1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለጤናችን እንቅስቃሴ እናዘውትር

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 2 2011

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ ሃገራት ውስጥ በማይተላለፉ በሽታዎች የሚጠቃው ሕዝብ ቁጥር ከፍ እያለ መሄዱን መረጃዎች ያሳያሉ። የዓለም የጤና ድርጅት እንዲህ ያሉ ህመሞች በየዓመቱ በዓለም ከሚከሰተው ሞት 63 በመቶውን እንደሚያደርሱ ያመለክታል።

https://p.dw.com/p/39tLZ
"Car Free day" in sieben Städten in Äthiopien am 09.12.2018 in Addis Abeba
ምስል Ethiopian Ministry of Health

ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች ብዙም ሳይወራላቸው ብዙ ጉዳት ያደርሳሉ

 ከማይተላለፉ ህመሞች የልብ ህመም፤ የደም ዝውውር መታወክ ወይም ስትሮክ፤ ካንሰር እና የስኳር ሕመም በዋናነት ይጠቀሳሉ።አብዛኞቹ ወትሮ የበለፀገው ዓለም ኅብረተሰብ ሕመም ተደርገው ሲታዩ ቢቆዩም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ድሀ ወደሚባሉት ሃገራት ጎራ ብለው በእነሱ ምክንያት ለሞት የሚዳረገው ሕዝብ ቁጥር ከፍ ብሏል። ለዚህ በዋና ምክንያትነት የሚጠቀሰው የሰዎች የኑሮ ሁኔታ መለወጥ እና አመጋገብ ነው። የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለሰዎች ሞት ምክንያት የሆኑ መንስኤዎችን የተመለከተ ጥናት አካሂዶ እንደነበረ እና ውጤቱ ደግሞ ተመሳሳይ ችግር መኖሩን ማመላከቱን ሚኒስትሩ ለDW ገልጸዋል። ጥናቱን ተንተርሶም ኅብረተሰቡ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግን እንዲያዘወትር አንድ መርሃግብር ነደፈ። ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ለጤናማ ሕይወት በሚል ከተሽከርካሪ ነፃ ቀን፤ ከትናንት በስተያ እሁድ ዕለት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ሰዎች በእግር እንዲጓዙ አብረውም የአካል እንስቃሴ እንዲያደርጉ አመቻቸ። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን መርሃግብሩ መሠረት ያደረጋቸውን ነጥቦች ዘርዝረዋል።

ይህ የተጀመረ መርሃግብር ከሁሉም የክልል ከተሞች ርዕሰ መስተዳድሮች እና በየደረጃው ካሉ አካላት ጋር በመወያየትም ተስፋፍቶ እንዲቀጥል መታሰቡንም ነው የገለፁት። እስካሁንም ሰባት የክልል ከተሞች በዚህ ለመሳተፍና ለመቀጠልም ቃል መግባታቸውንም አመልክተዋል። 

በሙያቸው የነርቭ ስፔሻሊስት መሆናቸውን የገለፁት ዶክተር ሜሎን በቀለ ከተሽከርካሪ ነፃ የሚለውን መርሃግብር ከጤና ጥበቃ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የአፍሪ ሃውስ ትሬዲንግ ባልደረባ ናቸው። ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የሰዎች ሕይወት ያለፈበትን ምክንያት አስመልክቶ የተሠራው ጥናት ከግማሽ በመቶ የሚበልጡት ምክንያተ ሞታቸው የማይተላለፉ የሚባሉት ህመሞች መሆናቸውን ማሳየቱን በመጥቀስ መርሃግብሩ ዜጎች ጤናቸውን በማሰብ እንቅስቃሴ እንዲያዘወትሩ ለመቀስቀስ እንዳለመ ያስረዳሉ።

በየዓመቱም በመላው ዓለም የማይተላለፉት ህመሞች ምክንያት 36 ሚሊዮን ሰዎች እንደሚሞቱ ነው የዓለም የጤና ድርጅትየሚያመለክተው። ከተጠቀሰው ቁጥር ደግሞ 80 በመቶው የሚከሰተው ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሃገራት ነው።  ቀደም ሲል ተላላፊ ለሆኑ በሽታዎች ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ የነበረ ሲሆን የማይተላለፉ ህመሞች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ትኩረት እያገኙ መጥተዋል።

Äthiopien Addis Abeba | Federal Minstry of Transport building
ምስል DW/H. Melesse

ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር የወጣ አንድ መረጃ እንደሚያሳየው ከመቶ ሚሊየን በላይ ሕዝብ ባለባት ኢትዮጵያ የሚገኘው የተሽከርካሪ ቁጥር 708,410 ነው። ከእነዚህም 62 በመቶው የሚገኘው በዋና ከተማ አዲስ አበባ ነው። የአዲስ አበባን ጎዳናዎች የሚያጨናንቁት እነዚህ ተሽከርካሪዎች ወደከባቢ አየር የሚለቁት ሙቀት አማቂ ጋዝም ሌላው የጤና ጠንቅ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች በይፋ ያሳሰቡ ጥቂት አይደሉም። መንገዶችን ከተሽከርካሪ ነፃ የሚያደርገው ይህ ጅምር በየወሩ መጨረሻ አንድ ቀን ይቀጥላል። ተከታታይነት መኖሩ ሰዎች እንዲለምዱት እና ከአንድ ቀኑም ጨመር እያደረጉ ለራሳቸው ጤና ብቻ ሳይሆን ለአካባቢያቸውም የበኩላቸውን ጥበቃ የሚያደርጉበት መንገድ ሊያመቻች እንደሚችል ይታመናል።

በነገራችን ላይ በሥራ ቦታም ሆነ በተለያዩ ስፍራዎች ረዥም ሰዓት መቀመጥ፤ ቅርብ ወደሆኑ ቦታዎች ሳይቀር መጓጓዣን መጠቀም፤ ደረጃዎች ባሉበት ሁለት ሦስት ፎቆችን በአሳንሰር መዉጣት ብዙዎች የማናስተውለው ግን ደግሞ በሂደት ጤናችን ላይ ችግር ሊኖረው የሚችል መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለዚህም ነው በሥራ ቦታ እያሰቡ ለተወሰኑ ደቂቃዎች መንቀሳቀስ እና የእግር ጉዞ ማዘውተር፤ ለጤና ጠቃሚ መሆኑን የሚመክሩት። ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው ጤና ላይ ትኩረት ያደረገው ከተሽከርካሪ ነፃ ቀን ሲጀመር 10 ሺህ የተገመቱ ወገኖች ቢሳተፉበትም ውሎ አድሮ የብዙዎችን ትኩረት መሳብ እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ