1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለየመን ሰላም ጥረት ጀርመን ፖለቲካዊና የገንዘብ ድጋፍን ታደርጋለች

ሐሙስ፣ ጥር 9 2011

የጀርመን መንግሥት በየመን የሰላም ጥረት 4.5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደሚሰጥ ተገለፀ ። ይህ የተነገረዉ የጀርመኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ በየመን ጉዳይ ላይ ረቡዕ በርሊን ላይ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ጉባዔ በተቀመጡበት ወቅት ነዉ።

https://p.dw.com/p/3Bjz9
Deutschland Jemen-Konference in Berlin | Außenminister Heiko Maas
ምስል picture-alliance/AA/A. Hosbas

ጀርመን ለየመን 4. 5 ሚሊዮን ዩሮ ትሰጣለች

የጀርመን መንግሥት በየመን የሰላም ጥረት 4.5 ሚሊዮን ዩሮ  ድጋፍ እንደሚሰጥ ተገለፀ። ይህ የተነገረዉ የጀርመኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ በየመን ጉዳይ ላይ ትናንት በርሊን ላይ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ጉባዔ በተቀመጡበት ወቅት ነዉ። ረቡዕ በርሊን ላይ በነበረዉ በዚህ ጉባዔ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የየመን ልዑክ ማርቲን ግርፊዝ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየመን የሰብዓዊ ርዳታ አስተባባሪ ሊዛ ግራንዴ ተገኝተዋል።
ከጎርጎረሳዉያኑ 2015 ጀምሮ በእርስ በርስ ጦርነት የደቀቀችዉ የየመን ተፋላሚ ኃይሎች ስዊድን ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ካደረጉ በኋላ በሃገሪቱ አሁንም አልፎ አልፎ ግጭት፣ ተኩስ በመታየቱ ስምምነቱ እክል እንደገጠመዉ ተነግሮአል። ይሁንና በየመን ሰላም ለማስፈን የተደረሰዉ ስምምነት ለሰላም መምጣት ፈር ቀዳጅ በመሆኑ ለየመን ሰላም ማግኘት ተስፋን ማጫሩን ትናንት በርሊን ላይ በተካሄደዉ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ተመልክቶአል። የጀርመኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ ባለፈዉ ወር መጨረሻ ስዊድን ስቶክሆልም ላይ የተደረሰዉን የተኩስ አቁም ስምምነትን ጨርሶ ገቢራዊ ለማድረግ በሚደረገዉ ጥረት  ጀርመን 4. 5 ሚሊዮን ዩሮ  ርዳታን ለመስጠት ዝግጁነትዋን ገልፀዋል።  
«ለየመን ሰላም መስፈን ከፍተኛ ስኬት የተገኘበት የስቶኮሆልሙን ስምምነት ለማስቀጠል ዛሬ እዚህ ተገናኝተናል። ይህን የሰላም ጅማሮን ከኛ ጋር ሆነዉ ለማስቀጠል ከዓለም የተሰበሰቡ በርካታ አጋሮቻችን እዚህ ከኛ ጋር ይገኛሉ። ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀዉስ አደጋ ዉስጥ በምትገኘዉ  የመን የሚታየዉን ጦርነት ጨርሰን ካላስቆመን ሁኔታዉ አሳሳቢ ይሆናል። እኛ ማለትም የጀርመን መንግሥት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የየመኑን ልዑክ ማርቲን ግርፊዝንን በተቻለ አቅማችን ሁሉ እንደግፋለን። በዚህም ሊዛ ግራንዴ ለየመን ርዳታ በሚያስተባብሩበት ሥራ ላይ የመጀመርያዉ ርዳታ አቅራቢዎች በመሆን  4.5 ሚሊዮን ዩሮ እንሰጣለን። ሌሎችም ይህን ምሳሌ ይከተላሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። »  
የጀርመኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የየመን ልዑክ ማርቲን ግርፊዝ ለየመን ሰላም መምጣት ፈር ቀዳጅ የሆነውን የሰላም ስምምነት በስቶኮልም እንዲደረስ በማድረጋቸው ስኬታማ ስራ ሰርተዋል ብለዋል። የየመን የሰላም ጥረት መጀመር ስኬት አንድ  «ትልቅ የብርሃን ብልጭታ ነዉ» ብለዉታል። 
«በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታዉ ምክር ቤት፤ በዓለም ዙርያ የሚታይ በርካታ ግጭትና ቀዉሶችን ይዘን እየተጓዝን መሆኑ በሚታወቅበት ሁኔታ ለየመን ሰላም ጥረት መጀመሩ እና በፖለቲካዊ ሂደት ጦርነቱን ማስቆም ከቻልን ለየመን ትልቅ የብርሃን ብልጭታን ማየት  ነዉ» በየመን ተፋላሚ ወገኖች መካከል ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት የሃገሪቱ ዋነኛ የባህር በር የሆነችው የሆዴይዳ ወደብ እና ከተማዋን ከውጊያ ነጻ ማድረግ የሚል መሆኑ ይታወቃል።  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የየመን ልዑክ ማርቲን ግርፊዝ ለ «DW» በሰጡት ቃለ ምልልስ ለየመን ሰላም መምጣት «ጦርነቱን ጨርሶ ከማስቆም ዉጭ ሌላ አማራጭ የለም» ብለዋል። ማርቲን ግርፊዝ የየመን ተቀናቃኝ ወገን ተወካዮች ስቶክሆልም ላይ ያካሄዱትን ስምምነት ተግባራዊ እያደረጉ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል። « ባለፈዉ ሳምንት ያየሁት ዋንኛ ነገር ቢኖር፤ የሁለቱ ተቀናቃኝ ወገን መሪዎች፤ ፕሬዚዳንት አብዱ ራቡ መንሱር ሃዲ እና የየመን አማጽያን መሪ አብደል ማሊክ ኧል-ሁቲን ባለፈዉ ሳምንት አግንቻቸዉ ነበር። ሁለቱም ወገኖች ስዊድን ላይ የተስማሙበትን ነጥቦች በቀጣይ በጽናት እንደሚተገብሩት ገልፀዉልኛል። » 
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የየመን ልዑክ ማርቲን ግርፊዝ እክል ታይቶበታል የተባለዉን የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ ከሳምንት በፊት ከሁለቱ ወገኖች ጋር ለመወያየት ወደ ሰንዓ እንዲሁም ከየመን መንግሥት ባለስልጣናት ጋር ለመወያየት ወደ ሳዑዲ አረቢያ መዲና ሪያድ ተጉዘዉ ነበር። ማርቲን ግርፊዝ ለ«DW» በሰጡት ቃለ ምልልስ ለየመን ጦርነቱን ከማስቆም እና ሰላም ከማስፈን ሌላ አማራጭ እንደሌለ አስረግጠዉ ተናግረዋል።  « ከሰላም ሌላ ምንም አይነት አማራጭ የለንም። ይህንንም እናሳካላን። እኔን ያስደነቀኝ ነገር ቢኖር የተኩስ አቁም ስምምነቱን በተመለከተ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ካልሆነ በስተቀር ስምምነቱ በጥሩ ሁኔታ ገቢራዊ እየሆነ ነዉ። በሆዴይዳ ይታይ የነበረዉ ግጭት በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሰረት ከታህሳስ 8 ጀምሮ በትክክል ገቢራዊ ሆንዋል። እርግጥ ነዉ ይህ ሁኔታ ሊቀየር የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል፤ እንዲያም ሆኖ ስምምነቱ ተፈፃሚ እንዲሆን በጽናት እንቆማለን። እስካሁን ግን በሆዴይዳ ሙሉ በሙሉ ስኬታማ ነን። » በሆዴይዳ አልፎ አልፎ ግጭቶች እንደሚታዩ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ባለፈው ሳምንት ዘግቦ ነበር።  ለግጭቶቹ የየመን መንግስት የሁቲ አማጽያን የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሰዋል ሲል ይከሳል። አማጽያኑ በበኩላቸው በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ወታደራዊ ጥምረት የጦር አውሮፕላኖች አሁንም በከተማይቱ ዝቅ ብለው እየበረሩ ነዉ ሲሉ መወነጃጀላቸዉን መቀጠላቸዉ ዘገባዎች አሳይተዉ ነበር።   

Schweden | Friedensgespräche Jemen-Konflikt
ምስል Getty Images/AFP/J. Nackstrand
Jemen Ankunft Martin Griffiths in Sanaa
ምስል Getty Images/AFP/M. Huwais


አዜብ ታደሰ 
ተስፋለም ወልደየስ