሉዓለም ያስረዱት።

ለሱዳን ይሰጥ በተባለው መሬት ላይ እጄን አላስገባም አልፈርምም ያሉት አቶ ሙሉዓለም በመጨረሻ በማያውቁት ጉዳይ 38 ያህል ልዩ ልዩ ክስ ተመስርቶባቸው አብዛኛው ማስረጃ ሊቀርብበት ባለመቻሉ ውድቅ ቢሆንም በ 2 ክስ 4 ዓመት ከ 8 ወራት ተፈርዶባቸው ለእንግልት መዳረጋቸውን ገልጸውልናል። አቶ አባይ ጸሃዬ የተፈራረሙበት የስምምነት ሰነድ ይፋ ከሆነ በኋላ የህዝብ ተቃውሞው ከየአቅጣጫው በመቀጣጠሉ ሱዳን ከ 12 ኪሎ ሜትር በላይ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንድትገባ በማድረግ የተሰጣት ከ 23 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአገር ሉአላዊነትም ሆነ በቀጣዩ የድንበር ማካለል ሂደት ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ተጽዕኖ በመገምገም አዴፓ በቅርቡ ባካሄደው ድርጅታዊ ጉባኤ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰቶ እንደሚንቀሳቀስ ውሳኔ አሳልፏል። የኢትዮጵያ ፓርላማ ተወያይቶ ሳያጸድቀው ለሱዳን የተሰጠው ይኸው መሬት እንዲመለስ የተደረገው ምስጢራዊ የፊርማ ስምምነት ህጋዊነት እንደማይኖረው እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መሬቱን ለማስመለስ ጥረት የሚያደርግ አንድ ኮሚቴ መቋቋሙንም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ልዩ ረዳት እና የኮምኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አብይ ኤፍሬም ገልጸውልናል።

የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ ከሱዳን የመከላከያ ሚኒስትር ሜጀር ጄኔራል አብዱልራሂም ሞሃመድ ሁሴን ጋር ምስጢራዊውን ሰነድ ከመፈራረማቸው ቀደም ብሎ የደለሎ አካባቢ መሬት ለሱዳን ተላልፎ ከመሰጠቱ በፊት የብአዲን የልማት ድርጅት የነበረው ዘለቀ ሜካናይዝድ የእርሻ ልማት ከ 70 የሚልቁ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች እና በመቶዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ጭምር በዚሁ አካባቢ ሰፊ የግብርና ልማት እንቅስቃሴ ያካሂዱ እንደነበረ ያስታወሱት አቶ ሙሉዓለም የፌደራል መንግስትም ይሁን የብአዲን አንዳንድ አመራሮች ስልጣናቸውን ላለማጣት ሲሉ ነገሩን እንደማያውቁ በማስመሰል በርካታ አርሶ አደሮች የህይወት ዋጋ የከፈሉበትን ይህን በአገር ሉዓላዊነት ላይ የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት እንዳይነሳ ሲያድበሰብሱ ቆይተዋል ሲሉ ይወቅሳሉ። የኢትዮጵያ መንግስት ለሱዳን ከሰጠው የመተማ ደለሎ መሬት ሌላ አሁንም ሱዳኖች ተጨማሪ መሬት ለመውሰድ የሚያስችላቸው ሌላም ምስጢራዊ ስምምነት እንዳለ ከተለያዩ የካርታ ሰነዶች ተገንዝቤያለሁ የሚሉት የቀድሞ የመተማ አስተዳዳሪ አቶ ሙሉዓለም ገሌ የመንግሥት አካላት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡትም ጥሪ አስተላልፈዋል።

 እንዳልካቸው ፈቃደ

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ