1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"ለውጡን ለማቆም የሚችል አንዳች የሞት ኃይል የለም" ጠቅላይ ምኒስትር አብይ

ሰኞ፣ ሐምሌ 9 2010

የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ማብሰሪያ በተባለው መድረክ ጠቅላይ ምኒስትር አብይ "ብዙ ስንገብር የመጣን ቢሆንም ለውጡን ለማቆም የሚችል አንዳች የሞት ኃይል የለም" ሲሉ ተደምጠዋል። የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ "በጋራ ጥረታችን የከሰርንውን አስመልሰን ለመጪው ጊዜ ግዙፍ ክንዋኔዎችን ሰርተን እንደምናሸነፍ እርግጠኞች ነን" ብለዋል

https://p.dw.com/p/31V5C
Eritrea - Der äthiopische Ministerpräsident Abiy und der eritreischen Staatschef Afewerki
ምስል Reuters/G. Musa Aron Visafric

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ «ለውጡን ሊያቆም የሚችል አንዳች የሞት ኃይል የለም» አሉ። ይኽን የተናገሩት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን አዲስ የሰላምና የወዳጅነት ምዕራፍ ለማብሰር በሚል ዛሬ አዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ውስጥ በተከናወነው ሥነሥርዓት ነው።

ጠቅላይ ምኒስትሩ "እኔ እንኳን የትናንትና የአዲስ አበባ የሕዝብ ፍቅር፤ የሐዋሳ ሕዝብ ፍቅር ዛሬ የእናንተን የማይነጥፍ ፍቅር ማየት የቻልኩት ሰኔ 16 ሁለት ጀግኖች ሕይወታቸውን ገብረው ነው። ብዙዎች ሴቶች ሳይቀሩ አካላቸውን አጉድለው ነው። ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው ብዙ ስንገብር የመጣን ቢሆንም ለውጡን ለማቆም የሚችል አንዳች የሞት ኃይል የለም" ሲሉ ተናግረዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ "አንድ ሰው ገድሎ ለውጥን ማደናቀፍ እንደማይቻል በተግባር ማስተማር ይኖርብናል" ሲሉ አክለዋል።

"የምንደመረው ለፍቅር እና ለይቅርታ ብቻ ይሁን፤ ለክፋት እና ለመግደል አንደመርም። የእኛ መደመር ለሌሎች ተስፋ እንጂ ጭንቀት አይሆንም" ብለው ሲናገሩ ታዳሚዎች በሆታ አጅበዋቸዋል። ንግግራቸው "ይደገም" የተባለበት ቅፅበትም አልጠፋም። አብይ ሥልጣን ከያዙ በኋላ በተደጋጋሚ ከአንደበታቸው የተደመጠውን የመደመር ፅንሰ ሐሳብ ከማቲማቲክስ ጋር አነፃፅረው ሊያስረዱ ሞክረዋል። "መባዛት ብቻ ሳይሆን ግን የእኛ የመደመር መፈክር መቀነስም አለው። የእኛ የመደመር መፈክር የሚቀንሰው በደል፣ ቂም፣ ክፋት፣ ጥላቻ፣ ስንፍና ቀማኛነት፤ ሀገር አለመውደድ፣ ሕዝብ አለማገልገል" የመሰሉ ጉዳዮችን እንደሆነ ገልጸዋል።

ከሃያ አምስት ሺህ በላይ ታዳሚያን መገኘታቸው በተገለጠበት ሥነ ሥርዓት ላይ «ክቡር የኢትዮጵያ ህዝብ» ብለው አጠር ያለ ንግግራቸውን በአማርኛ ቋንቋ ያሰሙት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ «ያለፈው በባሕላችን እና ታሪካዊ ጥልቅ ጥቅሞቻችን አንፃር ጥላቻ እና ቂም በቀል ውድመት ለመንዛት የተሞከረውን ሲራ አሸንፈን ለልማት ብልፅግናና መረጋጋት በሁሉም መስክ እና ግንባር አብረን ልንመርሽና ወደፊት ለመራመድ ቆርጠን ተነስተናል" ሲሉ ተናግረዋል።

በመርኃ-ግብሩ ላይ በጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ እና በታዳሚያን "ኢሱ" እየተባሉ የተቆላመጡት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ደረታቸውን እየጠበጠቡ፣ ጭንቅላታቸውን እያወዛወዙ ስሜታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ "ማንም ፍቅራችንንና ስምምነታችንን ለመበተንና ለማወክ፤ እርጋታችንን ለማሸበርና ለማጥቃት፣ ልማትና ዕድገታችንን ለማደናቀፍና ለማውደም እንዲፈታተነን አንፈልግም። በጋራ ጥረታችን የከሰርንውን አስመልሰን ለመጪው ጊዜ ግዙፍ ክንዋኔዎችን ሰርተን እንደምናሸነፍ እርግጠኞች ነን"ሲሉ ተናግረዋል።

በሚሊኒየም አዳራሽ በፕሬዚዳንቱ የተመራው የኤርትራ ልኡክ እንዲሁም ሌሎች ባለስልጣናትም ተገኝተዋል። ታዳሚያኑ «ዐቢይ፣ ኢሳያስ፣ ለማ፣ ደጉ» እያሉ በጩኸት ድጋፋቸውን ሲገልጡ ተሰምተዋል።በሃይማኖት አባቶች ቡራኬ በተከፈተው መርሐ-ግብር ማሕሙድ አሕመድ እና አሊ ቢራን የመሳሰሉ ሥመ-ጥር ድምፃውያን ሥራቸውን አቅርበዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ