1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕገወጥ የደን ወረራ በደቡብ ክልል

ሐሙስ፣ ጥር 2 2011

በደቡብ ክልል የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ እየተስፋፋ መጣው ሕገወጥ የደን ወረራ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ እየነገረ ነው ፡፡ በክልሉ የከፋ ዞን የአካባቢ ጥበቃና ደን ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው ካለፈው የሰኔ ወር አንስቶ በዞኑ በሚገኙ ስምንት ወረዳዎች ውስጥ ሃያ አምስት ሺህ ሄክታር የሚሸፍን የደን ይዞታ በሕገወጦች ተወስዷል፡፡

https://p.dw.com/p/3BKj9
Wald in Süd Äthiopien,
ምስል DW/ Shewangizaw W

«የከፋ ዞን ጥብቅ የተፈጥሮ ደን በተፈጥሯዊ መስህብነት በዩኔስኮ ተመዝግቧል»

 የደቡብ ክልል የአካባቢ፤ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው በተፈጥሮ ደኑ ላይ እየተካሄደ የሚገኘወን ወረራ ለመከላከል ወራሪዎቹን የመለየት እና ከደኑ ይዞታ የማስወጣት ሥራ መጀመሩን እየተናገሩ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ባለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከሚገኙት ጥቂት የደን ቅሪቶች መከከል እንዱ ጥቅጥቅ ባሉ አገር በቀል ዛፎች የተሸፈነው የከፋ የተፈጥሮ ደን ይገኝበታል፡፡  ይሁንእንጂ ይህ የተፈጥሮ ደን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ ህልውናው በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ መውደቁ እየተነገረ ይገኛል ፡፡ የከፋ ዞን የአካባቢ ጥበቃና ደን ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው የከፋ የተፈጥሮ ደን ካለፈው የሰኔ ወር አንስቶ በሕገወጥ ግለሰቦችና ቡድኖች እየተወረረ ይገኛል ፡፡ እስከአሁንም የተፈጥሮ ሀብቱ በሚገኝባቸው ስምንት ወረዳዎች ውስጥ ሃያ አምስት ሺህ ሺህ ሄክታር የሚሸፍን የደኑ ይዞታ በሕገወጦች መወሰዱን በጽሕፈት ቤቱ የደን ልማትና ጥበቃ ዋና ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ኢያሱ ወልደጊዮርጊስ ለዲ ደብሊው ገልጸዋል፡፡

Samuale Kekebo Regierungsbeamter in Süd-Äthiopien
አቶ ኢያሱ ወልደ ጊዮርጊስ

የከፋ ዞን ጥብቅ የተፈጥሮ ደን የአካባቢውን የአየር ሚዛን ከመጠበቁም በተጨማሪ ባለው ተፈጥሯዊ መስህብነት የተነሳ በዩኔስኮ ተመዝግቦ ይገኛል የሚሉት አቶ እያሱ አሁን የሚታየው ወረራ ከወዲሁ ካልተገታ በቀጣይ አለምአቀፍ ዕውቅናውን ሊነጠቅ ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸውም ጠቅሰዋል፡፡ ዲ ደብሊው በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የደቡብ ክልል የአካባቢ፤ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ቀቀቦ በበኩላቸው በከፋ ዞን የተፈጥሮ ደን ላይ ህገ ወጥ ወረራ መካሄዱን አረጋግጠዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ባለሥልጣን መሥሪያቤቱ ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት ህገ ወጥ ወራሪዎቹን የመለየት እና ከደኑ ይዞታው የማስወጣት ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ የሀዋሳው ወኪላችን ሸዋንግዛው ወጋየሁ ዝርዝሩን ልኮልናል።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ