1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ ውስጥ ለሚታየዉ የፅንፈኝነት አዝማሚያ ድህነት ትልቅ ሚና ይጫወታል፤ UNDP

ረቡዕ፣ መስከረም 3 2010

ከሃይማኖት ይልቅ ድህነት አፍሪቃ ዉስጥ ወጣቶችን ወደ ጽንፈኝነት እንዲያጋድሉ እያደረገ እንደሚገኝ ተጠቆመ። ይህን ያመለከተዉ አዲሱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናት ዕድሎች ለጠበቡባቸዉ ወጣቶች መፍትሄ ካልተፈለገ ችግሩ ይበልጥ እየተባባሰ እንደሚሄድም አስጠንቅቋል።

https://p.dw.com/p/2ju0X
Senegal Talibe bittet um Geld in Dakar
ምስል picture-alliance/Zuma Press/S. Gil Miranda

ከሃይማኖት ይልቅ ድህነት በፅንፈኛ ድርጅቶች ለመሳብ ሚና አለዉ፤

ካዲጃ ሃዋጃ ጋምቦ ለረዥም ዓመታት አንድ ጥያቄ በሃሳቧ ሲመላለስ ከርሟል። ጥያቄውም፤ ለመሆኑ ሙስሊም ወጣቶችን ወደፅንፈኛ ሙስሊምነት የሚስባቸዉ በዚህ አማካኝነትም እንደቦኮ ሃራም ወዳሉ ጂሃዲስት ድርጅቶች የሚከታቸዉ ምንድነዉ የሚል ነዉ። ናይጀሪያዊቱ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች እንደምትለዉ ብዙዎቹ የናይጀሪያ ወጣቶች ተስፋ መቁረጥ ይታይባቸዋል። በዚህ ምክንያትም ካሉበት ችግር የሚያወጣቸዉ አማራጭ መንገድ እንደሚፈልጉ ትናገራለች።
«አንዳንድ ሰዎች በራሳቸዉ ተቋማት ላይ ባደረባቸዉ ተስፋ መቁረጥ ምክንያት የተሻለ ኑሮ ለመኖር ወደፊት መጓዝ ይፈልጋሉ። ማለትም አማራጭ ይፈልጋሉ። እንደዚያ ወዳሉት ድርጅቶች የሚሄዱትም አማራጭ ፍለጋ ነዉ።»
ወደዚያ ገብተዉ አክራሪ ለመሆንም የሚያስፈልጋቸዉ አንድ ርምጃ ብቻ ነዉ። ጋምቦ ሙስሊም ስትሆን ማዕከላዊ ናይጀሪያ ዉስጥ የምትገኘዉ የጆስ ተወላጅ ናት። ጆስ ባለፉት ዓመታት የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች የሚያደርሱትን የከፉ ጥቃቶች አስተናግዳለች። ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2011ዓ,ም አንስቶም በፅንፈኞቹ ጥቃት 17 ሺህ ሰዎች አልቀዋል። በጥቅሉም ከሰሜን ናይጀሪያ 2,8 ሚሊየን ዜጎች የቀደሙ አባት እናቶቻቸዉ ለዘመናት ከኖሩበት አካባቢ በዚሁ ምክንያት ለመፈናቀል ተገደዋል። 
ካዲጃ ሃዋጃ ጋምቦ ሙስሊሞች ሆነዉ በቦኮ ሃራም ስብከት ወደአክራሪነት የተለወጡ በዕድሜያቸዉ ትናንሽ የሆኑ ልጆች በተደጋጋሚ የሚፈፀሙት የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቶች ይዘገንኗታል። 
ናይጀሪያ አፍሪቃ ዉስጥ ከሚገኙ እና ከፅንፈኛ ሙስሊሞች ጋር ግብግብ ከገጠሙ ሃገራት አንዷ ናት። ቦኮሃራም በሰሜን ናይጀሪያ ብቻ ሳይወሰን አጎራባች ሃገራትንም እያመሰ ነዉ። በምሥራቅ አፍሪቃም በሶማሊያ ስልጣን ለመጨበጥ አክራሪዉ አሸባብ ለዓመታት ውጊያዉን ቀጥሏል። ማሊ ዉስጥ ከሚንቀሳቀሱት መካከል ደግሞ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለዉ ፅንፈኛ ቡድን ይገኛል።  የተመድ እንደሚለዉ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2011 እስከ 2016 ባሉት ዓመት 33 ሺህ የሚሆን ሕዝብ የአክራሪዎች ጥቃት ሰለባ ሆኗል። አፍሪቃ ዉስጥ ወጣቶች ወደፅንፈኛ ቡድን በብዛት የሚሳቡትም በሃይማኖቱ አስተምህሮ ሳይሆን በድህነት እና አማራጭ ዕድል በማጣት መሆኑንም አመልክቷል። «ወደፅንፈኝነት ጉዞ» ለተሰኘዉ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት UNDP ላካሄደዉ ጥናት አፍሪቃ ዉስጥ ቀደም ሲል የፅንፈኛ ቡድኖች አባላት የነበሩ 500 ወጣቶች ተጠይቀዋል። አብዛኞቹ ሃይማኖቱ የሚለዉን አያዉቁም። 128 ገፅ ያለዉን ጥናት ያነበበችዉ ካዲጃ ሃዋጃ ጋምቦ ከጸሐፊዎቹ ሃሳብ ጋር ትስማማለች። እሷ እንደምትለዉም የሃይማኖቱን እዉነተኛ አስተምህሮ የሚያዉቅ እንደ ቦኮ ሃራም ያሉ ፅንፈኛ ድርጅቶች የሚሉት ፍፁም ተቃራኒ መሆኑን መረዳት አይከብደዉም።
«የእስልምና ትምህርት ማግኘት ያልቻሉ ሰዎች በአብዛኛዉ ደጋፊ እና ሰለባዎች ሲሆኑ የመመልመልና የእነዚህ አሸባሪ ድርጅቶች አባል የመሆን ዕድላቸዉም የሰፋ ነዉ። ምክንያቱም የኢስላምን ምንነት በቅጡ አልተረዱም። እናም ምንም ይሁን በእስላም ስም ከተነገራቸዉ ይቀበላሉ።»
የUNDP ጥናትም ጋምቦ ያለችዉን ነዉ የሚያረጋግጠዉ። ከተጠየቁት 57 በመቶ የሚሆኑት ስለእስልምና ሃይማኖት ያላቸዉ ዕውቀት ትንሽ ነዉ ወይም ደግሞ ምንም አያውቁም። የጥናቱ ጸሐፊ ማጠቃለያ በተለይም በገጠራማዉ እና የተሻለ ነገር በማይታይበት የአፍሪቃ አካባቢ «በሕይወቱ የተገፋ እና ችላ የተባለ የሚመስለዉ፤ ወጣት እና የመማር ዕድል ያላገኘ ሁሉ በፅንፈኞቹ ድርጅቶች መረብ እንደሚጠመድ ጠቁሟል። ለዚህም አንዱ ምሳሌ፤ ከአጎራባች ሃገራት ሳይቀር ተዋጊዎችን እየመለመለ በሶማሊያዉ የእርስ በርስ ጦርነት የሚያሰልፈዉ አሸባብ ነዉ። አላማቸዉ በአፍሪቃዉ ቀንድ እስላማዊ መንግሥት የማቋቋምና በመላዉ ዓለም «ቅዱስ» በሚሉት ጦርነት መሳተፍ ነዉ። 
ሞምባሳ፤ ኬንያ የሚገኘዉ ሃኪ አፍሪቃ የተሰኘ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ባልደረባ ሳልማ ሂሚድ፤ ወጣቶቹ በዚህ ቡድን የሚሳቡት በማይጨበጥ ተስፋ መሆኑን ይናገራሉ።
«ሶማሊያ ዉስጥ ሥራ እንደሚያገኙ ቃል ይገባላቸዋል። እናም እዚያ ከሄዱ ጥሩ እንደሚከፈላቸዉ እና ቤተሰቦቻቸዉን  መርዳት እንደሚችሉ ያስባሉ። ግን ይህ በምንም መልኩ እዉን አይሆንም።»
ይህም ሲታይ ወጣቶቹ ወደፅንፈኛ ቡድኖች የሚገቡበት መሠረታዊ ምክንያት ይበልጡን ኤኮኖሚያዊ መሆኑ ይገለጻል። ሳልማ ሂሚድ ወጣቶቹ እንዲህ ባሉት ፅንፈኛ ቡድኖች እንዳይጠመዱ የምክር አገልግሎት የሚያገኙባቸዉ ተቋማትን በመላዉ አፍሪቃ ማቋቋም አንዱ አማራጭ እንደሆነም ይመክራሉ። የአፍሪቃ ዳይሬክተር አብዱላዬ ማር ዲዬ፤ ጥናቱን ለአፍሪቃ መንግሥታት የማንቂያ ደወል ነዉ ብለዉታል። 

Somalia Restaurant Explosion
ምስል Picture alliance/AP Photo/F. Abdi Warsameh
Angola Jugendliche & Kinder in Luanda, Boa Vista Slum
ምስል Getty Images/AFP/S. de Sakutin

 አንቶኒዮ ካሽካሽ / ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ