1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕወሓትን በመቀሌ አጥብቆ የተቸውና የፕሬዚዳንቱ ኅልፈት

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 12 2011

ንግግራቸው በተደጋጋሚ ጭብጨባ የተቋረጠባቸው አቶ አምዶም በፈገግታ እንደተዋጡ፦«እሺ ሐሳቤን ላጠቃልል። ይኼ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ኮንፈረንስ መሰለኝ፤ የሕወሓት ጉባኤ አይደለም»» ሲሉ ተችተዋል። ከየአቅጣጫው ድጋፍ አግኝተዋል። የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ኅልፈትና ሥርዓተ ቀበርን በተመለከተ የቀረቡ አስተያየቶችንም አሰባስበናል

https://p.dw.com/p/3ASYZ
Addis Abeba, Trauerfeier für den ehemaligen äthiopischen Präsident Girma Wolde-Giorgis
ምስል Büro äthiopischer Premierminister

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በየሳምንቱ አንዳች አዲስ ነገር የማያጣው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ በዚህ ሳምንት የትኩረት አቅጣጫውን ወደ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጉባኤ አዙሯል። የአረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት ፓርቲ  የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አምዶም ገብረስላሴ ሕወሓቶችን በድፍረት መናገራቸው ከየአቅጣጫው አድናቆት እና ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል። ንግግራቸው በተደጋጋሚ ጭብጨባ የተቋረጠባቸው አቶ አምዶም በፈገግታ እንደተዋ አጨብጫቢዎቹን ተችተዋል። በዚህ ንግግራቸው ከየአቅጣጫው ድጋፍ አግኝተዋል። የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ኅልፈት እና ሥርዓተ ቀበርን በተመለከተ የቀረቡ አስተያየቶችንም አሰባስበናል።

ሕወሓትን በመቀሌ የተገዳደሩት ፖለቲከኛ

በዚሁ ሳምንት ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተለቀቀው አጭር የድምጽ እና ምስል መልእክት የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኖ ዘልቋል። ቪዲዮው በትዊተር እና በፌስቡክም በስፋት ተሰራጭቷል። አጭሩን ቪዲዮ ተመልክተው አስተያየት ከሰጡ ሰዎች መካከል ኤድና ዓለምአየሁ ለአቶ አምዶም ድፍረት የተሞላበት ንግግር አድናቆቷን ገልጣለች። «ልበ-ሙሉነቱ፣ ርጋታው እናም ያ ፈገግታው በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ሌላ አዲስ ትውልድ መሪ አገኘች፤ ቀልባችንን ጠቅልሎ ይዞታል። እኔስ ዛሬ ኹለ ነገሬ ስለ አምዶም ነው» ስትል ትዊተር ገጿ ላይ በእንግሊዝኛ ጽፋለች።

የአረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ በፌስቡክ ገጻቸው አጠር ያለ መልእክት አስፍረው የአቶ አምዶም ንግግርን ያካተተው ቪዲዮንም አያይዘዋል። አጭሩ መልእክት እንዲህ ይነበባል። «ይህንን ቪድዮ ተመልከቱና ዓምዶም ስለ ትግራይ ህዝብ ስቃይ ሲናገር እነማን እያጨበጨቡ እንዳስቆሙት እዩ። አሳፋሪ ድርጊት!» ይላል።

Emblem der Tigray People's Libration Font (TPLF)

በአጭር ቪዲዮው የአረና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምዶም ገብረስላሴ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጉባኤ ላይ ንግግር ሲያሰሙ ከታዳሚያኑ መካከልም የጭብጨባ ድምጽ ይሰማል። በወንበሮቻቸው መደገፊያ ወደ ኋላ ተለጥጠው እግሮቻቸውን አነባብረው በመሳቅ ከሚያጨበጭቡ ሰዎች መካከል አቶ ስብሐትም ይታያሉ።

ንግግራቸውን እንዳያሰሙ በተደጋጋሚ ጭብጨባ የተቋረጡት አቶ አምዶም በስተመጨረሻ፦ «እሺ ሐሳቤን ላጠቃልል። ይኼ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ኮንፈረንስ መሰለኝ፤ የሕወሓት ጉባኤ አይደለም» ሲሉ ቪዲዮው ይቋረጣል። የአረናው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ትችታቸውን ካሰሙ በኋላ ለእስር ተዳርገዋል የሚል መልእክት በዛው በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ ተሰራጭቷል። ታሰሩ መባላቸውን እሳቸውም ኾኑ ፓርቲያቸው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲያስተባብሉ፤ የለም መታሰራቸውን እርግጠኛ ነን «ለምንስ ለማስተባበሉ ያን ያኽል ዘገዩ?» የሚሉ ወገኖችም ተከራክረዋል።

አቶ አምዶም በፌስቡክ ገጻቸው ላይ፦«ወዳጆቼ ዓምዶም ታስረዋል የሚለው መረጃ ትክክል ኣይደለም። ኣልታሰርኩም። ስላሰባቹልኝ ኣመሰግናለው!» ሲሉ ማክሰኞ ታኅሣሥ 9 ቀን፣ 2011 ዓ.ም ጽፈዋል በአጭሩ። ሐሙስ ምሳ ሰአት ላይ ለDW በስልክ በሰጡት አጠር ያለ ቃለ መጠይቅ ደግሞ፦ «መታሰሩን አልታሰርኩም፤ ኅብረተሰቡ የሕወሓትን ባሕሪ ስለሚያውቅ የሚሰማውን ስሜት የገለጠበት ይመስለኛል» ብለዋል። በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ሰፊ መነጋገሪያ ስላደረጋቸው የመቀሌው ንግግራቸው እና ስለ ኅብረተሰቡ በማስቀደም ይናገራሉ።  

ስናፍቅሽ አዲስ ድሬ ትዩብ ላይ ባወጣችው የፌስቡክ ጽሑፍ፦«አደባባይ ላይ በጥይት ታስቆም የነበረችው ህወሃት አዳራሽ ውስጥ በጭብጨባ መታገል ጀምራለች፡፡ የአምዶም ዓይነቱን ወለጋም ጎንደርም ሐዋሳም ካበዛልን፤ ኢትዮጵያ የተተኪው ትውልድ ትሆናለች» ብላለች። ተሾመ ቦራንጎ በትዊተር ጽሑፉ «ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ ሕወሓትን በቤቱ የተገዳደረ አዲስ ጀግናዋ አምዶም ገብረሥላሴን አገኘች» የሚል አስተያየት ሰጥቷል።

Zusammenarbeit von Arena Tigray & Tigray democratic cooperation
ምስል DW/M. Haileselassie

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኅልፈት

ረቡዕ ታኅሣሥ 10 ቀን፣ 2011 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥርዓተ ቀብራቸው የተፈጸመው የቀድሞው የኢፊዴሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን በተመለከተ በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች የተለያዩ የድጋፍ እና የተቃውሞ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል።

ባለፈዉ ዐርብ ሌሊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቀድሞዉ የኢፊዴሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊርጊስ በሕይወት በነበሩበት ወቅት የዓይን ብሌናቸዉን ለመለገስ ቃል መግባታቸው መገለጡን በርካቶች አወድሰዋል። ለቀድሞው ፕሬዚደንት «ነፍስ ይማር» የሚሉ ማጽናኛዎችን የሰጡ ብዙዎች የመኾናቸውን ያኽል እንዲህ ያለ ክብር አይገባቸውም ያሉም ነበሩ። ለዚያ ደግሞ ምክንያታቸውን ሲገልጡ የነበረው ጨቋኝ አገዛዝን ሲቃወሙ አልታዩም የሚል ነው። ሣሙኤል ገብረሥላሴ የDW የፌስቡክ ገጽ ላይ ባሰፈረው የእንግሊዝኛ ጽሑፉ፦  «ለተጨናገፈው የ1997ቱ ዲሞክራሲ በዝምታቸው የደገፉ» ብሏል።

«ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የመንግሥት እና የስርዓት ለውጥ ሳያስደነብራቸው እና ከዚህኛው ወይም ከዛኛው ወገን ሳያስመድባቸው ሀገራቸው ኢትየጵያን በቅንነትና በታማኝነት ያገለገሉ የሀገር ትልቅ ሀብት ነበሩ» የኢብራሂም ሙሉሸዋ የፌስቡክ አስተያየት ነው።  

ለ12 ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ለነበሩት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የመጨረሻ ስንብት ሥርዓት የተከናወነው በሚሊኒየም አዳራሽ ነበር። በስንብቱ ቤተሰቦቻቸው፤ ባለሥልጣናት እና ሚኒስትሮች፣ እንዲሁም የውጭ ሃገራት አምባሳደሮች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ